ኃይሌ ገብረሥላሴ ናይሮቢ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዘጋጅ ሆና መመረጧን "አስደናቂ ዜና" ሲል አሞካሸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የ2029 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በናይሮቢ እንዲዘጋጅ መወሰኑ በመላው አፍሪካ ደስታ እና መነቃቃት ፈጥሯል።

የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ 10,000 ሜትር ሻምፒዮን የሆነው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በዓለም አትሌቲክስ ማክሰኞ ዕለት ይፋ የተደረገውን ውሳኔ "አስደናቂ ዜና" ሲል ያሞካሸ ሲሆን፣ ለመላው አፍሪካውያን የእንኳን ደስ አለን መልዕክት አስተላልፏል።

የኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ፣ ከዚህ ቀደም የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ያስተናገዱትን ለንደንን እና ሮምን አሸንፋ ውድድሩን በማስተናገድ የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ከተማ ለመሆን ታጭታለች።

የዓለም ምርጥ አትሌቶች ከሦስት ዓመታት በኋላ 48,000 ተመልካቾችን የሚያስተናግደውን የካሳራኒ ስታዲየም እንደሚያጥለቀልቁ የተሰማው ዜና፣ በምሥራቅ አፍሪካ ባሉ ታላላቅ አትሌቶች ዘንድ የደስታ ስሜት ፈጥሯል።

ይህ ስፖርት በኬንያ እጅግ ጠንካራ የደጋፊዎች መሠረት ያለው መሆኑን መነሻ በማድረግ፣ ብዙዎች "አትሌቲክስ ወደ ቤቱ እየተመለሰ ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ከዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ወቅት በፊት በአውሮፓውያኑ ቀጣይ ዓመት 2027 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድርን ለማስተናገድ እየተሰናዳ በሚገኘው የካሳራኒ ስታዲየም ውስጥ የሚኖረው ድባብ "የተለየ" እንደሚሆን ይጠብቃል።

"ይህ በሕዝብህ ፊት፣ በከተማህ የሚከናወን በጣም ትልቅ [ውድድር] ነው" ሲል ተናግሯል።

አክሎም "ብዙ ተመልካቾች ወደ ናይሮቢ ይበራሉ፤ ብዙዎችም የራሳቸውን አትሌቶች ሲወዳደሩ የማየት ዕድል ያገኛሉ" ብሏል።

ዝግጅቱ "እጅግ ድንቅ" እንደሚሆን እምነቱን ገልፆ "እኔም ራሴ ውድድሩን በስፍራው ተገኝቼ እመለከታለሁ" ብሏል ተወዳጁ አትሌት በናይሮቢ አዘጋጅነት የተሰማውን ደስታ ሲገልፅ።

"እንደ እግር ኳስ ሁሉ፣ በሜዳህ መጫወት እና ከሜዳህ ውጭ መጫወት የተለያዩ ናቸው" የሚለው ኃይሌ፣ በመሆኑም የ2029 ሻምፒዮና በናይሮቢ መዘጋጀቱ "ለኬንያውያን ትልቅ ዕድል ነው፤ ለኢትዮጵያውያንም ትልቅ ዕድል ነው" ብሏል።

'ለአፍሪካ ትልቅ ነገር ነው'

ሌሎች አትሌቶችም የኃይሌን ሃሳብ ይጋራሉ።

በ2015 የዓለም የጦር ውርወራ ሻምፒዮን የሆነው ጁሊየስ ዬጎ፣ በአዘጋጅነት መመረጥ ለአፍሪካ "ትልቅ ነገር ነው" ብሏል።

"ዓለም ወደ ኬንያ የሚመጣ በመሆኑ እጅግ ደስተኛ ነኝ" ሲል የ37 ዓመቱ አትሌት ለቢቢሲ ተናግሯል።

"አፍሪካ ምርጥ አትሌቶችን አፍርታለች፣ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ትልቅ ሻምፒዮና በቅርበት የመመልከት ዕድል አልነበረንም ያለው ዬጎ፣ "ይህ ከመላው ዓለም ሰዎችን ወደ አፍሪካ የሚያመጣ እና ሰዎች አፍሪካን የሚያውቁበት መድረክ ነው" ሲል አክሏል።

ኬንያውያን ለአትሌቲክስ ባላቸው ፍቅር ይታወቃሉ። በዓለም አትሌቲክስ በተካሄደ ጥናት ውስጥ ከተሳተፉት የአገሪቱ ዜጎች መካከል፣ 68 በመቶዎቹ ለስፖርቱ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

ቀጣዩን ትውልድ የሚያነሳሳ ነው

እአአ በ2007 የጃፓን ኦሳካ የዓለም ሻምፒዮና የሴቶች 800 ሜትር ወርቅ ያሸነፈችው ጃኔት ጄፕኮስጌይ፣ "አስደሳች" ያለችው ይህ ውሳኔ ቀጣዩን የአትሌቶች ትውልድ እንደሚያነሳሳ ታምናለች።

"ይህ ለወጣቶችና ለታዳጊ አትሌቶች በጣም ትልቅ ትርጉም አለው፤ ምክንያቱም ትልቅ ራዕይ እንዲሰንቁ ያደርጋቸዋል" ብላለች።

ውድድር ካቆመች በኋላ ፊቷን ወደ አሰልጣኝነት ያዞረችው ጄፕኮስጌይ፣ ተስፋ የሚጣልባቸው አትሌቶችን ለማዘጋጀት የሦስት ዓመታት ጊዜ መኖሩን በማንሳት፣ የናይሮቢው የ2029 ሻምፒዮና "ወጣቶች ተሰጥኦአቸውን የሚያሳዩበት እድል ነው" ስትል ተናግራለች።

"ከአትሌቶቼ ጋር ስነጋገር ቆይቻለሁ፤ እነሱም በሰጡኝ አስተያየት 'ውድድሩ ወደ ቤታችን መጥቷል፤ እኛም በዚያ፣ መገኘት አለብን' እያሉ ነው"ስትል አክላለች።

የአፍሪካ የ100 ሜትር ሪከርድ ባለቤት የሆነው የአጭር ርቀት ሯጩ ፈርዲናንድ ኦማንያላ፣ በ2017 ናይሮቢ የዓለም ከ18 ዓመት በታች ሻምፒዮናን ማስተናገዷ ከፍተኛ መነሳሳትን ፈጥሮለት እንደነበር ያስታውሳል።

የ30 ዓመቱ አትሌት፣ የ2029 ውድድርም እንዲሁ ለአሁን አትሌቶችም ሆነ ቀጣይ ለሚመጡት "ትልቅ መነቃቃት" እንደሚፈጥር እምነቱን ገልጿል።

አፍሪካ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ውስጥ ብዙ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን ታስተናግዳለች። ከእነዚህም አንዱ በሴኔጋል ዳካር የሚዘጋጀው በቀጣዩ ኅዳር ወር ላይ የሚሰናዳው የወጣቶች ኦለምፒክ ነው።

ደቡብ አፍሪካ፣ ዝምባብዌ እና ናሚቢያ ደግሞ በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት የወንዶችን የዓለም የክሪኬት ዋንጫ ሲያስተናግዱ፣ ሞሮኮ ደግሞ ከስፔን እና ፖርቹጋል ጋር የ2030 የዓለም ዋንጫን በማስተናገድ ከ2010 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ውድድሩ ወደ አፍሪካ እንዲመለስ ታደርጋለች።

ኬንያ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን እንድታዘጋጅ መመረጧ እና ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማዘጋጀት ዕድል ማግኘታቸው፣ ቀሪዎቹ የአህጉሪቱ አገራትም ቢሆኑ ትልልቅ ውድድሮችን ማስተናገድ እንደሚችሉ በራስ መተማመን እንደሚፈጥርላቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

"ይህ ትልቅ ዕድል ነው። በስፖርት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ እና በፖለቲካም አፍሪካውያን የፈለጉትን ማሳካት ይችላሉ" የሚለው ኃይሌ፣ "ናይሮቢ ይህን ሻምፒዮና ማዘጋጀት ከቻለች አዲስ አበባ፣ ሌጎስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኡጋንዳ ወይም ሩዋንዳ ማዘጋጀት የማይችሉበት ምክንያት ምንድነው?" በማለት የይቻላል ስሜትን እንደሚፈጥር አስረድቷል።