ካናዳ በአሜሪካ ምርቶች ላይ የ50 በመቶ የአጸፋ ታሪፍ ጣለች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ካናዳ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአገሪቱ ምርቶች ላይ በጣሉት ከፍተኛ ታሪፍ የተነሳ በተለያዩ የአሜሪካ ምርቶች ላይ እስከ 50 በመቶ የሚደርስ የአጸፋ ታሪፍ መጣሏን አስታወቀች።

ካናዳ ታሪፍ የጣለችባቸው የአሜሪካ ምርቶች ብረት፣ የቤት ዕቃዎች፣ ቱና እና ከጥጥ የሚመረቱ ቲሸርቶችን ያካትታል ተብሏል።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት አክለውም ወደ 28 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ዋጋ ባላቸው ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ማክሰኞ ዕለት አስታውቀዋል።

ታሪፍ የተጣለባቸው ዕቃዎች ዝርዝር አሜሪካ በካናዳ ምርቶች ላይ ከጣለችው ጋር እንዲጣጣም መደረጉ ተገልጿል።

ካናዳ የጣለችው ታሪፍ ከጳጉሜ 3/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።

አሜሪካ እና ካናዳ ባለፈው ሳምንት ለማድረግ አቅደውት የነበረው ድርድር ሳይሳካ ከቀረ በኋላ አንዳቸው ሌላኛቸውን በመጨረሻው ሰዓት ምክንያታዊ ያልሆነ መደራደሪያ በማቅረብ ወንጅለው ወደ ታሪፍ መጣል ተሸጋግረዋል።

የፋይናንስ ሚኒስትር ፍራንሷ ፊሊፕ ሻምፓኝ እንዳሉት የካናዳ የአጸፋ እርምጃ የትራምፕ አስተዳደር የንግድ ድርድሩ ከተቋረጠ በኋላ በተለያዩ የካናዳ ሸቀጦች ላይ ለጣለው 50 በመቶ ታሪፍ የተሰጠ ምላሽ ነው።

"እነዚህ ታሪፎች በአገራችን ውስጥ ላሉ ሠራተኞች፣ ንግዶች እና ማኅበረሰቦች ተጨባጭ መዘዝ ያስከትላሉ" ብለዋል።

"ካናዳ ምላሽ መስጠት አለባት።"

ሻምፓኝ የካናዳን የአጸፋ እርምጃ "ተመጣጣኝ" እና "ስትራቴጂካዊ" ሲሉ ገልጸውታል።

ካናዳ በተጨማሪም በአሜሪካ ታሪፍ ምክንያት ጉዳት ለሚደርስባቸው የንግድ ድርጅቶችና ሠራተኞች የሥራ ኪሳራን ለመቀነስና ኩባንያዎችን ለማንቀሳቀስ ተጨማሪ 7.5 ቢሊዮን የካናዳ ዶላር ድጋፍ እንደምታቀርብ አክለዋል።

በታሪክ በዓለም ላይ በጣም ቅርብ በሆኑት የንግድ አጋሮች መካከል በንግድ ላይ የሚጣል ግብር በሁለቱም አገራት መካከል ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ምንም ጥርጥር የለውም።

ባለፉት አስርት ዓመታት የተገነቡት የአቅርቦት ሰንሰለቶች በአሜሪካ እና ካናዳ በተቀመጡ የታሪፍ ማሻሻያዎች ምክንያት የግብይት ወጪዎችን እንደሚጨምሩ ይጠበቃል።

በሁለቱም ወገን ያሉ ንግዶችን እና ሸማቾችን በከፍተኛ ዋጋ ጭማሪ እንደሚጎዱ ይጠበቃል።

አብዛኛዎቹ ካናዳውያን መንግሥታቸው በአሜሪካ ላይ የአጸፋ እርምጃ እንዲወስድ እንደሚደግፉ የሕዝብ አስተያየት መስጫዎች ያሳያሉ።

ነገር ግን የንግድ ድርድሩ ለምን ሳይሳካ እንደቀረ የሚጠይቁ የኅብረተሰብ ክፍሎችም አሉ።

ወግ አጥባቂ ተቃዋሚዎች ከአሜሪካ ጋር የተደረገው የረቂቅ ስምምነት ሰነድ ይፋ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የንግድ ድርጅቶችም ከካናዳ ትልቁ የንግድ አጋር ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀው የንግድ ጦርነት ስለሚያስከትለው ተጽእኖ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ዋይት ሐውስ ካናዳ የአጸፋ ታሪፍ እርምጃዋን ይፋ ካደረገች በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ አሜሪካ በቅርቡ በተደረጉ የንግድ ውይይቶች ለካናዳ "በምድር ላይ ካሉ ከማንኛውም አገራት የላቀ የገበያ መዳረሻ" ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗን ገልጿል።

"ካናዳ ከአጋርነት ይልቅ ምክንያታዊ ያልሆኑ ጥያቄዎችን፣ ወደኋላ መመለስን እና ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረግን መርጣለች" ሲል ወንጅሏታል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ አርብ ዕለት አገራቸው ከአሜሪካ ጋር ስታደርገው የነበረው ድርድር ከተቋረጠ በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ የጣለችው አዲስ የታሪፍ ናዳ ካናዳን "ለመጉዳት እና ለመከፋፈል" የተነደፈ "የተሳሳተ ስሌት" መሆኑን ተናግረዋል።

ትራምፕ በድርድሩ ከካናዳ ብዙ መጠየቃቸውን እና በእነርሱ በኩል ግን ትንሽ ማቅረባቸውን የተናገሩት ካርኒ፣ አሁን ላይ አሜሪካ እና ካናዳ በንግድ "ጦርነት" ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ጥቃት ሲሰነዘርባችሁ ጦርነት ውስጥ ትገባላችሁ፤ ጥቃት ተሰንዝሮብናል" ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ከጳጉሜ 3/2018 ዓ.ም. ጀምሮ በብረት፣ በወተት፣ በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እና በመሳሰሉት ከአገሪቱ በሚገቡ ምርቶች ላይ በአሜሪካ ታሪፍ ልክ ቀረጥ በመጣል ምላሽ እንደሚሰጡ ዝተው ነበር።