የኤርትራው ፕሬዝዳንት በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ካይሮ አመሩ

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ከግብፅ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ሲወያዩ

የፎቶው ባለመብት, @hawelti

የምስሉ መግለጫ, የኤርትራው ፕሬዝዳንት በካይሮ ከግብፅ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ሲወያዩ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሦስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ወደ ግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ተጉዘዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከግብፅ ጋር ያላቸው ግንኙነት እየተጠናከረ የመጣው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ካይሮ ሲያመሩ በዚህ ዓመት ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ግብፅ ያመሩት እሁድ ግንቦት 30 2018 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በቀጣናው ደኅንነት፣ በአፍሪካ ቀንድ እና መካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ ተገልጿል።

ስለ ፕሬዝዳንቱ ጉብኝት በኤክስ ገጻቸው ላይ የጻፉት የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር የሁለቱ መሪዎች ውይይት በአፍሪካ ቀንድ፣ የቀይ ባሕር ደኅንነት እና በመካከለኛው ምሥራቅ ባሉ መጠነ ሰፊ ለውጦች ዙሪያ እንደሚያተኩር ገልጸዋል።

ወደ ግብፅ ካመራው የኤርትራ ፕሬዝዳንት ልዑካን ቡድኑ ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውም ተካትተዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በጥቅምት ወር በካይሮ ባደረጉት የአምስት ቀናት ጉብኝት ወቅት አል ሲሲ አገራቸው "የኤርትራን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለመደገፍ ቁርጠኛ" መሆኗን ተናግረው ነበር።

ከኢትዮጵያ ጋር በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ለዓመታት ውዝግብ ውስጥ የምትገኘው ግብፅ፣ ሶማሊያን ጨምራ ባለፈው ዓመት ከኤርትራ ጋር የትብብር ጥምረት ፈጠራቸው ይታወሳል።

ግብፅ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ ባለፈው ዓመት ጥቅምት የጋራ ግንባር የመሠረቱት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በግንቦት ወር የግብፅ እና የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተገናኝተው በቀይ ባሕር እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ እና የግብፅ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሌተናንት ጄነራል ከማል አልዋዚር፤ ግንቦት 8/2018 ዓ. ም. ወደ አሥመራ በማምራት ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተወያይተዋል።

ከዚህ ውይይታቸው በኋላ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ "የቀይ ባሕር አስተዳደር እና ደኅንነት ጉዳይ በዋነኛነት የሚመለከተው የቀይ ባሕር አጎራባች አገራትን ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት ተከትሎ ከኢትዮጵያ በኩል ስጋት የተደቀነባት ኤርትራ ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ በኩል የድጋፍ ማረጋገጫ ያገኘች ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሥመራ በተገኙበት ወቅትም ፕሬዝዳንቱ ይህንኑ በድጋሚ እንዳረጋገጡላቸው ተገልጿል።

የአሁኑ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጉብኝት የተሰማው በቀጣናው ከቀይ ባሕር ጋር በተያያዘ ያለው ውጥረት በተካረረበት ወቅት ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት አጀንዳዋን ይፋ ካደረገች በኋላ ግብፅ "ከበባ በሚመስል መልኩ" እየተንቀሳቀሰች ነው ስትል ኢትዮጵያ ክሷን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በኩል አሰምታለች።

ቃል አቀባዩ ይህንን ያሉት ቀይ ባሕር ላይ የሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን እና የወደብ ትስስርን በተመለከተ ግብፅ እና ኤርትራ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ነቢያት ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ቅድሚያ የምትሰጠው አጀንዳ መሆኑን ካነሳች ጊዜ ጀምሮ ከግብፅ በኩል "ውጥረት፣ ትንኮሳ የሚመስሉ ነገሮች እየታዩ" መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄዋን ዲፕሎማሲያዊ በሆኑ መንገድ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የባሕር በር አጀንዳ መነሳትን ተከትሎ ግብፅ በኢትዮጵያ ዙሪያ ከሚገኙ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ከማጠናከር አልፋ በአንዳንድ አገራት ውስጥ ሠራዊቷን የመሰማራት እንቅስቃሴ እያደረገች ነው።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት "ጽምዶ" በሚባለው እንቅስቃሴ በኩል "በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የሚቃጣ" ስጋት ቢኖር ስለሚወስደው እርምጃ አገር ውስጥ ለሚገኘው ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ማሳወቁን ተናግሯል።

የመከላከያ የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክተር ይህንን እንቅስቃሴ "'ወደ መሬት እናወርዳለን' ብለው ስንዝር እንቅስቃሴ" የሚያደርጉ አካላትን አስጠንቅቀዋል።

ዳይሬክተሩ ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ "ጽምዶ" በሚለው ስያሜ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች እና በኤርትራ መካከል ይደረጋል ስለሚባለው እንቅስቃሴ ሲናገሩ "ፀረ ሉዓላዊነት" በማለት ጠርተውታል።

አክለውም ጫንቃቸውን ለፈርኦን ቀንበር" በሰጡ የኢትዮጵያ አካላት እና "አካባቢው ላይ ባሉት ስብስብ" የተፈጠረ ነው ብለዋል።

"ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ነገ ትልቅ [እርምጃ] የሚያስወስድ ጉዳይ ቢነሳ የማንንም ፈቃድ መጠየቅ እንኳ ባያስፈልግ፤ ወዳጆቻችን፣ አብረውን የሚሠሩ ሰዎች የውጪ ሰዎች ይሄን ሐሳብ እንዲገነዘቡ ማድረግ ተገቢ" መሆኑንም አብራርተዋል።

ሜጀር ጄነራል ተሾመ፤ የውጭ ጉዳይ ሚስቴርም በዚሁ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ ሥራ ያከናውናል የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለዋል።

በ"ጽምዶ" እንቅስቃሴ የሚሳተፉ አካላት ሃሳባቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚንቃቀሱ ከሆነ ". . . እንደ ሉዓላዊ አገር ይሄ ተቋም ደግሞ በመንግሥት ግዳጅ እንደተሰጠው፣ ኃላፊነት እንደተሰጠው፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሥራ እንደሚሠራ አካል፤ ሰም በእሳት እንደሚቀልጥ ይቀልጣሉ ብለን ነው የምናስበው፣ የምናምነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን በአገሪቱ ውስጥ ሰላምን ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው የሚሏቸውን ቡድኖች በኤርትራ እና በግብፅ የሚደገፉ ናቸው በማለት ይከስሷቸዋል።