ስፔን ለ500 ሺህ ሕገ ወጥ ስደተኞች ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ልትሰጥ ነው

በሳይክል እቃ የማድረስ ሥራ ላይ ያለ ስደተኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝ እርምጃው የዕለት ተዕለት ሕይወታችን አካል የሆኑ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ሠዎችን ይፋዊ እውቅና ለመስጠት ነው ብለዋል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የስፔን መንግሥት 500 ሺህ ለሚሆኑ ሕገ ወጥ ስደተኞች ሕጋዊ ሰነድ በመስጠት መደበኛ የሥራ ኃይሉን እንዲቀላቀሉ የሚያደርገውን ዕቅድ አፀደቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ የመንግሥታቸውን ውሳኔ "የፍትህ እርምጃ" እና "ለስፔን አስፈላጊ" ሲሉ ገልፀውታል።

ለስፔናዊያን በማኅበራዊ የትስስር ገፆች በተሰራጨ ደብዳቤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝ የጅምላ ሕጋዊ የማድረግ እርምጃው "የዕለት ተዕለት ሕይወታችን አካል የሆኑ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ሠዎችን በይፋ እውቅና ለመስጠት ነው" ብለዋል።

ፒፒ የተባለው የስፔን ወግ አጥባቂ ፓርቲ ሕገ ወጥ ስደተኞችን የሚሸልም እና ተጨማሪ ስደተኞችም እንዲመጡ የሚያበረታታ ነው በማለት ሕጉን እንደሚያግድ አሳውቋል።

የመንግሥት ዕቅድ ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞች በአንድ ዓመት የሚታደስ የመኖሪያ ፈቃድ ይሰጣል። አመልካቾች ብቁ ለመሆን ስፔን ውስጥ ለአምስት ወራት ያህል መኖራቸውን ማስመስከር እና የወንጀል ማኅደር እንደሌላቸው ማቅረብ አለባቸው። ለማመልከት የተሰጣቸውም ጊዜ ከነገ ሐሙስ ጀምሮ እስከ መጪው ሰኔ ድረስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝ ስደተኞች የሆነውን እና ለመሆን የምንፈልገውን ከበርቴ፣ ክፍት እና ብዝኃ የሆነች ስፔን ለመገንባት ያግዛሉ ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማስቀጠል እና የሕዝብ ቁጥሩ እያረጀ ላለው ማኅበረሰብ ሕዝባዊ አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

አክለውም በታሪክ አብዛኞቹ የራሷ ዜጎችም የተሻለን ዕድልን ፍለጋ ስደተኞች ለነበሩባት አገር ትክክለኛ መንገድን የያዘ እርምጃ ነው ሲሉ ስለ ዕቅዳቸው ተናግረዋል።

ዘ ፉንካስ የተባለው የሊሂቃን ስብስብ በስፔን 840 ሺህ የሚሆኑ ሰነድ አልባ ስደተኞች እንደሚገኙ የሚገምት ሲሆን፤ አብዛኞቹም ላቲን አሜሪካዊያን ናቸው።

ቋሚ ሥራ ማግኘት ፈተና ሆኖበት የቆየው ቦሉቪያዊው ሪካርዶ ሰነድ ለማግኘት የማመልከት ውጥን ያለው ሲሆን፤ "ይህ ብዙ ሠዎችን የሚጠቅም ነው። የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ መስራት የሚችሉበትን ዕድል ስጧቸው" ይላል።

"እና ይህም ማለት ለስፔን መንግሥት ተጨማሪ ገንዘብ ማለት ነው። ተጨማሪ ሠራተኞች ለአሰሪዎቻቸው በሕጋዊ መንገድ ይገኛሉ" ብሏል ሊኖረው የሚችለውን አዎንታዊ ተፅዕኖ በመጥቀስ።

የመንግሥት ተቃዋሚዎች ግምታዊ ቁጥሮች ስህተት መሆናቸውን በመግለፅ ለዚህ ዕድል አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ስደተኞች ያመለክታሉ ብለዋል።

ፒፒ የተበላው ወግ አጥባቂ ፓርቲ ዕድቁን "የሚያበሳጭ" ሲል ገልፆታል።

በአንፃሩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት ያወጣውን ሕግ ደግፋለች።

የስፔን እርምጃ አብዛኞች ጎረቤቷ የሆኑ የአውሮፓ አገራት ስደተኞች ላይ ሕጋቸውን ጠበቅ እያደረጉ ባለበት ጊዜ የመጣ ነው።

ከዚህ ቀደም የስፔን ሁለቱም ሶሻሊስት እና ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች የስደተኛ ሕጋቸውን አሻሽለዋል። በቅርብ ከተሻሻሉት ውስጥ እ.አ.አ በ2005፤ በሶሻሊትስት መንግሥት አስተዳደር 577 ሺህ ስደተኞች የመኖሪያ ፈቃድ አግንተዋል።