ትራምፕ አገራቸው ከካናዳ ጋር የምትጋራውን ኦንታሪዮ ሐይቅ ስያሜ የሚቀይር ውሳኔ አሳለፉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ከካናዳ ጋር የምትጋራውን 'ኦንታሪዮ' እየተባለ ይጠራ የነበረውን ሐይቅ በአሜሪካ ስም የሚቀይር ፕሬዚዳንታዊ ውሳኔ አስተላለፉ።

ትራምፕ ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት በአሜሪካ እና በካናዳ መካከል የሚደረገው የንግድ ድርድር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ሳይሳካ ከቀረ በኋላ ነው።

የኦንታሪዮ ሐይቅ በካናዳዋ ኦንታሪዮ እና የአሜሪካዋ ኒውዮርክ ግዛት ድንበር ላይ የሚገንኝ የውሃ አካል ነው።

በካናዳ እና በአሜሪካ መካከል ሲካሄድ የቆየው የንግድ ድርድር መፍረስን ተከትሎ ትራምፕ ከካናዳ በሚገቡ 20 ቢሊዮን ዶላር በሚያወጡ ምርቶች ላይ የ50 በመቶ ቀረጥ ሲጥሉ ካናዳም ተመሳሳይ የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች።

ትራምፕ በንግድ ቀረጦች ላይ ሁለቱ አገራት አለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ በተደጋጋሚ የሐይቁን ስም ለመቀየር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ሲዝቱ ነበረ።

ሐሙስ ዕለት ውሳኔው "ይፋዊ እና ወዲያውኑ ተፈጻሚ የሚሆን" እንደሆነ አስታውቀው አስተዳደራቸው ስሙን ለመቀየር የሚያስችሉ "አስፈላጊውን የወረቀት ሰነዶች ሞልቷል" ብለዋል።

የፕሬዚዳንቱ ልዩ ትዕዛዝ የአሜሪካ አገር ውስጥ መሥሪያ ቤት የሐይቁን ስም በ30 ቀናት ውስጥ እንዲለውጥ ያስችለዋል።

የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ የኦንታሪዮ ሐይቅ ከ400 ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው መሆኑን እና የካናዳ ኮንፈዴሬሽን እና የአሜሪካ የነጻነት አዋጅን እንደሚቀድም በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ጽፈዋል።

"ዩናይትድ ስቴትስ እየለወጠችው መሆኑን እናውቃለን። የንግድ ግንኙነታቸውን፣ የውጪ ፖሊሲያቸውን፣ ብሔራዊ ሐውልቶቻቸውን፣ የውሃ አካሎቻቸውን [እየለወጡ ነው]" ሲሉ ጽፈው "የካናዳ ዜጎችም ነገሮች በስማቸው መጠራት አንዳለባቸው ያውቃሉ። እናም ይህ ሐይቅ ዛሬም ወደፊትም ኦንታሪዮ እየተባለ እየተጠራ ይቀጥላል" ብለዋል።

ትራምፕ እአአ በ2025 ወደ ዋይት ሐውስ ተመልሰው ሥልጣናቸውን ዳግም ሲቆናጠጡ 'የሜክሲኮ ባህረ ሰላጤ በመባል የሚታወቀውን ክፍል 'የአሜሪካ ባህረ ሰላጤ' ብለው መቀየራቸው ይታወሳል።

ሜክሲኮ የስም ለውጡን ውድቅ አድርጋ የዓለም አቀፍ ውሃ አካልን አንድ አገር ተነስቶ ስሙን መቀየር አይችልም ብላ ነበር።

ይህ ውሳኔ በሜክሲኮ እና በካርታ መተገበሪየዎች ላይ ስሙን በቀየረው የቴክኖሎጂ ኩባንያ፣ ጉግል መካከል የሕግ ክርክር አስነስቷል።

በዚህም የተነሳ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የጉግል ማፕ ተጠቃሚዎች "የአሜሪካ ባሕረ ሰላጤ" የሚለውን ሲመለከቱ በሜክሲኮ ወገን ያሉ ደግሞ "የሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ" የሚለው ይታያቸዋል።

በሌላ አገራት የሚገኙ የመተግበሪያው ተጠቃሚዎችም "የሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ (የአሜሪካ ባሕረ ሰላጤ)" የሚለውን መመልከት ይችላሉ።

በወቅቱ ዋይት ሐውስ የፈረንሳዩ የዜና ወኪል "የአሜሪካ ባሕረ ሰላጤ" የሚለውን በዘገባው ላይ ሽፋን ባለመስጠቱ ከፕሬዚዳንታዊ መግለጫዎች ላይ አግዶት ነበር።

ኤፒ በምላሹ የትራምፕ አስተዳደርን ፍርድ ቤት ከስሶ ጉዳዩ እየታየ ይገኛል።

ለዓለም አቀፍ ውሃ አካሎች ስም የሚሰጥ ወይንም የሚያጸድቅ እውቅና ያለው ዓለም አቀፍ አካል የለም።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አገራቸው በይፋ አንዳንድ ታዋቂ መጠሪያዎችን እንዴት እንደምትጠራ ሰፊ ውሳኔ ቢያሳልፉም ሌሎች አገሮች ግን ያንን መከተል አልፈለጉም።

ካናዳ በሌሎች አገሮች የተደረጉ የስም ለውጦችን እውቅና መስጠት የሌለባት ሲሆን ባለሥልጣናትም ሀሳቡን ውድቅ አድርገውታል።

የኦንታሪዮ አስተዳዳሪ ዳግ ፎርድ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "ለካናዳውያን እና ለተቀረው ዓለም የኦንታሪዮ ሐይቅ ነው። አሁን እና ለዘላለም" ሲሉ ጽፈዋል።

የኖቫ ስኮሺያ አስተዳዳሪ ቲም ሂዩስተን ደግሞ "አሁን ወደ ሞኝነት ዘልቀን ገብተናል። ወዳጄ የኦንታሪዮ ሐይቅ" ሲሉ ተናግረዋል።

"ሁልጊዜም ሐይቁን ኦንታሪዮ ብለን እንጠራዋለን" ያሉት ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ ናቸው።

በካናዳ እና አሜሪካ የሚገኙ የአራቱ ታላላቅ ሐይቆች ስሞች ኦንታሪዮ፣ ሁሮን፣ ሚቺጋን እና ኤሪ ስያሜዎች የተገኙት ከአገሬው ነባር ሕዝቦች ቋንቋ ውስጥ በተወሰዱ ቃላት ነው።

ሱፐርኢየር ሐይቅ የተሰየመው በእንግሊዝኛ ቋንቋ በተጻፈ የፈረንሳይኛ ቃል ነው።

ከታላላቅ ሐይቆች ውስጥ ትንሹ የሆነው የኦንታሪዮ ሐይቅ በካናዳ እና በአሜሪካ ከኒውዮርክ ግዛት ጋር ይዋሰናል።