ቮልስዋገን 100 ሺህ ሠራተኞችን ለመቀነስ ማቀዱ ተገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የጀርመኑ ግዙፉ መኪና አምራች ኩባንያ - ቮልስዋገን ግሩፕ- በዓለም አቀፍ ደረጃ 100 ሺህ ሠራተኞችን ለመቀነስ ማቀዱን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አረጋገጡ።

ቁጥሩ ቀደም ሲል ከተገለፀው በሁለት እጥፍ የላቀ ነው።

መኪና አምራቹ ቀደም ሲል በ2030 በጀርመን ወደ 50 ሺህ ሠራተኞችን እንደሚቀንስ ገልጾ ነበር።

ድርጅቱ በዋና ገበያው ሽያጩ እየቀነሰበት በመምጣቱ እንዲሁም የቻይና ብራንድ ወደ አውሮፓ በመግባቱ ምክንያት ባለፈው ዓመት ትርፉ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶበታል።

በስፋት በተሰራጨና ለሠራተኞች የተላከ ማስታወሻ ላይ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኦሊቨር ብሉም፣ ድርጅቱ ወጪዎቹ ከሌሎች ተፎካካሪ ቢዝነሶች ጋር ሲወዳደር 20 በመቶ መጨመሩን እና ይህንን መቀነስ እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

ይህም በጠቅላላ በዓለም 50 ሺህ ሠተራኞች ይቀነሳሉ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።

" ምን ያህል ማስተካከያዎች አስፈላጊ እና ተጨባጭ እንደሆኑ ለማወቅ አሁን ላይ ሁሉንም ብራንዶች፣ ኩባንያዎች እና ቀጣናውን እየገመገምን ነው" ብለዋል።

" በጣም ውጤታማ እና ቀልጣፋ መሆን አለብን፤ ወጪያችንንም መቀነስ አለብን" ሲሉም አክለዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጨምረውም ኩባንያው " ከዚህ ቀደም የመዘጋት እጣ ፋንታ ተደቅኖባቸው የነበሩት በጀርመን የሚገኙ አራት ፋብሪካዎቹ ለሌላ አገልግሎት መዋላቸውን በተመለከተ ማረጋገጥ አልቻለም ብለዋል።

በዝዊካው እና በኤምደን የሚገኙት ሁለቱ ፋብሪካዎቹ የኤሌክትሪክ መኪና ለማምረት የሚያገለግሉ ሲሆን በሃኖቨር እና በኔካርሱልም ከሚገኙት ሌሎች ፋብሪካዎች ጋር ሲነፃፀሩ የሥራ ማስኬጃቸው ውድ እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቮልስዋገን ትርፉ እያሽቆለቆለበት ነው።

እአአ በ2023 የተጣራ 25.8 ቢሊዮን ዶላር (22 ሚሊዮን ዩሮ) ትርፍ ያገኘ ሲሆን፣ ይህ በ2024 ወደ 19.1 ቢሊዮን ዩሮ ወርዷል። ባለፈው ዓመት ደግሞ ወደ 8.9 ቢሊዮን ዩሮ ተንኮታኩቷል።

ኩባንያው በተለይ ዋነኛ የሆነው የቻይና ገበያው በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶበታል።

በአሜሪካም የትራምፕ አስተዳዳር ወደ አገሩ በሚገቡ መኪኖቹ ላይ ከጣለው ታሪፍ ጋር ተያይዞ ያለው ሽያጭ ከሰባት በመቶ በላይ አሽቆልቁሎበታል።

በዚህ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ያለው ገበያው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 26 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

ይህ በእንዲህ እያለ የቻይና መለያ ያላቸው ምርቶች በስፋት ዓለም አቀፍ ገበያውን እየተቀላቀሉ ነው። እነዚህ ምርቶች ከአውሮፓ ተፎካካሪያቸው ጋር ሲነፃፀሩ ዝቅተኛ የምርት ወጪ ነው ያላቸው።

ይህም ሌሎች ነባር ብራንዶች ወጪያቸውን ለመቆጣጠር እና ትርፋቸውን ለማስጠበቅ እንዳይችሉ ጫና ፈጥሮባቸዋል።

በ2024 በሥራ ማቆም አድማ ዛቻ ምክንያት ቮልስዋገን ከጀርመኑ የንግድ ማኅበር ሜቶል ጋር በ2030 "ማኅራዊ ኃላፊነትን ከግምት ባስገባ" መልኩ 35 ሺህ ሠራተኞችን እንደሚቀንስ እና ሌሎች 15 ሺህ ሠራተኞቹን ደግሞ በሌሎች ምርቶቹ ለመቀነስ ከስምምነት ደርሶ ነበር።

እቅዱ አሁንም ውይይት እየተደረገበት ነው።

የሠራተኞች ተወካዮች እና የድርጅቱ ኃላፊዎች የሚሳተፉበት የቮልስዋገን ቦርድ ስብሰባ ከመደረጉ አስቀድሞ ባለፈው ሳምንት በመላ ጀርመን በቮልስዋገን ተቋማት ሰፊ ተቃውሞ ተካሂዷል።

አንዳንድ የዘርፉ ተንታኞች ቮልስዋገን ሆነ ብሎ 100 ሺህ ሠራተኞችን እንደሚቀንስ በይፋ ያስታወቀው እንደ የመደራደሪያ ስልት እንደሆነ እና ቁጥሩ አነስተኛ ሊሆን እንደሚችል ለኤኤፍፒ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።