በሞያሌ ከተማ ዛሬ አርብ ተኩስ ቀጥሎ መዋሉን እና ንብረቶች መቃጠላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በሚጋሯት የድንበር ከተማዋ ሞያሌ የተቀሰቀው ግጭት ዛሬ አርብም ቀጥሎ መዋሉን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ። በከተማዋ የሚገኙ በርካታ መደብሮች እና ቤቶች መቃጠላቸውንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ከሶማሌ ክልል ባንዲራ መሰቀል ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰው ግጭት የተጀመረው ባለፈው ሳምንት እሁድ ጥቅምት 8/2019 ዓ.ም. ነበር። ከዚሁ ውዝግብ ጋር በተያያዘ አንዲት የ13 ዓመት ልጅ መገደሏ ግጭቱን ያባባሰው ሲሆን ከትናንት ሐሙስ ንጋት ጀምሮ ደግሞ የተኩስ ልውውጥ መጀመሩን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ይህንን ግጭት የሸሹ ነዋሪዎች በኬንያ ማርሳቢት ግዛት ውስጥ ወደሚገኘው ሌላኛው ሞያሌ መሻገራቸውን የአገሪቱ ቀይ መስቀል አስታውቋል።

ቢቢሲ፣ የዛሬውን የከተማዋን ውሎ በተመለከተ አመሻሽ ላይ ያነጋገራቸው ሦስት የሞያሌ ነዋሪዎች ዛሬም ከንጋት አንስቶ የተኩስ ልውውጥ መቀጠሉን አስረድተዋል። አንድ ነዋሪ "ዛሬ ትንሽ በጣም ከበድ ያለ ነው፣ የተለየ ነው" ሲሉ ሁኔታውን ገልጸውታል።

"በጣም ከፍተኛ ተኩስ ነው ያለው" የሚሉት እኚህ ነዋሪ፣ "ከባድ መሣሪያ" ጥቅም ላይ ውሏል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው፤ "ጥይት ከተጀመረ ዛሬ ሁለተኛ ቀን ነው፤ ትናንት [ሐሙስ] ንጋት አስር ሰዓት ነው የጀመረው። ማታ ሲታኮሱ አደሩ፤ ዛሬ [አርብ] ሌሊት ወደ አስራ አንድ ሰዓት መተኮስ ጀመሩ፣ እስካሁን ይኸው [አለ]" ብለዋል።

የተኩስ ልውውጡ "ከተማ ውስጥ" እየተደረገ መሆኑንም አክለው፤ "ተደብቀን በየጥጉ ጥጉ ቁጭ ብለን ነው። ምንም መፍትሄ የተበጀልን ነገር የለም" በማለት ያሉበትን ሁኔታ አረስድተዋል።

ሦስቱም ነዋሪዎች እንደሚናገሩት ሞያሌ ከተማ ውስጥ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች፣ መደብሮች እንዲሁም ሌሎች የንግድ ተቋማት ተቃጥለዋል።

አንድ ነዋሪ ቃጠሎውን ሲገልጹ፤ "ከተማ ላይ ምንም ሱቆችም የቀረ የለም። የተሰበረው ተሰብሯል፣ የተወደመው እንዳለ እሳት አሁን ከተማውን ግማሽ ክፍሉ ተቃጥሏል" ብለዋል።

ሌላ ነዋሪ ደግሞ "ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች ራሱ የተቃጠሉ አሉ። የድርጅት ኢምፖርት ኤክስፖርት የሚሠሩ መኪኖች ራሱ መስመር ላይ እየተመቱ ነው፤ ተመተው በየአስፋልቱ ቆመዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ቤታቸው እየተቃጠለ፣ ሱቃቸው እየተቃጠለ፣ ሁሉም በስደት ላይ ነው ያለው" ሲሉም አክለዋል።

የኬንያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዛሬ አርብ ጥቅምት 13/2019 ዓ.ም. ባጋራው መረጃ፣ ግጭት ሸሽተው ወደ ኬንያ ለገቡ ነዋሪዎች "መጠለያ፣ ድንኳን፣ ሸራዎችን እንዲሁም እንደ ብርድ ልብስ፣ መተኛ ምንጣፎች፣ ጄሪካን እና የማብሰያ ዕቃዎችን ያሉ አስፈላጊ" ቁሳቁሶችን እያቀረበ መሆኑን አስታውቋል።

ወደ ኬንያ ከሸሹት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መካከል አብዛኞቹ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ወጣቶች መሆናቸውን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ የአገሪቱን ቀይ መስቀል እና የአካባቢው አስተዳደርን ጠቅሶ ዘግቧል።

በኦሮሚያ እና ሶማሌ አዋሳኝ ስፍራ የተቀሰቀሰውን ግጭት በተመለከተ እስካሁን በክልል ደረጃም ሆነ ከፌደራል መንግሥት የተሰጠ አስተያየት የለም።