ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሱዳን በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ እና 15 የጦር አዛዦች ላይ የሞት ፍርድ አስተላለፈች
የሱዳን ፍርድ ቤት ከአገሪቱ ጦር ጋር ጦርነት ላይ ያለውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በሚመሩት ሞሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ላይ በሌሉበት የሞት ፍርድ አስተላለፈ።
ሄሜቲ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው በጦር ወንጀል፣ በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች እንዲሁም በምዕራብ ዳርፉን ክልል በተካሄደ ዘር ማጥፋት ነው።
የጸረ ሽብር እና በአገር ላይ የተፈጸመ ወንጀልን ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት፤ ከሄሜቲ በተጨማሪ 15 የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) አዛዦች እና አጋሮቻቸው ላይ በስቅላት የሞት ፍርድ እንዲፈጸም ውሳኔ አስተላልፏል።
በፖርት ሱዳን የሚገኘው ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ካስተላለፈባቸው መካከል የሄሜድቲ ወንድም እና ምክትላቸው የሆኑት አብደልራሂም ሃምዳን ዳጋሎ ይገኙበታል። ሌላኛው ወንድማቸው አል ቆኒ ሃምዳን ዳጋሎ እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የምዕራብ ዳርፉር አዛዥ አብዱል ራህመን ጁማ ባርካላህም ተፈርዶባቸዋል።
አቃቤ ሕግ ክሱን የመሠረተው በምዕራብ ዳርፉር ዋና ከተማ በሆነችው በኤል ጄኒና የተፈጸሙ ወንጀሎችን እንዲሁም እአአ በሰኔ 2023 ካህሚስ አባካር የተባሉ የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ግድያ በማካተት ነው።
ፍርድ ቤቱ፤ ተከሳሾቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃቶችን በማቀነባበር እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን፣ የአምልኮ ስፍራዎችን እና የመኖሪያ አካባቢዎችን ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ ውድመት በመፈጸም እና በመዝረፍ ጥፋተኛ ናቸው ብሏል።
ዳኛው ሞሃመድ አል አሚን ሁሉም የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ንብረቶች ተወርሰው ለሱዳን መንግሥት ገቢ እንዲደረጉ የወሰኑ ሲሆን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ኢንተርፖል ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር አውሎ እንዲያስረክባቸው እንዲጠይቁ አዝዟል።
በሱዳን እአአ በ2023 የእርስ በእርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አመራሮች ላይ እንዲህ ዓይነት የፍርድ ውሳኔ ሲሰጥ ይህ የመጀመርያው ነው።
ይሁን እንጂ ቡድኑ በርካታ የምዕራብ ሱዳን ስፍራዎችን በመቆጣጠሩ እና መሪዎቹም ከባለሥልጣናት እይታ ርቀው ስለሚገኙ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሚኖረው ተጽዕኖ ግልጽ አይደለም።
ሄሜቲ ያሉበት ቦታ በይፋ አይታወቅም።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ አስተያየቱን ያልሰጠ ቢሆንም ከዚህ በፊት ግን በጦር ወንጀሎች የቀረቡበትን ውንጀላዎች ውድቅ አድርጓል።
የተባበሩት መንግሥታት መርማሪዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አርኤስኤፍ እና የአረብ አጋሮቻቸው ብሔር ተኮር ጥቃት በማሳሊት ነዋሪዎች ላይ ፈጽመዋል ሲሉ ወንጅለዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በግንቦት 2024 ሂውመን ራይትስ ዎች ባወጣው ሪፖርት በኤል ጄኒና እና አካባቢው ከሚያዚያ እስከ ኅዳር 2023 ድረስ በተካሄደ ዘመቻ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሲገደሉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ደረግሞ ተፈናቅለዋል ብሏል።
ድርጅቱ የተፈጸሙት ጥቃቶች በማሳሊት ሕዝብ ላይ እና ሌሎች አረብ ባልሆኑ ሕዝቦች ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻው አካል መሆናቸውን ከጦር እና ከሰብዓዊነት ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ መሆናቸውን ጠቅሷል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) በ2021 አል ቡርሐን መፈንቅለ መንግሥት በሚወጥኑበት ወቅት እገዛ አድርጎላቸዋል።
ይህ ግን ጄነራል ዳጋሎ የመከላከያ ኃይላቸውን ወደ ጦር ሠራዊቱ የማዋሀድ ዕቅዱን ከተቃወሙ በኋላ ወደ አለመግባባት እና ወደ ጦርነት አድጓል።