የጋና ፓርላማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርግ ሕግ አጸደቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የጋና ፓርላማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን እና ተግባራቱን የሚያስተዋውቅ የትኛውንም እንቅስቃሴ ወንጀል የሚያደርግ ሕግ አጸደቀ።
በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ውስጥ ተሳትፎ የሚገኝ ማንኛውም ግለሰብ በሦስት ዓመት እስራት እንደሚቀጣ ሕጉ ይደነግጋል።
አዲስ የጸደቀው ሕግ በተጨማሪም በዚህ የተከለከለ ተግባር ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎችን የሚያውቅ ግለሰብ ለፖሊስ የመጠቆም ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።
ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ የሃይማኖት አባቶች የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ላይ ያሉ ሕጎችን እንዲያጠብቁ ጫና ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ሕጉን እንደ ሂውማን ራይትስ ዎች ያሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አጥብቀው የተቹት ሲሆን የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ሕይወትን አደጋ ላይ ይጥላል እንዲሁም "ዜጎች እርስ በእርስ እንዲሰላለሉ እና እንዲወነጃጀሉ ያደርጋል" ብለዋል።
በጋና የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ከብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ጀምሮ የተከለከለ ነው።
ሕጉን ያረቀቁት መጋቢ ጆን ንቲም ፎርዦር ለምክር ቤቱ ሕጉ የጋና ቤተሰብ እና ባህላዊ እሴቶች እከላከላል ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም አዲሱ ክልከላ ከዚህ ቀደም የነበሩ ሕጎችን "የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ለመከላከል የበለጠ ጠንካራ ፣ የበለጠ አካታች፣ የበለጠ ጥብቅ ያደርጋል" ብለዋል።
ማንኛውም የተመሳሳይ ጾታን የሚደግፍ ወይም የሚያግዝ አካል እስር ሊጠብቀው እንደሚችልም ተነግሯል።
በሕጉ ላይ ለተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን የተሌያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የሕግ፣ የመገናኛ ብዙኃን እና የጤና ባለሙያዎች እንዳይካተቱ ተደርገዋል።
ሂውማን ራይትስ ዎች በጋና አክራ ለሚገኘው የፓርላማው የሕገ መንግሥት እና ሕግ ጉዳዮች ኮሚቴ ሕጉን ዳግም እንዲመለከቱት ጥያቄ አቅርቦ ውድቅ እንዲሆን ጠይቋል።
ጋና እአአ በ2024 ተመሳሳይ ህግ ብታወጣም የወቅቱ ፕሬዚዳንት አኩፎ አዶ ሳያጸድቁት በመቅረታቸው ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል።
ፕሬዚዳንት ማሃማ ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ ሕጉ እንዲጸድቅ እንደሚፈልጉ ተናግረው "ሁለት ጾታዎች ወንድ እና ሴት ብቻ በሚለው መርህ እና እሴት አምናለሁ። እና ጋብቻ በወንድ እና በሴት መካከል ብቻ ነው" ብለው ነበር።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የአፍሪካ አገራት በተመሰሳይ ጾታ አፍቃርያን ላይ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።
የሴኔጋል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጋቢት ወር ተመሳሳይ ሕግ ያጸደቀ ሲሆን የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ጥንዶች ወሲብ ሲፈጽሙ ቢያዙ እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጡ ደንግጓል። በተጨማሪም የተመሳሳይ ጾታ ተግባራትን "በሚያስተዋውቁ" ተግባራት ላይ ተሳትፎ መገኘትም ወንጀል ሆኗል።
ኡጋንዳ እአአ በ2023 የተወሰነ የተመሳሳይ ጾታ ተግባር ላይ የሞት ቅጣት ደንግጋለች።















