ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማትን አስመልክቶ ኖርዌይን በመተቸት 'ለአገሪቱ ጠባሳ' ይተዋል አሉ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማትን ባለማግኘታቸው በድጋሚ ቅሬታቸውን ገልጸው፣ የዘንድሮውን ውሳኔ "አሳፋሪ እና ክብረ ነክ" ሲሉ ጠርተውታል።

የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት የተሰጠው ለቀድሞዋ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ናቪ ፒላይ ነው።

ደቡብ አፍሪካዊቷ ፒላይ ዕውቅናው የተሰጣቸው "ለሰላም፣ ዓለም አቀፍ ሕግን ለማስከበር እንዲሁም ለጦር እና ለዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲኖር ላደረጉት አስተዋፅኦ" መሆኑን የኖቤል ኮሚቴ አስታውቋል።

የዘንድሮው የሰላም ኖቤል ለማን እንደተሰጠ ይፋ ከሆነ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ዶናልድ ትራምፕ በኒው ዮርክ በተካሄደ የምርጫ ቅስቃሳ ዘመቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ስለዚች "ሚስጥራዊው ሰው"፤ "በፍፁም ሰምቼ አላውቅም" ብለዋል።

"ይህ በኖርዌይ ላይ የማይጠፋ ጠባሳ ነው" ያሉት ትራምፕ "አንረሳውም" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማትን ለማግኘት ያላቸውን ፍላጎት በተደጋጋሚ በግልጽ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ለቬንዙዌላ የተቃዋሚ መሪ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ በተሰጠበት ወቅትም ተመሳሳይ ትችቶችን አቅርበዋል።

ባለፈው ዓመት የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆናስ ጋህር ስቶር ለትራምፕ ሽልማቱን የሚያገኘው ማን እንደሆነ የሚወሰነው በኖርዌይ መንግሥት ሳይሆን በገለልተኛ ኮሚቴ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በኒው ዮርክ ሲራኩስ በተካሄደው የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ለደጋፊዎቻቸው ስምንት ጦርነቶችን ማስቆማቸውን እና "ሁለት ተጨማሪ ጦርነቶችን እልባት ሊሰጡ ወይም ሊያሸንፉ እንደሆነ" ተናግረዋል።

"የኖቤል የሰላም ሽልማት ፀረ ዲሞክራሲ እና ሥልጣኔ ጠል በሆኑ ጥቂት አክራሪ ቡድኖች ምክንያት ተዓማኒነቱን አጥቷል" ብለዋል።

ደቡብ አፍሪካዊትዋ ዳኛ ናቪ ፒላይ የዘንድሮዉን የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሸነፉት ለሰላም እና ለዓለም አቀፍ ሕግ መከበር ላደረጉት ጥረት መሆኑን የሽልማት ኮሚቴው ይፋ አድርጓል።

እንደኖቤል ኮሚቴው ገለጻ፣ በዚህ ዓመት ለሰላም ሽልማቱ በአጠቃላይ 287 እጩዎች ቀርበዉ ነበር። ከእጩዎቹ መካከል፤ በተለይ የዩክሬን የሰብዓዊ እና የሕፃናት መብት ተሟጋች ማይኮላ ኩሌባ፣ የሕፃናት እርዳታ ድርጅት "ሴቭ ዘ ችልድረን" እና መንግሥታዊ ያልሆነው የጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ ፤ ያሸንፉ ይሆናል ተብለዉ ከተጠበቁት መካከል ነበሩ።

ደቡብ አፍሪካዊቷ ዳኛ ናቪ ፒላይ፣ በአገራቸው ከተካሄደው አፓርታይድ እስከ ሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ክስ፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሆነው አገልግለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ነፃ ዓለም አቀፍ የፍልስጤም ግዛት የምርመራ ኮሚሽን ሊቀመንበር በመሆንም ሠርተዋል።

የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ሊቀመንበር ዮርገን ዋትኔ ፍሪድነስ ስለ ናቪ "የጦር ወንጀሎች፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተገቢውን ቅጣት ማግኘታቸውን በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል" በማለት ተናግረዋል።

የ85 ዓመቷ አዛውንት ፒላይ ሽልማቱን እንዳሸነፉ ሲነገራቸው እውነት መሆኑን ለማመን መቸገራቸውን ተናግረዋል።

"ቀልድ መሆን አለበት" ያሉት ፒላይ፣ "አድናቆታችሁ ለእኔ ብዙ ነገር ማለት ነው፤ ግን እንደ የሕግ ሰው እና ዳኛ ይህንን ማጣራት አለብኝ" ሲሉ ንግግራቸውን በቀልድ አዋዝተዋል።

ቀጥለውም "ትንሽ ካጨበጨባችሁልኝ ሽልማቱን ለትራምፕ ላጋራ እችላለሁ" ሲሉም ባለፈው ዓመት የኖቤል የሰላም ተሸላሚ የሆኑት ማሪያ ኮሪና ማቻዶ ሜዳሊያቸውን ለአሜሪካው ፕሬዚደንት መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

ባለፈው ዓመት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሽልማቱን በማጣታቸው ቅሬታቸውን በግልጽ ካስታወቁ በኋላ ዋይት ሐውስ ኮሚቴው "ፖለቲካን ከሰላም በላይ አስቀምጧል" ሲል ከሷል።

በጥር ወር ማቻዶ ለትራምፕ በዋይት ሐውስ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ሜዳሊያዋን ሰጥታለች። ሜዳሊያዋን የሰጠቻቸው ለአገሯ ነፃነት ላሳዩት ቁርጠኝነት እውቅና ለመስጠት እንደሆነ ተናግራለች።

ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንደተናገሩት እርምጃው "እርስ በርስ የመከባበር አስደናቂ ምልክት ነው" ብለዋል።

የኖቤል ኮሚቴ በኋላ ላይ ሽልማቱ ሊተላለፍ የማይችል መሆኑን ግልጽ አድርጓል።

"የኖቤል ሽልማት አንዴ ከታወጀ በኋላ ሊሻር፣ ሊጋራ ወይም ለሌሎች ሊተላለፍ አይችልም" ሲል በመግለጫው አስታውቋል። "ውሳኔው የመጨረሻ እና ለዘላለም የሚጸና ነው" ብሏል።