ትራምፕ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ለመገደብ ያደረጉት አዲስ ጥረት በዳኛ ውድቅ ተደረገ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ለመገደብ በድጋሚ ያደረጉት ሙከራ በፍርድ ቤት ዳኛ ውሳኔ ታገደ።

ፕሬዝዳንቱ ከዚህ ቀደም ያሳለፉት መሰል ውሳኔ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከተሻረ በኋላ ነበር እንደ አዲስ እርምጃውን ለመውሰድ የወሰኑት።

የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ተከትሎ፣ ትራምፕ "የውጭ ጠላቶች" ላሏቸው ልጆች እና ለመውለድ ብለው ወደ አሜሪካ የሚሄዱ ሰዎች ለሚወልዷቸው ህጻናት ዜግነት እንዳይሰጥ የሚደነግግ አድማሱ የጠበበ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

ይህም ትዕዛዝ ቢሆን ግን በዩናይትድ ስቴትስ የሚወለዱ ህጻናት በቀጥታ የአሜሪካ ዜግነት እንደሚያገኙ የሚደነግገውን ሕገ-መንግሥታዊ መብት ሊጥስ የሚችል ነው ሲሉ የፍርድ ቤቱ ዳኛ ዲቦራ ቦርድማን ተናግረዋል።

ቦርድማን፣ ረቡዕ ዕለት ባሳለፉት ውሳኔ የስደተኞች ተሟጋች ቡድኖች ያቀረቡት ክስ እስኪፈታ ድረስ የትራምፕን ትዕዛዝ ለጊዜው አግደዋል። የትራምፕ አስተዳደር ይግባኝ ሊያቀርብ ይችላል።

"የ2026ቱ ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ በእርግጠኝነት ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ነው" ሲሉ ቦርድማን ጠቅላይ ፍርድ ቤት በትራምፕ የቀደመ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን የመገደብ ጥረት ላይ የሰጠውን ውሳኔ በመጥቀስ ተናግረዋል።

"ይህ ፍርድ ቤት አሁንም በድጋሚ የፕሬዝዳንቱን የዜግነት መብት የመንጠቅ አዲስ ሙከራ ተፈጻሚ እንዳይሆን በጊዜያዊነት ማገድ አለበት" ብለዋል።

የስደተኞች ተሟጋች ቡድኖች የትራምፕን ውሳኔ በመቃወም ክስ ከፍተዋል። ክሱን ያቀረቡት፣ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ለሚወልዷቸው ልጆች ዜግነት እንዳይሰጥ በሚል ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዚህ ቀደም የፈረሙት ትዕዛዝ እንዲቀለበስ ለማድረግ ነው።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰኔ ወር ላይ የትራምፕን ትዕዛዝ ከሻረ በኋላ፣ ፕሬዝደንቱ ይዘቱን በማጥበብ አዲስ ትዕዛዝ የፈረሙት ብዙም ሳይቆዩ ነሐሴ ወር ላይ ነው። አዲሱ ትዕዛዝ፣ በአሜሪካ የተወለዱ ልጆች በቀጥታ ዜግነት ስለሚያገኙ ነፍሰጡር ሴቶች ለመውለድ ወደ አሜሪካ የሚሄዱበትን "የመውለድ ቱሪዝም" ዒላማ ያደረገ ነው።

ለመውለድ ብቻ በሚል ወደ አሜሪካ መጓዝ አስቀድሞም ቢሆን በአሜሪካ ሕግ አይፈቀድም። አዲሱ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ይህንን ልምምድ ለማስቀረት የሚያስችሉ ደንቦችን ማጥበቅ እና ተግባራዊ ማድረግ ላይ ያተኩራል።

ትዕዛዙ በተጨማሪም፣ "የውጭ ጠላቶች" ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ወላጆች ለሚወልዷቸው ልጆች የዜግነት መብትን ይነፍጋል። "የውጭ ጠላቶች" የሚለው አገላለፅ ለአሸባሪ ድርጅ አባላት እና ለዕፅ አዘዋዋሪዎች የሚውል ነው።

የነሐሴው ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ፣ ወላጆቻቸው በአሜሪካ ውስጥ ለውጭ መንግሥታት የሚሰሩ ልጆችም ዜግነት እንዳያገኙ ይከለክላል።

የመንግሥት ጠበቆች፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሰኔ ወር ያሳለፈው ውሳኔ በመወለድ የሚገኝ የዜግነት መብትን መገደብ የሚያስችሉ ሌሎች ጠባብ አማራጮችን እንደማያግድ ተከራክረዋል።

አስቀድሞም የዲፕሎማት ልጆችን እና የውጭ ጠላቶችን ጨምሮ በልዩ ሁኔታ ገደብ ሊጣልባቸው እንደሚችል የተፈቀዱ አሉ በማለት አስረድተዋል።

የቢቢሲ የሚዲያ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ እንደዘገበው "ይህ በባይደን የተሾሙ አክቲቪስት ዳኛ የተላለፈ የፕሬዝዳንት ትራምፕን ምክኒያታዊ አጀንዳ የሚደናቅፍ ሌላ ውሳኔ ነው" ሲሉ የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።

በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን በተመለከተ የወጣው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ "ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይዘቶች እና ትንታኔዎች ጋር የሚጣጣም ነው" ሲሉም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ነቅፈዋል።

በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ለማስቀረት ወይም ለመቀነስ የሚደረጉት የትራምፕ ተደጋጋሚ ሙከራዎች፣ ወደ አሜሪካ የሚደረግ ስደትን እና ፍልሰትን ለመቀነስ የሚተገበረው ትልቅ ስትራቴጂ አካል ናቸው።

ይህ ስትራቴጂ ለብዙ አገሮች የተሰጠውን ጊዜያዊ ከለላ ማቆም እና በተለያየ ምክንያት የውጭ ዜጎችን ከአገር ማባረርን ያካትታል።