ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ከቀናት ተቃውሞ በኋላ የአገሪቱን የጦር አዛዥ አባረሩ
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የአገሪቱን የጦር አዛዥ ኦሌክሳንደር ስሪስኪን ከሥልጣናቸው አባረሩ።
የጦር አዛዡ ከሥራቸው የተባረሩት ተወዳጅ የሆኑት የመከላከያ ሚኒስትር ሚካየሎ ፌዶሮቭ መነሳታቸው በመላው አገሪቱ ተቃውሞ ካስነሳ ከቀናት በኋላ ነው።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ከኃላፊነታቸው ለመነሳታቸው መጀመሪያ የነበረው ከጦር አዛዡ ጋር የነበራቸው የግጭት ጭምጭምታ በኋላ ላይ ተረጋግጧል።
የ35 ዓመቱ ፌዶሮቭ ሚኒስቴሩን በማነቃቃት እና የጦር ኃይሎችን በማሸጋገር እንዲሁም በሙስና ላይ በወሰዷቸው እርምጃዎች አድናቆትን አግኝተዋል።
የ60 ዓመቱ የጦር አዛዥ ሴሪስኪ በዩክሬን በብዙዎች በጦሩ ውስጥ ስር ነቀል ለውጥ ለማድረግ ያመነቱ የሶቪየት ኅብረት ዘመን አዛዥ ተደርገው ይታያሉ።
በ43 ዓመቱ ታዋቂ የጦር ግንባር ጀነራል ሚካየሎ ድራፓቲ ተተክተዋል።
"በኃላፊነት እሠራለሁ፤ በሙሉ ትኩረት እና ዛሬ አገራችንን እየተከላከሉ ያሉ ሰዎችን አክብሬ እሠራለሁ" ሲሉ አዲሱ የዩክሬን ጦር አዛዥ በፌስቡክ ገፃቸው ገልፀዋል።
የተኳቸውን የጦር አዛዥ "የዩክሬንን ጦር ለማጠናከር ወጥ ለሆነው ሥራቸው" አመስግነዋል።
"እዚህ ላይ ነው ያደግኩት" ሲሉ አክለዋል።
ማክሰኞ እለት በማኅበራዊ የትስስር ገፆች በተለጠፈ ተንቀሳቃሽ ምስል ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ፤ ኦሌክሳንደር ስሪስኪ እ.አ.አ በ2022 ሩሲያ በጀመረችው ወረራ የመጀመሪያዎቹ ቀናት ዋና ከተማዋን ኪየቭን በስኬት በመከላከል የነበራቸውን ሚና ጨምሮ ለወታደራዊ ተልዕኳቸው አመስግነዋል።
ከኃላፊነታቸው ለተነሱት የመከላከያ ሚኒስትርም "የሚገባ የሥልጣን መደብ" እንዳቀረቡላቸው የተናገሩ ሲሆን፤ ፌደሮቭ ይህን ኃላፊነት መቀበላቸውን ግን አልጠቀሱም።
ፌዶሮቭ ባለፈው ሳምንት በቀድሞ የደኅንነት ባለሥልጣን ተተክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፌደሮቭ ለአዲሱ የጦር አዛዥ እንኳን ደስ አለዎት የሚል መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ ሥራቸውን "ለሕዝቦች ነፃነት እና ፍትሕ በሚደረገው ውጊያ አዲስ ተስፋ" ሲሉ ገልፀውታል።
"ወደ ጎን የማይባሉ የለውጥ ድምፅ" ሲሉም ጠርተዋቸዋል።
ፌደሮቭ ወደ ተነሱት የጦር አዛዥ ኦሌክሳንደር ስሪስኪ የኪየቭ ክልልን በመከላከል እና በሌሎች "ታሪካዊ ጦርነቶች" ለማመስገን ደውለው እንደነበር ተናግረዋል።
"ይሁን እንጂ ከዚህ ፍጥነት በላይ መራመድ እና ሁሉንም የቀድሞ ስህተቶች ለማረም አዲስ ምዕራፍ መፃፍ አለብን" ብለዋል።
ፌደሮቭ ባለፈው ጥር የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ቢሾሙም የጦር ግንባሮችን በመረጃ ትንተና ለመምራት ባሳዩት ብቃት ሰፊ ተወዳጅነት አላቸው።
የቀድሞ 'የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን' ሚኒስትር ሲሆኑ በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀናት ሩሲያ ላይ የሳይበር ጥቃት ለመፈፀም "የዩክሬን የአይቲ ጦር" የሚል የበጎ ፈቃድ ቡድን አቋቁመዋል።
ከሥልጣን መነሳታቸው በዩክሬን የስድስት ቀናት ተቃውሞ የቀሰቀሰ ሲሆን፤ ይህም ፕሬዝዳንቱ የጦር አዛዡን እንዲያባርሩ ጫና ፈጥሮባቸዋል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ወጣት እና ፈጠራ ዘመም የሆኑትን ደራፓቲን የጦሩ አዛዥ በማድረግ ለጫናው የተንበረከኩ መስለዋል።
ደራፓርቲ የፌደሮቭ የቅርብ ወዳጅ እንደሆኑ ይታመናል።