በቻይና ዝናብ ባስከተለ ከባድ አውሎ ነፋስ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቀሉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በቻይና በሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በተከሰተ ከባድ የአውሎ ነፋስ ማዕበል ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቀሉ።

ወደ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ወይም የፈረንሳይን ስፋት ያህል የሚያካልለው ከባድ አውሎ ነፋስ (ታይፎን ባቪ) መጀመሪያ ላይ የተከሰተው በባሕር ዳርቻዋ ታይዡ ከተማ ቅዳሜ ምሽት ነበር ።

ከዚያም ሌሊቱን በዌንዡ ከተማ ተከስቷል።

ዝናብ ያዘለው አውሎ ነፋስ የጃፓን ደሴቶችን መትቶ ካለፈ በኋላ በታይዋን ላይ ከባድ ዝናብ ያስከተለ ሲሆን በሰሜናዊ ክፍሏም የመሬት መንሸራተት አጋጥሟል።

ቀደም ሲል በፊሊፒንስ በተከሰቱ የመሬት መንሸራተቶች ቢያንስ 17 ሰዎች ሞተዋል።

ምንም እንኳን አውሎ ነፋሱ እየቀነሰ ቢመጣም እርጥበት ያዘለ ደመና ስላለ አሁንም አደጋ ያስከትላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

'ታይፎን ባቪ' የተባለው ከባድ አውሎ ነፋስ እሁድ ዕለት በምሥራቃዊ ዢጂያንግ እና በሰሜን ምሥራቅ ፉጂያን ግዛቶች የተለየ ከባድ ዝናብ እንደሚያስከትል መተንበዩንም ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ሊከሰቱ የሚችሉ አስከፊ አደጋዎችን ቀድሞ ለማስቀረት ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ነዋሪዎችን እያስወጡ እንደሆነ ባለሥልጣናቱ አክለዋል።

በዢጂያንግ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን በጎረቤት ግዛቶችም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀያቸውን ለቀው መውጣታቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በዢጂያንግ ትምህርት ቤቶች ፣ የሥራ እና ከቤት ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተከልክለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ 400 በረራዎች እና በርካታ የባቡር አገልግሎቶች ተሰርዘዋል።

10 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ የሚኖርባት ዌንዡ ከተማ አውሎ ነፋሱ ለሚያልፍበት መስመር ቅርብ በመሆኗ ባለሥልጣናት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን አስወጥተዋል።

ቤጂንግም በተፈጥሯዊ አደጋው ሊከሰት የሚችል አደጋን ለማስወገድ 100 ሺህ ሰዎች እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቷን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ባቪ የተባለው ማዕበል ከጉዋም እና ሰሜናዊ ማሪያና ደሴቶች በሰዓት 290 ኪሎሜትር ከሚነፍስ ነፋስ ጋር የተነሳው ባለፈው ሳምንት ሰኞ ነበር።

በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ሲያልፍ ፍጥነቱን ቀንሶ በሰዓት 144 ኪሎሜትር እየተጓዘ የነበረ ሲሆን በጃፓን ዋና ዋና ደሴቶች እና በታይዋን መካከል የሚገኙት ሪዩክዩ ደሴቶች ሰንሰለት አካል የሆነችውን ሳኪሽማ ደሴትን መትቷል።

ይህም ቢያንስ አምስት ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ ከኃይል አቅርቦት ውጭ ሆነዋል።

ታይዋን በማዕበሉ በቀጥታ ባትመታም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤታቸውን ለቅቀው ለመውጣት ተገድደዋል። ከባድ ዝናቡን ተከትሎም የመሬት መንሸራተት አጋጥሟታል። ሆኖም ጃፓንም ሆነች ታይዋን የሰዎች ሞት ሪፖርት አላደረጉም።

የታይዋን ባለሥልጣናት 'ባቪ' አንድ ሜትር ጥልቀት ያለው ጎርፍ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

በታይዋን በርካታ በረራዎች የተሰረዙ ሲሆን ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ነዋሪዎች ምግብ ቀድመው ፍጆታቸውን በማከማቸታቸው የሱፐር ማርኬት መደርደሪያዎችም ባዶ ሆነዋል።

የቻይና ደቡባዊ ክፍሎችም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ካጋጠማቸውና 'ታይፎን ሜይስክ' የተባለው ዝናብ ያዘለ አውሎ ነፋስ ካደረሰባቸው ጉዳት እስካሁን አላገገሙም።

ሜይስክ ቢያንስ 39 ሰዎችን እና በርካታ እንስሳትን የገደለ ሲሆን የእርሻ ሰብልም አውድሟል።

ከዚህም በተጨማሪ በማዕከላዊ ሁቤ ግዛት "ሁለት ብዙም ያልተለመደ ከባድ አውሎ ነፋስ " አስከትሏል።