ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኬንያ ራስ ተፈሪያን ካናቢስ ለሃይማኖታዊ ዓላማ እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ተደረገ
የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የራስ ተፈሪያን ማኅበረሰብ የካናቢስ እፅን ለሃይማኖታዊ ዓላማ መጠቀም ሕጋዊ እንዲደረግ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አደረገ።
ራስ ተፈሪያኑ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት የካናቢስ እፅ ክልከላ በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን የሃይማኖት እና የእምነት ነፃነት እንደሚጋፋ በመግለጽ ነው።
ታሪካዊ በሆነው የፍርድ ቤቱ ውሳኔም ዳኛ ባሃቲ ምዋሙይ ማኅበረሰቡ የእፅ ሕጎች እንዴት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንደሚጥስ ማረጋገጥ አልቻለም ብለዋል። ሆኖም በአገር አቀፍ ደረጃ ካናቢስን በተመለከተ የመነጋጋር ፍላጎት እንዳለ አምነዋል።
በኬንያ ካናቢስን ሕጋዊ ለማድረግ የሚደረጉ ግፊቶች ቀጥለዋል።
አንዳንድ ተሟጋቾች ካናቢስን ማምረት እና መነገድ የሥራ እድልን እንደሚፈጥር ፣ የገቢ ግብርን እንደሚያሳድግ እና ኢንደስትሪን እና ሕክምናን እንደሚደግፍ ይከራከራሉ።
በኬንያ የእፅ እና አደንዛዥ ንጥረ ነገሮች ቁጥጥር ደንብ ካናቢስን መጠቀም ወንጀል እንደሆነ ይደነግጋል።
ካናቢስን ሲጠቀም የተገኘ ሰውም እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስር እና እስከ 800 ዶላር የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል።
ካናቢስን ማምረት ደግሞ እስከ 1 ሺህ 900 ዶላር ቅጣት ወይም እፁ የሚያወጣውን ዋጋ ሦስት እጥፍ የገንዘብ ቅጣት እንዲሁም እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስርን ያስከትላል።
ለዝውውር እና ሌሎች ከእፅ ጋር ለተያያዙ ወንጀሎችም ተጨማሪ ከባድ ቅጣቶች ተግባራዊ ይደረጋሉ።
ራስ ተፈሪያኑ ባሰባሰቡት ፊርማ ካናቢስ በእምነታቸው 'ቅዱስ' እንደሆነ ጠቅሰው፣ ተከታዮቻቸው እፁን እንዲያለሙ እና በአምልኮ ሰዓት ያለምንም የእስር ስጋት እንዲጠቀሙ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።
እየጠየቁ ያሉት የካናቢስን የጅምላ ሽያጭ ፈቃድ እንዳልሆነ በማስረገጥም፣ ለሃይማኖታዊ ዓላማ በግል ቤቶች እና የአምልኮ ሥፍራዎች ውስን የሆነ ፈቃድ እንዲሰጣቸው እንደሆነ አስረድተዋል።
ሆኖም ፍርድ ቤቱ ለሃይማኖታዊ ዓላማ መፍቀዱ የፀረ አደንዛዥ እፅ ሕግ አተገባበር ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል እንዲሁም ለሕገ ወጥ የእፅ ዝውውር መንገድ ይከፍታል ሲል ጥያቄያቸውን ሳይቀበለው ቀርቷል።
ዳኛ ምዋሙየ የእፅ ሕግ ካናቢስን ማምረት ፣ ይዞ መገኘት እና መጠቀምን እንደሚከለክል በመግለፅም ራስ ተፈሪያኑ ለስድስት ዓመት ያደረጉትን ትግል መና አስቀርተውታል።
ዳኛው ካናቢስን ለሃይማኖታዊ ዓላማ ጥቅም ላይ እንዲውል ለመፍቀድ ሌላ ሕገ መንግሥት እና ሕጋዊ መሠረት ሊኖር ይገባል ብለዋል።
" የካናቢስ ጉዳይን በተመለከተ ምን ዓይነት አቅጣጫ ልንከተል እንደሚገባ ትክክለኛ የሆነ ውይይት ያስፈልገናል" ሲሉም ይህ የራስ ተፈሪያኑ ጥያቄ ብቻ እንዳልሆነ አመልክተዋል።
የማኅበረሰቡ ጠበቃ ዳንስታን ኦማሪ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።
"ኬንያ የራስ ተፈሪያንን ማኅበረሰብ የምታስቸግር ብቸኛዋ አገር ልትሆን አትችልም። የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለመሻር እና በኬንያ የራስ ተፈሪያውያንን ክብር ለመመለስ ቆርጠን ተነስተናል" ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው ሌላኛው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፀጉሯን ድሬድ ያደረገች ተማሪ ከትምህርት ቤት መባረሯን ተከትሎ እርምጃው ሕገ መንግሥታዊ መብቷን የጣሰ ነው ሲል ራስ ተፈሪያን ሃይማኖት እንደሆነ እውቅና ከሰጠ ከሰባት ዓመት በኋላ ነው።
በኬንያ ያሉ ራስ ተፈሪያን ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ አይታወቅም። ሆኖም እንቅስቃሴው በተለይ በወጣቶች ዘንድ እያደገ እንደሆነ ይታሰባል።
ራስ ተፈሪያኑ ፀጉራቸውን ድሬድ ሎክ የማድረግ ባህል ያላቸው ሲሆን ይህም ከኬንያ ፀረ ቅኝ ግዛት ታሪክ ጋር የሚገናኝ ነው።
የእንግሊዝን አገዛዝ የተፋለሙ የማኦ ማኦ ተዋጊዎች ፀጉራቸውን በረዥሙ ያሳድጉ የነበረ ሲሆን ይህም የተቃውሞ ምልክት ተደርጎ ይታያል።