ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሕገ ወጥ ስደት ላይ እርምጃ ለመውሰድ መመሪያዎችን ይፋ አደረጉ
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ስሪል ራማፎሳ በአገሪቱ ፀረ ስደኛ ተቃውሞ እና ውጥረት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሕገ ወጥ ስደተኞች ላይ አዳዲስ እርምጃዎችን ለመውሰድ ይፋ አደረጉ።
ከእርምጃዎቹ መካከል ቀጣሪዎች ሰነድ የሌላቸውን ሠራተኞች ከቀጠሩ እስር፣ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችን ከአገር የሚያባርር ሥራን ለማፋጠን ራሱን የቻለ ፍርድ ቤት ማቋቋም እንዲሁም የማንነት መለያ ስርቆትን ለመቆጣጠር "በአገሪቱ ያለ እያንዳንዱ ሰው" የ'ባዮሜትሪክ" መረጃዎች እንዲመዘገብ የሚሉት ይገኙባቸዋል።
ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ደቡብ አፍሪካዊያኑ ሕግን በራሳቸው እጅ እንዳያስፈፅሙ አስጠንቅቀዋል።
ባለፉት ሳምንታት የአመፅ ስጋቱ በመጨመሩ በርካታ የአፍሪካ አገራት ዜጎቻቸውን ከደቡብ አፍሪካ እያስወጡ ነው።
የፀረ ስደተኛ ተቃዋሚዎች ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞች እስከ ሰኔ 23/2018 ዓ.ም. ድረስ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ቀን ቆርጠዋል።
በዌስተርን ኬፕ ግዛት ቤት ለቤት በተደረገ ማስፈራራት እንዲሁም ሞሰል ቤይ በተባለ ስፍራ ሁለት የሞዛምቢክ ዜጎች መገደላቸውን ተከትሎ ባለፈው የሳምንቱ መገባደጃ ቀናት በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍሪካዊ ስደተኞች አገሪቱን ለቀው ወጥተዋል።
በርካታ ስደተኞች በማኅበረሰብ አዳራሾች፣ በባሕር ዳርቻዎች አሊያም በተራራማ ስፍራዎች ለመጠለል ተገደዋል። አንዳንዶች ደግሞ ወደ አገራቸው ለመመለስ የመረጡ ሲሆን ባለፈው ሳምንት የ140 ሰዎች ቡድን ወደ ማላዊ እና ሞዛንቢክ ተመልሷል።
በደርባን የውጭ አገር ሰዎች ለበርካታ ሳምንታት ለሕይወታችን እንሰጋለን በማለት በአገር ውስጥ መስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ አካባቢ ተጠልለዋል።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ሕገ ወጥ ስደት በደቡብ አፍሪካ የሕዝብ ግልጋሎት ላይ ጫና ማሳደሩን እውቅና ሰጥተው፤ ጉዳዩ በመንግሥታቸው እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይፋ ያደረጓቸው አምስት ቁልፍ ስልቶች፤ ሕግ በሚጥሱት ላይ እርምጃ መውሰድ፣ ጠንካራ የድንበር ደኅንነት፣ በኢምግሬሽን ስርዓቱ ላይ ያለውን ሙስና ማስወገድ፣ የኢምግሬሽን ሕጉ ላይ ያሉ ክፍተቶችን መድፈን እንዲሁም ችግሩን ለመፍታት ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር መስራት ናቸው።
ራማፎሳ ሰዎች ተደራጅተው የሚወስዱትን እርምጃ አስጠንቅቀዋል።
"ለምሳሌ መንገድ ላይ ሰውን አስቁሞ ዜግነታቸውን ለማረጋገጥ ማስረጃ መጠየቅ ማንም ሰው አልተፈቀደለትም" ብለዋል።
አንዳንድ ተንታኞች የመጤ ጠልነት አዝማሚያው ደቡብ አፍሪካ በመጭው ኅዳር ከምታካሄደው የአካባቢ ምርጫ ጋር ይያያዛል እያሉ ነው።
ፕሬዝዳንቱ ምክንያታዊ የሆነ ስጋትን በመያዝ አመፅ በመቀስቀስ አገሪቱን "ለማተራመስ" የሚጠቀሙ ቡድኖችን እንዲንቀሳቀሱ አንፈቀድላቸውም ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ ሦስት ሚሊዮን ለሚሆኑ የውጭ አገር ዜጎች መኖሪያ መሆኗ ይፋዊ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፤ ይህም ከአገሪቱ ጠቅላላ ሕዝብ አምስት በመቶ ገደማ ነው። ይሁን እንጅ ከዚህ በላይ በርካታ ስደተኞች ያለ ሕጋዊ ሰነድ በአገሪቱ እንደሚኖሩ ይታመናል።
ፕሬዝዳንት ስሪል ራማፎሳ 30 ደቂቃ በወሰደ ንግግራቸው የችግሩን ስፋት እና የሕገ ወጥ ስደት መስመሮች ከተደራጀ ወንጀል ጋር እንዴት እንደሚተሳሰሩ ገልፀዋል።