የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ለትራምፕ የስደተኞች ተቋማት 70 ቢሊዮን ዶላር ፈቀደ

የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስደተኞች ተቋማት 70 ቢሊዮን ዶላር እንዲሰጣቸው ፈቀደ።

የአሜሪካ የስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የድንበር ቁጥጥር ባለሥልጣን እና ሌሎችም በስደተኞች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ተቋማት ለቀጣይ ሦስት ዓመታት በዚህ ገንዘብ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ውሳኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ድምጽ ከተሰጠበት በኋላ ይሁንታ ካገኘ ትራምፕ ፊርማቸውን ያኖራሉ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔውን በመቃወም ከዴሞክራቶች ጎን የቆሙት አንድ ሪፐብሊካን የሕዝብ እንደራሴ ብቻ ስለሆኑ 52 ለ 47 የሆነ አብላጫ ድምጽ አግኝቷል።

ትራምፕ ያቀረቡት ሌላ አወዛጋቢ ሐሳብ በቀድሞው አስተዳደር "በደል ለደረሰባቸው ሰዎች" 1.8 ቢሊዮን ዶላር መመደብን የተመለከተ ሲሆን፤ ዴሞክራቶች ዕቅዱ ውድቅ እንዲሆን ሲከራከሩ ቆይተዋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቶድ ብላንቼ ባለፈው ሐሙስ ትራምፕ ያቀረቡት ዕቅድ ውድቅ እንደሚሆን ቢጠቁሙም ፕሬዝዳንቱ ግን "ሐሳቡ ገና አልሞተም፤ ጠበቆች መጠየቅ አለብኝ" ብለዋል።

የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የፈቀደው ወደ 72 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ትራምፕ ስደተኞች ላይ እየወሰዱ ያሉትን እርምጃ በዋነኛነት ለሚያስተገብሩት የአሜሪካ የስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲሁም የድንበር ቁጥጥር ባለሥልጣን ይሰጣል።

ዴሞክራቶች እነዚህን ተቋማት ለመደገፍ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል።

የአሜሪካ የስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኞች በሜኒሶታ ሁለት ሰዎችን በጥይት መግደሉን ተከትሎ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በከፊል ለተወሰነ ጊዜ ተዘግቶ እንደነበር ይታወሳል።

የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ለትራምፕ የስደተኞች ተቋማት 70 ቢሊዮን ዶላር የፈቀደው፤ ሕግ አውጪዎች በአብላጫ ድምጽ ከወጪ ጋር የተያያዘ ውሳኔ ማሳለፍ የሚችሉበትን አሠራር ተጠቅሞ ነው።

ተቃውሞ ያሰሙት ብቸኛው ሪፐብሊካን ሊሳ ሙኮስኪ ሲሆኑ አንድ ዴሞክራት ድምጽ አልሰጡም።

18 ሰዓት በወሰደው ውይይት ዴሞክራቶች ከስደተኞች ጉዳይ ጋር ያልተያያዙ ማሻሻያ ነጥቦችን ለማስገባት ሞክረዋል።

አብዛኞቹ ማሻሻያዎች ትራምፕ ካቀረቡት የ1.8 ቢሊዮን ዶላር ፈንድ ጋር የተያያዙ ናቸው።