ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የነዋሪዎችን ሕይወት የቀጠፉት የሰሞኑ የምሥራቅ ወለጋ ጥቃቶች እና የነዋሪዎች ስጋት
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ሰሞኑን በተፈፀሙ ጥቃቶች በርካታ ሲቪሎች መገደላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ከነሐሴ ወር መጀመሪያዎች አንስቶ በክልሉ መንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች እንደነበሩ የሚገልፁት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ግጭቶቹ እየቀጠሉ ሲሔዱ ሲቪሎችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች መከተላቸውን ተናግረዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም የፋኖ ታጣቂዎች ፈፀሙት በተባለ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች ታፍነው መወሰዳቸውን ተከትሎ ደግሞ፣ የክልሉ ኃይሎች ወሰዱት ባሉት "አፀፋዊ እርምጃ" ብዙዎች መገደላቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ለቢቢሲ አብራርተዋል።
ግጭቶች መቀጠላቸውንም ገልፀዋል።
በሰሞኑ ጥቃቶች በርካታ ንብረት ሲወድም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉም አያሌ ናቸው።
ወትሮም ሰላም የራቀው ይህ አካባቢ፣ የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ ወዲህ ባሉት ያለፉት ስምንት ዓመታት ደግሞ ተባብሶበት ቀጥሏል።
አካባቢው ከኦሮሞ ማኅበረሰብ በተጨማሪ በደርግ ዘመነ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ወደ አካባቢው የሄዱ በተለይም የአማራ እና የትግራይ ማኅበረሰቦች በመንደር በመንደር ሰፍረው የሚገኙበት ሲሆን የተለያዩች ብሔረሰብ አባላትም ይገኙበታል።
ግጭቶች እና የሰላማዊ ሰዎች ግድያዎች ለአካባቢው አዲስ ባይሆኑም፣ በተለይ ያለፉት 6 ወራት ተደጋጋሚ ግድያዎች እና የንብረት ውድመቶች የሚስተዋሉበት ነበር ይላል የሰሞኑን ሁኔታ በተመለከተ ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች መካከል የሆኑ ግለሰብ።
ቢቢሲ ስለሰሞነኛው ጥቃት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት ሲዘዋወር የነበረውን በጥቃቱ የተገደሉ ካህን የቅርብ ዘመድን ጨምሮ ሰባት የአካባቢውን ነዋሪዎች አነጋግሯል።
በታጣቂዎች መካከል ሲካሔድ የነበረው ግጭት ሲቪሎችን ወደማጥቃት ስለመሸጋገሩ፣ አምቡላንስ ውስጥ የነበረ ታማሚን እና ከሕጻን ልጇ ጋር እንዳለች በልጇ ፊት የተገደለች ነፍሰጡር እናትን ጨምሮ የሰሞኑ ጥቃት ሰለባ ስለሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በዝርዝር ነግረውናል።
ካናገርናቸው የወረዳው ነዋሪዎች ያገኘናቸው አስተያየቶች እጅግ ተቀራራቢ እና እርስ በርስ የሚደጋገፉ ናቸው።
ቢቢሲ ጥቃቶቹ ከተፈጸሙባቸው ቦታዎች የዐይን እማኞች እና ከሰለባዎች ቤተሰቦች ያገኛቸውን መረጃዎች በተመለከተ ከባለሥልጣናት አስተያየት ለማግኘት ለቀናት የዘለቀ ጥረት ቢያደረግም ምላሽ አላገኘም።
በጥቃቶቹ ቤተሰብ እና ዘመድ ያጡ መሆናቸውን የሚገልፁት ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለፅ ጠይቀዋል።
"የፋኖ ጥቃት"፡ "13 ቤት ለቅሶ ደርሻለሁ"
ነሐሴ 13 በፋኖ የተፈፀመውን ጥቃት በቦታው ተገኝቼ ተመልክቻለሁ ያሉን የጊዳ አያና ወረዳ ነዋሪ፣ ከዚያ ጥቃት በፊት ባሉት ቀናት የፋኖ ታጣቂዎች ከሚሊሻዎች ጋር በተለያዩ ቦታዎች ተኩስ ሲለዋወጡ እንደነበር ይገልፃሉ።
ሚሊሻዎች መቋቋም ሲያቅታቸው "ገዳ ኮማንዶ" በመባል የሚታወቀው በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የተቋቋመ "ልዩ ኮማንዶ ገብቶ ከፋኖ ጋር ፊትለፊት ሲዋጋ ነበር" በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል።
በአካባቢው ባለው ስጋት ምክንያት የሕዝብ መገልገያ ተሽከርካሪዎች ተሰባስበው በመከላከያ ሠራዊት እየታጀቡ ነው የሚንቀሳቀሱት።
ረቡዕ ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም የሕዝብ ማመላለሻ፣ የጭነት እና ሌለች ተሽከርካሪዎች በመከላከያ እጀባ ከጊዳ አያና ወደ ነቀምቴ ሲጓዙ በነበሩበት ወቅት፣ ቱሉ ሌንጫ በምትባል ቀበሌ ውስጥ በሚገኝ ተራራማ አካባቢ ላይ ደፈጣ አድርገው ሲጠብቁ ነበሩ ያሏቸው የፋኖ ታጣቂዎች በተሽከርካሪዎቹ ላይ ጥቃት ስለመፈፀማቸው እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
በወቅቱ በእጀባ ሲጓዙ የነበሩት ተሽከርካሪዎች በቁጥር እስከ 30 እንደሚደርሱ እና ከመካከላቸው ታማሚ የጫነ አምቡላንስ እና የሦስት ባንኮችን ገንዘብ ከእነ ኃላፊዎቹ የጫነ ተሽከርካሪ ይገኝበት እንደነበር ተናግረዋል።
በጥቃቱ አምቡላንሱ ውስጥ የነበሩ በዕድሜ ጠና ያሉ ታማሚ እና አብራቸው የነበረች የሕክምና ባለሙያ እንዲሁም የሦስቱ ባንኮች ኃላፊዎች መገደላቸውን እንዳረጋገጡ ገልፀዋል። የባንኮቹ ገንዘብ በታጣቂዎቹ መዘረፉን፣ አምቡላንሱም መቃጠሉን የሚገልፁት ግለሰቡ፣ ሌሎች ሲቪሎችም መገደላቸውን ተናግረዋል።
"ወንድማችን የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የጊዳ አያና ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ነበር። በመከላከያ ሠራዊት እጀባ የባንኩን ገንዘብ ይዞ ወደ ነቀምቴ እየሔደ ነበር። በመንገድ ላይ እንዳለ በተፈፀመበት ጥቃት መገደሉን በድንገት ሰማን" ሲሉ የሟቹ ወንድም ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግረዋልገ።
በጥቃቱ የተገደሉት የባንኩ የቅርንጫፍ ኃላፊ ማሙሽ ማሩ እንደሚባሉ የገለፁት መንድማቸው፣ የአራት ልጆች አባት እንደነበሩም ተናግረዋል።
አቶ ካፋሎ ነጋሳ ደያስ የተባሉ የቀርሳ ሀርቡካኔ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደርም በዚሁ ጥቃት መገደላቸውን የቤተሰብ አባላት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የተመሳሳይ ቀበሌ ነዋሪ የነበረ ጫላ ናጋሳ የተባለ ባለፈው ዓመት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ወጣት ልጅም የጥቃቱ ሰለባ መሆኑን ቤተሰቦቹ ገልፀዋል።
በአምቡላንስ ወደ ነቀምት ስትጓዝ የነበረች ልኪቱ አማኑ የተባለች አዋላጅ ነርስ እንዲሁም ሌላ በአምቡላንስ ውስጥ የነበሩ እና ወደ ነቀምቴ ሆስፒታል ለተሻለ ህክምና ሲጓዙ የነበሩ አቶ አማኑ ሂርጳ የተባሉ ታማሚ ከሟቾቹ መካከል መሆናቸውንም ቢቢሲ ከምንጮቹ አረጋግጧል።
በወቅቱ ሟቾቹን ወደ ትውልድ ቀያቸው ወስዶ መቅበር አዳጋች እንደነበረም ምንጮች ገልፀዋል።
በጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉቴ ከተማ ብቻ "13 ቤት ለቅሶ ደርሻለሁ" ያሉን አስተያየታቸውን የሰጡን የአካባቢው ነዋሪ፣ ይሁን እንጂ ስለተገደሉት ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር አያውቁም።
ከተገደሉት በተጨማሪ ብዙ ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውንም እኚሁ ግለሰብ ተናግረዋል።
በተኩስ መሃል ተይዘው የነበሩ ተሳፋሪዎች፣ ራሳቸውን ለማዳን እግራቸው ወደመራቸው አቅጣጫ ሲሯሯጡ "የፋኖ ታጣቂዎች ወዳሉበት አቅጣጫ የሄዱት ታፍነው ተወሰዱ" ይላሉ። ቁጥራቸው እስከ 70 ሊደርስ አንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ታፍነው ከተወሰዱት ውስጥ ሦስቱ ዘመዶቻቸው መሆናቸውን ተናግረዋል። ታጋቾቹን ለመልቀቅ ታጣቂዎቹ ገንዘብ እየጠየቁ እንደሆነም አመልክተዋል።
ከታገቱት መካከል አንዷ "ትዳር ከመሠረተች ገና አንድ ሳምንቷ ነው።"
በጅማ መምህርት የሆነች የ3 ልጆች እናትም ወደ ቤተሰቧ በመመለስ ላይ እንዳለች ታፍና መወሰዷን ገልፀዋል።
ከታገቱት መካከል አምልጠው የተመለሱ ስለመኖራቸው ጠቅሰው አብዛኞቹ ግን የት እንደደረሱ አይታወቅም ብለዋል።
እርሳቸውን ጨምሮ በጥቃቱ በርካታ ሰዎች ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም ገልፀዋል።
ሌሎች ያናገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም በፋኖ ታጣቂዎች በተፈፀመው ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን፣ የታገቱ መኖራቸውን እና የተወሰኑ ተሽከርካሪዎች ቃጠሎ እና ሌላ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
ይህን ጥቃት ተከትሎ ሲቪሎች የተጎዱበት "አፀፋዊ እርምጃ" በስፋት መፈፀሙን ገልፀዋል።
"የአፀፋ ጥቃት"፡ ካህኑን "ከቤተክርስቲያን ወስደው የገደሏቸው"
በጊዳ አያና ወረዳ የክልሉ መንግሥት ኃይሎች እርምጃ መውሰድ የጀመሩት ከነሐሴ 2/2018 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ ከተጎጂዎች መካከል የሆኑ አራት የወረዳው ነዋሪዎች ይገልፃሉ። ከነሐሴ 12 ወዲህ ደግሞ "ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ተጀመረ" ይላሉ አስተያየት ሰጪዎቹ።
ፋኖ ነሐሴ 13 ከፈፀመው ጥቃት በኋላ ደግሞ፣ ሲቪሎችን ዒላማ ያደረገ "አፀፋዊ" እርምጃ በብዛት መቀጠሉን አመልክተዋል።
"ግጭቶች ከተጀመሩ አንድ ወር አካባቢ ይሆናል። ንፁሃንን ዒላማ ማደረግ የተጀመረው ግን ከ5 ቀን ወዲህ ነው" ነሐሴ 21 ያናገርነው የመንደር 22 ነዋሪ የተናገረው ነው።
"የተገደሉትን በቁጥር ለመግለፅ ይከብዳል። በርካታ ናቸው። ካኅናት፣ ሕጻናት እና አቅመ ደካሞች ተገድለዋል" የሚሉት ግለሰቡ፣ ከተገደሉት መካከል የቅርብ ዘመዳቸው የሆኑ ካህን እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ካህኑ ቆሞስ አቡሀይ ታደሰ መኮንን እንደሚባሉ እና የኦሮሚያ ክልል መለዮ የለበሱ ታጣቂዎች ልብሳቸውን አስወልቀው ሲያንገላቷቸው የሚያሳየው ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ በሰፊው ሲዘዋወር የነበረው ቪዲዮ የእርሳቸው መሆኑን አስረድተዋል።
በጊዳ አያና ወረዳ አንዶዴ ዲቾ ቀበሌ የምትገኘው ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሥራ አስኪያጅ ነበሩ ያሏቸው ቆሞስ አቡሀይ ታደሰ፣ ነሐሴ 15/2018 ዓ.ም. ዓርብ መገደላቸውን "የሥጋ ዘመዴ ናቸው" ያሉን ግለሰብ ተናግረዋል።
"ከቤተክርስቲያን በአገልግሎት ላይ ከነበሩበት ነው ይዘው የወሰዷቸው። ከዚያን ጫካ ወስደው አሰቃይተው ነው የገደሏቸው" ብለዋል።
በቀበሌው በምትገኝ 'ፈንደቃ' የምትባል መንደር "ቤቶች መቃጠል ሲጀምሩ ሰው በፍራቻ ሸሽቶ ነበር" የሚሉት ግለሰቡ፣ ካህኑ ግን የሃይማኖት አባት እንደመሆናቸው "ምንም አያደርጉኝም" ብለው በማሰብ ቤተክርስቲያኑንም ትተው ላለመሔድ መቅረታቸውን አብራርተዋል።
ካህኑ ዓርብ ተገድለው በአምስተኛው ቀን ማክሰኞ ዕለት መቀበራቸውን ገልፀዋል። "የፀጥታ ኃይሎች ቦታውን ለቀው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ አስከሬናቸው ከጫካ ውስጥ ተፈልጎ ነው የተቀበረው" ያሉ ሲሆን፣ ሌሎች ሟቾችም በተመሳሳይ ቀን ተቀብረዋል ሲሉ አክለዋል።
ሌላ የካህኑ የቅርብ ዘመድ የሆኑ ቄስ አዲስ የሚባሉ የሃይማኖት አባትም አገልግሎት ለመስጠት ወደ ቤተክርስቲያን በሚሄዱበት ሰዓት ተይዘው እንደተገደሉ ተናግረዋል።
በቤተክርስቲያኒቱ ደጅ በልመና ይተዳደሩ የነበሩ እናት ደግሞ ከሕጻን ልጃቸው ጋር እንዳሉ መገደላቸውን ያነሱት የተናገሩ ነዋሪ፣ ከአራት ቀናት በላይ "አስከሬናቸው ሳይነሳ ቆይቷል" ብለዋል።
እናት በልጇ ፊት መገደላቸውን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ፎቶግራፎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች በስፋት ተዘዋውረዋል። እናቲቱ ነፍሰጡር እንደነበሩ የተናገሩት እማኙ፣ አብራቸው የነበረችው ሕጻን ሁለተኛ ልጃቸው መሆኗን እና በሕይወት ተርፋ ዘመድ እንደወሰዳት አስረድተዋል።
ጥቃቱን እየፈፀሙ ያሉት "ገዳ ኮማንዶ፣ በቅርቡ ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት የፈፀመ በአካባቢው ይንቀሳቀስ የነበረ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቡድን ታጣቂዎች እና የሚሊሻ አባላት ናቸው" የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ በሂደቱ የሚሳተፉ ሌሎች አካላትም እንዳሉ አክለዋል።
"በጣም ከባድ ሁኔታ እያሳለፍን ነው" ይላሉ በአሁኑ ወቅት እየተጋፈጡት ያሉትን ፈተና ሲገልፁ። እርሳቸውን ጨምሮ የብዙ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች በእሳት መውደማቸውን፣ አንስሳት እና ሌሎች ንብረቶቻቸውም መዘረፋቸውን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት "በየአቅጣጫው ከአካባቢው ሸሽተን በጫካ፣ ሰዎች ጋር ተጠግተን እና በቤተክርስቲያናት ተጠልለን ነው ያለነው" ብለዋል።
ጥቃት የተፈፀመባቸው መንደሮች በርካታ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በዋናነትም በአንዶዴ ዲቾ እና በቱሉ ሌንጫ ቀበሌዎች የሚገኙ ብዙ መንደሮች በአብዛኛው መውደማቸውን እና ዋና ከተማዋን አንገር ጉቴ (ጉትንን) ጨምሮ በከተሞች ያሉ መጋዘኖች እና የንግድ ቤቶች ዘረፋ እና ቃጠሎ እንደተፈፀመባቸውም ገልፀዋል።
የአንገር ጉቴ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ የእህል ክምችት ያለበት መጋዘናቸው እንደተቃጠለባቸው አመልክተዋል።
"አሁንም ጥቃቱ እንደቀጠለ ነው" የሚሉት የአካባቢው ነዋሪ፣ "የደረሰልንም የጠየቀንም አካል የለም" ብለዋል።
"መሔጃም የለንም፤ እርዳታም የለም፤ ሁላችንም ተፈናቃዮች በችግር ላይ ነን" ያሉን ደግሞ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው።
የቱሉ ሌንጫ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ በዕድሜ ጠና ያሉ ግለሰብ ደግሞ፣ "በገዳ ኮማንዶ የተመራ ኃይል" በቀበሌው በሚገኙ መንደሮች ላይ እርምጃ መውሰድ የጀመረው ከነሐሴ 16 ጀምሮ መሆኑን ገልፀዋል።
መንደር 3፣ መንደር 22 እና በጭበጭ በሚባሉ መንደሮች ውስጥ ሰኞ ነሐሴ 18 እና በቀጣዩ ቀን በተፈፀሙ ጥቃቶች በርካታ ሲቪሎች መገደላቸውን እና መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን እንዲሁም ዘረፋ መፈፀሙን አመልክተዋል።
ከተገደሉት መካከል በሚካኤል ቤተክርስቲያን ተጠልለው የነበሩ በትንሹ 20 ሰዎች እንደሚገኙበት ለቢቢሲ ተናግረዋል። ሌሎች ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎችም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።
በአካባቢው ያለው የፀጥታ ኃይሎች እንቅስቃሴ ጋብ ሲል በ3ኛው ቀን ተደብቀው የሔዱ ሰዎች "20 አስከሬን ቀብረው ተመልሰዋል" ያሉ ሲሆን፣ የጠፉም መኖራቸውን ተናግረዋል። ጥቃቱ የተፈፀመበት "ግንድአንሳ ሚካኤል ቤተክርስቲያንም ተቃጥሏል" ብለዋል።
ከተገደሉት ሲቪሎች መካከል ዘመዶቼ ይገኛሉ ያሉት እኚህ ግለሰብ፣ አካባቢያቸውን ጥለው ማምለጥ ያልቻሉ አቅመ-ደካማ ሲቪሎች ዋነኛ ሰለባዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሁኔታውን "መአት ነው ወረደብን" ሲሉ የገለፁት የመንደር 3 ነዋሪው፣ የሦስቱ መንደሮች ነዋሪዎች ጥቃቱ ሲጀመር ቱሉ ገና ወደምትባል ቀበሌ ሸሽተው መሔዳቸውን ጠቅሰዋል።
ዋናው ጥቃት ከመፈፀሙ ከሁለት ቀን ፊት "በ16 ቅዳሜ የመንግሥት ኃይሎች መጥተው መተኮስ ጀመሩ፤ እነሱ [የፋኖ ታጣቂዎች] ቀድመው መንደሮቹን ጥለው ሄደዋል" ብለዋል።
በወቅቱ "10 ሽማግሌዎች በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የመከላከያ ካምፕ ሔደን እንዲታደጉን አመልክተን ነበር። ከዚያ ስንመለስ ሚሊሻዎች አሰሩን። ከስድስት ሰዓት የእስር ቆይታ በኋላ የመከላከያ ኮሎኔል መጥቶ ሁኔታውን አስረድተነው ተለቀቅን" ሲሉ አክለዋል።
"ፋኖን ትደግፋላችሁ፤ እዚህ ነው ሚደበቁት እናንተ ናችሁ ምትመግቧቸው" በሚል ነው ጥቃት የተፈፀመው የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ በአካባቢው የፋኖ እንቅስቃሴ መኖሩን ግን አልሸሸጉም። ነገር ግን የመንግሥት ኃይሎች ጥቃት ከመፈፀማቸው በፊት ከስፍራው ለቀው ወጥተው ነበር ይላሉ።
ቦታው "የበረሃ ፋኖዎች የሚንቀሳቀሱበት መስመር ነው፤ ይህ ሃቅ ነው! በፊትም ከሩቅ እየመጡ እነዚህን መንደሮች ማረፊያ ያደርጋሉ" ካሉ በኋላ "ሕዝቡ ሂዱልን፤ እኛን እንዳታስገድሉን" ብሎ ሲማጸናቸው እንደነበር ጠቅሰው፣ "የታጠቁ ናቸው፤ የታጠቀን ኃይል ማን ያግደዋል? ማን ይከለክለዋል? የፈለጉትን ነው የሚያደርጉት" ሲሉ ያስረዳሉ።
በጥቃቶቹ ስለተገደሉት ሰዎች እንዲሁም ስለተቃጠሉት ቤቶች ትክክለኛ ቁጥር እንደማያውቁ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት ጥቃቱ የተፈፀመባቸው መንደሮች ሰው አልባ እንደሆኑም ነው የተናገሩት።
የነዋሪዎቹ ቀጣይ ስጋት
"ተዋደው ተጋብተው እየኖሩ ያሉ ማኅበረሰቦች አብሮ የመኖር ሁኔታ በፖለቲካ ምክንያት እተሸረሸረ ነው" ይላሉ፣ ካናገርናቸው የጊዳ አያና ነዋሪዎች መካከል አንዱ።
በአካባቢው ባሉት ግጭቶች እና የሲቪሎች ግድያዎች ምክንያት፣ ፖለቲካ በማያውቀው አርሶ አደር ማኅበረሰብ ዘንድ "መተማመን እየቀነሰ" መምጣቱን ጠቅሰው "ሕዝብ እንዲጨካከን እየተደረገ ነው" ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል። በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እንኳን በስጋት ምክንያት እንደከዚህ ቀደሙ ወደ ከተሞች መሸሽ መተዋቸውንም ነው ያስረዱት።
አሁን ያለው ሁኔታ "እጅግ በጣም አስፈሪ ነው" ያሉን ሌላ ግለሰብ፣ የታጠቁት ኃይሎች የሚያደርጉት ግጭት በቀጠለ ቁጥር የሲቪሉ ሕይወት ይበልጥ አደጋ ላይ እየወደቀ ይሄዳል የሚል ስጋት አላቸው።
ተፈናቃዮች ወደ መንደራቸው ለመመለስ የደኅንነት ስጋት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
ወደ ቀያቸው ተመልሰው የመኖር ድፍረት እንደሌላቸው ብዙዎቹ ያናገርናቸው ተጎጂዎች ይገልጻሉ። በመሆኑም መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል።
"ተፈናቅለው ጫካ ያሉ ሰዎች ምንም አይነት የምግብ እና የመድኃኒት አቅርቦት የላቸውም። የትኛውም ዓይነት ሰብዓዊ ድርጅት እየደረሰልን አይደለም" ከተፈናቃዮች መካከል የሆኑ ግለሰብ ያሉት ነው።
አርሶ አደሩ በዚህ የክረምት ወቅት እርሻውን ተንከባክቦ ዘር መሰብሰብ ካልቻለ ከፊት ለፊቱ ሌላ የከፋ ችግር እንደሚጠብቀውም ይገልፃሉ።
ይሁን እና ወደ እርሻቸው ተመልሰው ለመሥራት ዋስትና እንደሌላቸው ተፈናቃዮቹ ተናግረዋል።
ከነስጋታቸው እንመለስ ቢሉ እንኳን፣ ቤት ንብረታቸውን ያጡ "በርካታ ተፈናቃዮች ማረፊያ አይኖራቸውም" ይላሉ ብዙ ቤቶች መቃጠላቸውን የተናገሩ አስተያየት ሰጭ።
"እርምጃ በፋኖ እና በሸኔ ላይ"
በምሥራቅ ወለጋ ጊዳ አያና ወረዳ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ቢቢሲ ከመንግሥት አካላት እና ከፋኖ ታጣቂዎች አስተያየት ለማግኘት ከሳምንት በላይ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ከወረዳው ጀምሮ እስከ ኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ያሉ ባለሥልጣናት ለስልክ ጥሪ እና ለፅሁፍ ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም። ከመከላከያ ሠራዊትም አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
ሆኖም የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች የፋኖ ታጣቂዎችን ዒላማ ያደረገ ወታደራዊ እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን የምሥራቅ ወለጋ ዞን ፖሊስ አስታውቋል።
የዞኑ ፖሊስ፣ የፋኖ ጥቃት ከመፈፀሙ አንድ ቀን ቀደም ብሎ "ሕዝቡ በሁለት ታጣቂዎች፡ በሸኔ (የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት) እና በፋኖ ፅንፈኞች በሚፈፀሙበት ጥቃቶች ለተለያዩ ጉዳቶች ተጋልጧል" ሲል በፌስቡክ ገጹ ላይ አስታውቋል።
የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች "በፋኖ ፅንፈኛች ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን" የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ቦጃ ባልቻ መግለጻቸውም በዚሁ የፌስቡክ ልጥፍ ተጠቅሷል።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በሚል ስያሜ የተደራጀው የፋኖ አማጺ ቡድን፣ በወለጋ የሚንቀሳቀስ የፋኖ አደረጃጀት መመሥረቱን በቅርቡ ገልጿል። የወለጋ ፋኖ ነሐሴ 13 በጊዳ አያና ጥቃት መፈፀሙንም በማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች የገለፁት የታጣቂ ቡድኑ አመራሮች፣ ዒላማቸው የመንግሥት አካላት እንደሆኑ ነው የሚናገሩት።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)፣ በምሥራቅ ወለጋ ጊዳ አያና የተፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ክትትል እያደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል። ይሁን እንጂ በአካባቢው ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ የተነሳ እስካሁን የተሟላ መረጃ ማግኘት እንዳልቻለ አስታውቋል።
ከመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስተያየት ለማግነት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ፣ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በንጹኃን ዜጎች ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶችና የተከሰቱት ተደጋጋሚ ሰብዓዊ ቀውሶች "የመንግሥትን መሠረታዊ የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ውድቀት እንደገና በግልጽ ያሳዩ" ናቸው ብሏል።
ይህም "በጥልቅ" እንደሚያሳስበው አብን ገልጿል።
በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ፣ እና በሌሎች የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በንጹኃን ዜጎች ላይ የተፈጸሙት "የማንነትና ዕምነት ተኮር" ጥቃቶች፣ "የአገራችንን ሰላም እና ማኅበራዊ አንድነት በእጅጉ እየጎዱ ይገኛሉ" ሲል ስጋቱን ገልጿል።
የዜጎችን ደኅንነት የማረጋገጥ ቀዳሚና የመጀመሪያው ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑን በማስታወስ፣"ጥቃቶችን በታጣቂዎች ላይ ብቻ በማሳበብ መንግሥት ከተጠያቂነት ነፃ ሊሆን አይችልም!" በማለት መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል።
በጥቃቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ፣ ንብረታቸው ለወደመባቸው እና የነፍስ አድን እርዳታ ለሚሹ ዜጎች በአስቸኳይ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው፣ እንዲሁም ወደ ቀደመ ቀያቸው ተመልሰው በዘላቂነት እንዲቋቋሙም ጥሪ አቅርቧል።