ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ የንጉሡ ቻርልስ ጉብኝት ከዩኬ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማስተካከል እንደሚረዳ ለቢቢሲ ተናገሩ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ሳምንት ንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊ እና ንግሥት ካሚላ በአሜሪካ የሚያደርጉት ጉብኝት ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማስተካከል ሊረዳ እንደሚችል ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ የንጉሡ ጉብኝት ግንኙነቱን ለማስተካከል ሊረዳ ይችላል ወይ በሚል ከቢቢሲ በስልክ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ "በትክክል። እሱ ድንቅ ነው። የሚገርም ሰው ነው። ምላሼ አዎ የሚል ነው" ብለዋል።
"በደንብ አውቀዋለሁ፣ ለዓመታት አውቀዋለሁ። እሱ ደፋር እና ታላቅ ሰው ነው። [ግንኙነቱ] በእርግጥም አዎንታዊ ይሆናል" ሲሉ አክለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ጋር ስላላቸው ግንኙነትም ሲናገሩ፤ እሱ በስደተኞች ላይ ያለውን አካሄድ ከቀየረ ብቻ "መሻሻል" እንደሚችል ገልጸዋል።
ንጉሡ እና ንግሥቲቱ ሰኞ ዕለት ለአራት ቀናት ጉብኝት ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ሲሆን ከትራምፕ ጋር በዋይት ሐውስ ይገናኛሉ።
ንጉሡ ከፕሬዚዳንቱ ጋር የግል ውይእት የሚያደርጉ ሲሆን ለአገሪቱ ኮንግረስም ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል።
ለሁለት ቀናት በዋሽንግተን ዲሲ ከቆዩ በኋላ ወደ ኒውዮርክ፣ ቨርጂኒያ እና ቤርሙዳ ተጉዘው ወደ ዩኬ ይመለሳሉ።
የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዞው የአሜሪካን 250ኛ ዓመት የነፃነት በዓል በሚከበርበት ወቅት የሚካሄድ እና "የጋራ ብልጽግና፣ ደህንነት እና የታሪክ" አጋርነት የሚያሳይ መሆኑን አስታውቋል።
ሐሙስ ዕለት ከቢቢሲ ጋር በስልክ ለአምስት ደቂቃ በነበራቸው ቃለ ምልልስ ትራምፕ ከሰር ኪር ጋር ስላላቸው ግንኙነትም ተጠይቀዋል።
ሁለቱ መሪዎች በኢራን ጦርነት ምክንያት አለመግባባት ውስጥ ከመግባታቸውም ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሎርድ ማንዴልሰንን በአሜሪካ የዩኬ አምባሳደር አድርገው በመሾማቸው ከፍተኛ ጫና ገጥሟቸዋል።
ትራምፕ ሰኞ ዕለት በትሩዝ ሶሻል ላይ ባወጡት ጽሑፍ ሎርድ ማንዴልሰን "በጣም መጥፎ ምርጫ" እንደሆኑ ተናግረዋል።
በልጥፉ ምን ማለት እንደፈለጉ የተጠየቁት ትራምፕ "የሰሜን ባህርን ከከፈተ እና አሁን ጠንካራ ያልሆነውን የስደተኛ ፖሊሲ ጠንካራ ካደረገ፣ ሊያገግም ይችላል፣ ካልሆነ ግን ዕድሉ አለው ብዬ አላምንም" ሲሉ መልሰዋል።
ትራምፕ ዩናይትድ ኪንግደም በሰሜን ባህር የነዳጅ እና የጋዝ ምርቷን እንድታሳድግ በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
ሰር ኪር ሐሙስ ዕለት ስለፕሬዚዳንቱ አስተያየት ሲናገሩ "ውሳኔዎቼን የምሰጠው የብሪታንያን ብሔራዊ ጥቅም ከግምት በማስገባት እንጂ ሌሎች ሰዎች በሚሉት ወይም በሚያደርጉት ነገር አይደለም" ብለዋል።
"ለዚህም ነው በኢራን ጦርነት ውስጥ እንዳንሳተፍ የወሰንኩት። ሌላ ሰው በሚናገረው ነገር ምክንያት ከዚህ አቅጣጫ አልወጣም ወይም አልቀይርም።"
ትራምፕ የዩኬን መንግሥት እና ሌሎች አጋሮች ለኢራን ጦርነት የሰጡትን ምላሽ ተችተዋል። ከዩኬ ባገኙት ድጋፍ "ደስተኛ እንዳልሆኑ" ቢገልጹም፣ ሰር ኪር ደግሞ አገሪቱ ወደ ሰፊ ግጭት እንደማትገባ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንደ ዩኬ ያሉ አጋሮች ለምን እንዲሳተፉ እንደሚፈልጉ ሲጠየቁ "በፍጹም ባያስፈልጉንም ግን መገኘት ነበረባቸው። እኔ በግልጽ አያስፈልጉኝም ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።
"የኢራንን ወታደራዊ ኃይል አጥፍተናል። ስለዚህ ማንም አያስፈልገንም ነበር" ብለዋል።
"ተሳታፊ መሆን አለመሆናቸውን ማየት ፈልጌ ነበር" ያሉት ትራምፕ፤ ለአጋሮቻቸው ያቀረቡትን የድጋፍ ጥሪ "ልፈትናቸው ያደረግኩት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
ትራምፕ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ "ዛሬ ማታ ኢራን ስምምነት ላይ ካልደረሰች ሙሉ ስልጣኔ ይሞታል" ስለማለታቸውም ተጠይቀው ነበር። ይህ አስተያየታቸው ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ሊዮ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ እና ሰር ኪርን ጨምሮ በስፋት ተወግዟል።
"ሌላኛው ወገን ስምምነት ለማድረግ እየሞከረ ነው" ሲሉ ትራምፕ ገልጸው "ስለዚህ የምለው ወይም የማደርገው ነገር ሁሉ በጥሩ መልኩ እየሠራ ያለ ይመስላል" ብለዋል።
በስልክ ቃለ መጠይቁ መጨረሻ ላይ ፕሬዝዳንቱ በቢቢሲ ላይ የከፈቱትን የባለ ብዙ ቢሊዮን ዶላር የስም ማጥፋት ክስ ጠቅሰዋል።
እአአ ጥር 6/2021 የካፒቶል ረብሻ ከመፈጸሙ በፊት ያደረጉት ንግግር በፓኖራማ ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ያልተናገሩትን ንግግር እንደተናገሩ ሆኖ በመቅረቡ ክስ መስርተዋል።
ቢቢሲ "በጣም መጠንቀቅ" እንዳለበት እና ካልሆነ ስሙን "ሊያጠፋው" እንደሚችል ትራምፕ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ቀደም ሲል በፓኖራማ አርትኦት ምክንያት ትራምፕን ይቅርታ ቢጠይቅም ግን የካሳ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጓል።
"በእኛ ላይ የቀረበውን ክስ በጽኑ እንደምንከላከል በተደጋጋሚ ተናግረናል" ሲሉ የቢቢሲ ቃል አቀባይ ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።
ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በትልልቅ የአሜሪካ ቴክኖሎጂዎች ላይ የተጣለው የ2 በመቶ የዲጂታል አገልግሎት ታክስ ከተነሳ ዩኬ ላይ አዲስ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀዋል።
"እየተመለከትነው ነው። በዩኬ ላይ ትልቅ ታሪፍ ልንጥል ስለምንችል ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው" ሲሉ በኦቫል ኦፊስ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ቢቢሲ ኒውስ ስለጉዳዩ ከዩኬ መንግሥት አስተያየት ጠይቋል።