ደቡብ አፍሪካ በዓለም ዋንጫ በሜክሲኮ በመሸነፏ ከአፍሪካውያን ደጋፊዎች ፌዝ ገጠማት

የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ደቡብ አፍሪካዊያን በሜክሲኮ ከተሸነፉ በኋላ ጭንቀት ውስጥ ሆነው ታይተዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በዓለም ዋንጫ መድረክ የተለመደው የአፍሪካ አንድነት መገለጫ ዘንድሮ በማኅበራዊ የትስስር ገፆች አልነበረም።

በመላው አህጉሪቱ በርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪያን በዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ ላይ ደቡብ አፍሪካ እና ሜክሲኮ ሲገናኙ የሜክሲኮ ደጋፊዎች ነበሩ።

በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ከተጋሩ የፌዝ ምሥሎች መካከል ሜክሲኮ የምትታወቅበት ባርኔጣ፣ የሙዚቃ ማሪያቺ ባንድ እና ታኮ መዘዋወር በቀላሉ የሚታዩይቢመስልም በውስጡ ግን ጥቁር ነጥብ ይዟል።

ቀልድ አዘል ክርክሩ በደቡብ አፍሪካ የተቀሰቀሰውን የመጤ ጠል ጥቃቶችን ያንፀባርቃል።

በዓለም ዋንጫ ሜዳ ደካማ አቋም ያሳየችው ደቡብ አፍሪካ በጋራ አዘጋጇ ሜክሲኮ ሁለት ለዜሮ እንድትሸነፍ አድርጓታል።

የፍፃሜው ፊሽካ ሲነፋ ማኅበራዊ ሚዲያው በመሳለቂያ ልጥፎች ተሞልቷል። አንዳንድ ደቡብ አፍሪካዊያን ቡድናቸውን በመከላከል 'ባፋና ባፋና' በመባል የሚታወቀውን የቡድኑን ስሜት አድንቀዋል።

ደቡብ አፍሪካ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጥምረት ባዘጋጁት የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ከሚሳተፉ 10 የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ አንዷ ናት።

ከሐሙሱ ጨዋታ አስቀድሞ አንዳንድ የአፍሪካ እግር ኳስ ደጋፊዎች የሜክሲኮ ድጋፋቸውን በአሁኑ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ በስተኞች ጉዳይ ካለው ውጥረት ጋር አያይዘውታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"እግር ኳስ ስትጫወቱ አፍሪካዊ በመሆናችን ብቻ እንድንደግፋችሁ ትፈልጋላችሁ?" በማለት አንድ የኤክስ ተጠቃሚ የስደተኞችን ተገቢ ያልሆነ አያያዝ በመጥቀስ አስፍሯል።

"ሜክሲኮን እየደገፍን ነው። ምክንያቱም ደቡብ አፍሪካ ቀድማ አገሯ ሄዳ ሥራዎቿን እንድትጠብቅ" በማለት ሌላ ተጠቃሚ፤ የውጭ አገር ሰዎች ለደቡብ አፍሪካ የሥራ አጥ ምጣኔ ኃላፊነት አለባቸው የሚለውን ክስ ጠቁሟል።

በኬንያ ታዋቂ ጠበቃ የሆኑት አህመድናስር አብደላሂ ደግሞ "ደቡብ አፍሪካ ከሜክሲኮ ጋር በነበራት ጨዋታ ሁለት ለዜሮ ለሆነው ሽንፈቷ እና ለሁለት ቀይ ካርዷ የአፍሪካ ስደተኞችን ተጠያቂ እንደማታደርግ ተስፋ አለኝ" ብለዋል።

ሌሎች ደግሞ የሜክሲኮ ባህልን በመቀበል የመለያ ምሥላቸውን ወደ ሜክሲኮ ሰንደቅ ዓላማ በመቀየር እና ስፓኒሽ ቋንቋ ለዛ ወደላቸው ስሞች በማጋደል "ሜክሲኮ ከዚኖፎቢያ ጋር" ከሚል ፅሑፍ ጋር አጋርተዋል።

የኮንጎ ደጋፊ የሆነው እና በአሜሪካ አትላንታ ከተማ የደጋፊዎች ፓርክ ውስጥ የነበረው ዳንኤል ካኒኪ ለቢቢሲ "አፍሪካ አንድ አገር አይነት ናት። እና አንዱ ሌላኛውን የሚያባርር ከሆነ ከዚህ በኋላ አንድ ቤተሰብ አይደለንም። ዛሬ ሜክሲኮን የምደግፈው ለዚህ ነው" ብሏል።

ይሁን እንጂ ሁሉም በዚህ አይስማማም።

በዚህ ፓርክ ውስጥ የነበረው ጋናዊ ቫናሪ ኪውስት ደቡብ አፍሪካን እየደገፈ እንደሆነ እና "ኩሩ አፍሪካዊ" መሆኑን ተናግሮ፤ በደቡብ አፍሪካ ላለው የመጤ ጠልነት አዝማሚያ ጥቂት ግለሰቦችን ወቅሷል።

በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ በሕዝባዊ የእይታ ማዕከል ውስጥ የነበሩ ደጋፊዎች ባፋና ባፋናን እየደገፉ ነበር።

የ23 ዓመት ተማሪ የሆነው ጆርጅ ኬኒ ቻርለስ ሬሂና ለቢቢሲ "በማኅበራዊ ሚዲያ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ሜክሲኮን በመደገፍ እና የሜክሲሆን ማሊያ በመልበስ ያየነው ነገር ምቾት አልሰጠንም። እንደ ደቡብ ሱዳናዊ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ነን እናም ደቡብ አፍሪካን መደገፋችንን እንቀጥላለን። ምክንያቱም አፍሪካን ስለወከሉ። ስለዚህ ሁሉም የአፍሪካ አገራት በዚህ ዓለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካን መደገፍ አለባቸው" ብሏል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ባወጠው መገለጫ "ስሜት ላለው ጨዋታቸው" ባፋና ባፋና አመስግኗል።

የመጨረሻው ውጤት እንደተመኘነው ባይሆንም ቡድኑ "ደቡብ አፍሪካን በአንነድት፣ በቁርጠኝነት እና በዓለም ትልቁ መድረክ በኩራት ስሜት ወክሏል" ብሏል።

ደቡብ አፍሪካዊያን በማኅበራዊ ሚዲያ ለተጋሩ የፌዝ ልጥፎችም ምለሽ ሰጥተዋል።

"ለዓለም ዋንጫ ያለ እናንተ ድጋፍ አልፈናል። እና ብናሸንፍም ብንሸነፍም አገራቸውን የሚወዱ ደቡብ አፍሪካዊያን መሆናችንን እንቀጥላለን። እና ሕገ ወጥ ስደተኞች ወደዳችሁም ጠላችሁም አሁንም አገራችንን ለቀው ይወጣሉ" ሲል አንድ ተጠቃሚ አጋርቷል።

ሌላ ተጠቃሚ ደግሞ "ሜክሲኮን እንደፈለጉ መደገፍ ይችላሉ፤ እኛ ወደ ኋላ አንልም። ወደ ደቡብ አፍረካ በሕጋዊ መንገድ ኑ" ብሏል።

በደቡብ አፍሪካ ከአፍሪካ የመጡ ስደተኞች ባለፉት ሳምንታት የጥቃት እና የዛቻ ዒላማ ሆነዋል።

ፀረ ስደተኛ ተቃዋሚዎች ካለ ሕጋዊ ሰነድ የሚኖሩ ስደተኞች አገሪቱን እስከ ሰኔ 23/ 2018 ዓ.ም. ድረስ ለቀው እንዲወጡ ቀን ቆርጠዋል።

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በራሳቸው እጅ ሕግ ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን አስጠንቅቀው "ፈቃድ ያላቸው የመንግሥት ተቋማት ብቻ ሕግ ሲጣስ ያስከብራሉ" ብለዋል።