በናይጄሪያ ነዳጅ ለመስረቅ የሞከሩ ከ30 በላይ ሰዎች በመርዛማ ጭስ ታፍነው ሞቱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በናይጄሪያ ሪቨርስ ግዛት ቢያንስ 37 ሰዎች ከነዳጅ ቧንቧ ነዳጅ ለመስረቅ ሲሞክሩ በመርዛማ ጋዝ ጭስ ታፍነው መሞታቸውን በነዳጅ ሀብት በበለጸገው ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀስ አንድ የአካባቢ ጥበቃ ቡድን ገለጸ።

የወጣቶች እና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ማዕከል በመባል የሚታወቀው ቡድን እንደገለጸው፣ ከ100 በላይ ሰዎች በሌሊት ጨለማን ተገን አድርገው በትናንሽ ጀልባዎች በመሆን የተጣራ ነዳጅ ለመቅዳት ሲሞክሩ ነው ለአደጋ የተጋለጡት። ከሞቱት በተጨማሪ በርካታ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።

ፖሊስ ለቢቢሲ እንደገለጸው፣ ተጎጂዎቹ ምን ያህል እንደሆኑ ለማረጋገጥ ምርመራ በመካሄድ ላይ ነው። ከአካባቢው የወጡ ሪፖርቶች እንደሚሉት አንዳንዶቹ ሰዎች በጋዝ ጭስ ታፍነው ተዝለፍልፈው ወደ ቦኒ ወንዝ ውስጥ ሲወድቁ፣ ሌሎች ደግሞ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

ከነዳጅ ቧንቧዎች ላይ ስርቆት መፈጸም በናይጄሪያ የነዳጅ ማዕከላት አካባቢ ለብዙ አስርት ዓመታት የቆየ ክስተት ነው።

ሪቨርስ ግዛት በደቡባዊ ናይጄሪያ በሚገኘው ኒጀር ዴልታ ክልል ውስጥ ከሚካተቱ ግዛቶች መካከል አንዱ ነው። ይህ ሰፊ ረግረጋማ አካባቢዎች ያሉበት ክልል በናይጄሪያ የባሕር ጠረፍ ላይ ትልቅ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አለው።

ለብዙ ዓመታት ወንጀለኛ ቡድኖች የነዳጅ ቧንቧዎችን በመስበር ድፍድፍ ነዳጅ ወይም ሌሎች የነዳጅ ምርቶችን ወደ ጀልባዎች እና የማከማቻ በርሜሎች በመውሰድ በጥቁር ገበያ ይሸጣሉ ወይም ወደ ሕገወጥ ማጣሪያ ቦታዎች ይወሰዳሉ።

የወጣቶች እና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ማዕከሉ እንደገለጸው፣ በጎ ፈቃደኞቹ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት በኦክሪካ የሚኖሩ ሰዎች በአካባቢው "ኢንዶራማ ነዳጅ" ተብሎ በሚጠራው ጋዝ በመታፈናቸው ሕይወታቸውን አጥተዋል። ለሰዎቹ ሞት ምክንያት የሆነው ፒኤምኤስ (ፕሪሚየም ሞተር ስፒሪት) ተብሎ የሚታወቀው የተጣራ ቤንዚን ዓይነት ነው።

የናይጄሪያ የደኅንነት እና ሲቪል መከላከያ ቡድን በበኩሉ፣ ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመተባበር ሐሙስ ዕለት ለሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ክስተት በትክክል ምን እንደነበር ለማጣራት እየሠራ በመሆኑ፣ ሕዝቡ እና መገናኛ ብዙኃን የተረጋገጠ መረጃ ብቻ እንዲጠቀሙ አሳስቧል።

ተቋሙ የነዳጅ ቧንቧዎችን በሕገ ወጥ መንገድ በመስበር እና ነዳጅ መስረቅን በጥብቅ አውግዞ፣ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች የሰው ሕይወት፣ አካባቢ እና ኢኮኖሚን ለከፍተኛ አደጋ እንደሚዳርጉ አስጠንቅቋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ብዙ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ይህ ድርጊት ለብክለት እና ለአካባቢ ጉዳት መባባስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ።

የናይጄሪያ መንግሥት በቅርብ ዓመታት በነዳጅ ስርቆት ላይ የሚደረጉ እርምጃዎችን አጠናክሯል።

ሐሙስ ዕለት የአገሪቱ ባሕር ኃይል መረጃ ዳይሬክተር ካፒቴን አቢዮዱን ፎሎሩንሾ፣ በኒጀር ዴልታ የውሃ መስመሮች እና የባሕር ጠረፎችን ከሚጠብቀው የባሕር ኃይል "መሸሸግ የሚቻልበት ቦታ የለም" በማለት ለዘራፊዎች ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

"ቀናቸው ደርሷል፤ ከያዝናችሁ ደግሞ ከሕግ ፊት እናቀባችኋለን" ሲሉ ለናይጄሪያው የቴሌቪዥን ጣቢያ 'ቻናልስ ቲቪ' በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

የናይጄሪያ የባሕር ኃይል የባሕር ላይ ደኅንነት ጥበቃ ዘመቻዎችን እያጠናከረ ሲሆን፣ ወታደራዊ ኃይሎች እና ሌሎች የፀጥታ ተቋማት በአካባቢው በሚገኙ ጥብቅ ደኖች ውስጥ የሚደበቁ የነዳጅ ሌቦችን ለማስቆም ተከታታይ ዘመቻዎችን እያካሄዱ ነው።

ናይጄሪያ በነዳጅ ስርቆት፣ በፀጥታ ችግሮች እና ኢንቨስትመንት እጥረት ምክንያት ለዓመታት የተፈጠሩ ችግሮችን ከተጋፈጠች በኋላ የነዳጅ ምርትዋን ለማሳደግ እየሞከረች ነው።

አገሪቱ እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ድረስ የቀን የነዳጅ ምርቷን ወደ ሦስት ሚሊዮን በርሜል ለማሳደግ ያቀደች ሲሆን፣ አዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ እና ማሻሻያዎችን በማካሄድ ላይ ናት።