በዲሞክራቲክ ኮንጎ ደን ውስጥ ተደብቆ የተገኘው ባለ ብርቱካናማ ከንፈር ዝንጀሮ አዲስ ዝርያ ሆኖ ተመዘገበ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደን ውስጥ ተደብቆ የተገኘው ዝንጀሮ በሳይንሱ ዓለም እስካሁን ድረስ ያልታወቀ አዲስ ዝርያ ሆኖ ተመዝግቧል።

የዝንጀሮው ከንፈር ሮዝ እና ብርቱካናማ ቀለም ያለው ሲሆን፤ ፊቱ ደግሞ ጥቁር ነው።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ማዕከላዊ ምሥራቅ አካባቢ በሚገኘው ሎማሚ ብሔራዊ ፓርክ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ ተደብቆ የተገኘውን ባለ ጥቁር ፀጉር ዝንጀሮ ፎቶ ማንሳት እና ቪድዮ መቅረጽ ተችሏል።

የእንሰሳት ጥበቃ ባለሙያዎች በአውሮፓውያኑ 2008 ለየት ያለ ገጽታ ያለው እንሰሳ ማየታቸውን ቢናገሩም የተነሳው አንድ ደብዛዛ ፎቶ ነበር።

ዝንጀሮው ከ10 ዓመት በኋላ በድጋሚ መታየቱን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የአጥኚዎች ቡድን ወደ ሥፍራው ለምርምር አቅንቷል። ዝንጀሮው ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ዓይነት ዝርያ እንደሆነም ተደርሶበታል።

ባለፉት 75 ዓመታት የተገኘ አምስተኛው የአፍሪካ የዝንጀሮ ዝርያ ነው።

በፍሎሪዳ አትላንቲክ ዩኒቨርስቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ ጁንየር አምቦኮ የጥናቱ መሪ ናቸው። ዝንጀሮውን ፎቶ አንስተው፣ ድምጹን ቀድተው የዘረ መል ጥናት ሠርተዋል።

ፕሎስ ዋን በተባለው መጽሔት ላይ የጥናቱ ግኝት ታትሟል።

ጥቂቶች ብቻ መኖሩን የሚያውቁትን እንሰሳ መመልከት "በጣም አስደሳች ስሜት እንደሚፈጥር" ተመራማሪው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አዲስ ዝርያ ተገኝቷል ሲባል እንሰሳው በዝግመተ ለውጥ ልዩ የሚያደርገው ዘረ መል ተለይቶ ተመዝግቧል ማለት ነው።

አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ዝንጀሮው መኖሩን ያውቁ ነበር። 'ሊክዋሊ' በሚል ስያሜም ይጠሩታል።

የጥናቱ መሪ ጁንየር አምቦኮ ዝንጀሮው "ዐይን አፋር" እንደሆነ ገልጸው ዛፍ አናት ላይ ለመደበቅ መሞከሩን ተናግረዋል።

"ለጥናታችን በእንስሳው ቅርብ ርቀት በሚገኙ 52 መንደሮች የሚኖሩ ሰዎችን አነጋግረናል። በስምንት መንደሮች ያሉ ነዋሪዎች ብቻ ናቸው የተመለከቱት" ብለዋል።

ከዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ አሜሪካ እና ጀርመን የተውጣጣ የጥናት ቡድን ለዝንጀሮው የሰጠው የላቲን ስም ኮሎቡስ ኮንጎንሲስ (Colobus congoensis) ሲሆን፤ ይህም ለተገኘበት አገር ዕውቅና ለመስጠት ነው።

ኮሎቡስ የተባለ የዝንጀሮዎች ዝርያ ውስጥ ይመደባል።

የፍሎሪዳ አትላንቲክ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ ፕ/ር ኬት ድትዊለር "እነዚህ በጣም ጠቃሚ የሆኑ እና አውራ ጣት የሌላቸው የአፍሪካ ዝንጀሮዎች ናቸው" ብለዋል።

በጣም ብሩህ የሆነው እና እምብዛም ያልተለመደው የፊታቸው ገጽታ ለሌሎች እንሰሳት ምልክት የሚሰጡበት፣ ከሌሎች ዝንጀሮዎች ጋር የሚለያዩበት እንዲሁም ለስሪያ የሚጋብዙበት መንገድ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ዝንጀሮዎቹ ልዩ የሆነ የጩኸት ድምጽ እንደሚያሰሙ የሚናገሩት ጁንየር አምቦኮ "ድምጻቸው ይሰማል እንጂ በብዛት አይታዩም" ሲሉ ይገልጿቸዋል።

እነዚህ ዝንጀሮች እምብዛም አይገኙም። የሚፈልጉትን ምግብ የሚያገኙበት የደኑ አካባቢ መኖር ይመርጣሉ።

የእንስሳቱ ሥጋ ስለሚበላ በአካባቢው ነዋሪዎች ይታደናሉ።

ልዩ ዝርያ ተብሎ የተመዘገበው ዝንጀሮ ልዩ ከለላ ይደረግለታል ብለው አጥኚዎች ተስፋ ያደርጋሉ።

ስለ ዝንጀሮው ምሥጢራዊ ባሕሪዎች ተጨማሪ ጥናቶችም ይደረጋሉ።