ዩኬ ቲክቶክን ጨምሮ ከ16 ዓመት በታች ላሉ ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያን ልታግድ ነው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ቲክቶክ፣ ስናፕቻት እና ኢንስታግራምን ጨምሮ ከ16 ዓመት በታች ላሉ ታዳጊዎች ትላልቅ የማኅበራዊ የትስስር ገፆችን እንደሚያግዱ አስታወቁ።

መንግሥት ሕፃናት "ደኅንነት" አላቸው በተባሉ ድረ ገፆች ላይ በቀጥታ እንዳያስተላልፉ እና በጌም መተግበሪያዎች የማያውቋቸውን ሰዎች እንዳያነጋግሩ ያግዳልም ተብሏል።

የአገሪቱ ሚኒስትሮች ለታዳጊዎች የማኅበራዊ የትስስር ገፆች መጠቀሚያ የሰዓት እላፊ እግድ ለማውጣትም ያሰቡ ሲሆን፤ ነገር ግን ዕቅዱ በሚቀጥለው ወር ይፋ እስኪሆን ድረስ ተጨማሪ ዝርዝሮች አልተገለጹም።

አውስትራሊያ ባለፈው ታኅሳስ ከ16 ዓመት በታች ማኅበራዊ የትስስር ገፆችን በማገድ የዓለማችን የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።

የመንግሥት ምንጮች ዕቅዱ ከአውስትራሊያው ጠበቅ የሚል እንደሆነ ጠቁመዋል።

ሰር ኪር ስታርመር "ከየትኛው ወገን እንደሆንን የምንመርጥበት ነው። በመላው አገሪቱ ካሉ ቤተሰቦች ወይስ እየሰራ ካልሆነው ነባራዊ ሁኔታ" ብለዋል።

ምንም እንኳ በመንግሥታዊ መማክርት ከ16 ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት ማኅበራዊ የትስስር ገፆችን ለማገድ ትልቅ ድጋፍ ቢያገኙም፤ አንዳንድ ተሟጋቾች እንደዚህ ዓይነት ድፍን ያለ እርምጃ የበለጠ ችግር ያመጣል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች የታገዱትን 10 መድረኮች ይፋ አድርገዋል።

ይህም ቲክቶክ፣ ስናፕቻት እና ኢንስታግራምን የሚጨምር ሲሆን፤ ዩቲዩብ፣ ረዲት፣ ቲውች፣ ኤክስ፣ ትሬድስ፣ ፌስቡክ እና ኪክን አይጨምርም።

ዩናይትድ ኪንግደም ከአውስትራሊያ በበለጠ እግዱን ጠበቅ እንደምታደርግ የተጠቆመ ሲሆን፤ በእድሜ ከፍ ላሉ ታዳጊዎች የሰዓት ገደብ እና የኤአይ የመልዕክት ልውውጦችን እንደምትገድብ ተነግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር "ሕፃናትን ከኢንተርኔት እንዴት መጠበቅ እንዳለብን የዘመናችን መከራከሪያ ነው። እንደ ወላጅ አባት እያንዳንዱ ወላጅ ልጆቹ ደስተኛ እና ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲያድጉ እንደሚፈልጉ አውቃለሁ" ብለዋል።

"ይህ በመላው አገሪቱ ከቤተሰብ ወይንም እየሰራ ካልሆነው ነበራዊ ሁኔታ ውስጥ ከየትኛው ወገን እንደሆንን የምንመርጥበት ነው።"

"ሰዎች ትክክለኛ እርምጃ ይጠብቃሉ፤ እና ይህ መንግሥት ሁሌም ለወላጆች የሚቆም እና ልጆችን የሚያስቀድም ነው።

"ለዚህም ነው ልጆቻችን እየጎዳ ያለው ስርዓት ላይ ጊዜ ወስደን እና ሁሉም ሕፃናት የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ወሳን እርምጃ የምንወስደው" ብለዋል።

መንግሥት ቀን የቆረጠለት የሦስት ወራት ምክክር ጊዜው ካበቃ በኋላ ነው አዲሱ ዕቅድ ይፋ የሚያደርገው።

ከማኅበረሰቡ ክፍልም ስለ እግዱ አስተያየት ተጠይቋል። በአስተያየቱ ሱስ የሚያሲዙ መሣሪያዎችን መዝጋት፣ የሰዓት እልፊ ገደብ፣ የእድሜ ቁጥጥርን ማጠናከር እና የኤአይ የመልዕክት መለዋወጫ መገደብ ይገኙበታል።