ቀጥታ, የኢራን ጠቅላይ መሪ ለአባታቸው ግድያ “የበቀል እርምጃ” እንደሚወሰድ ተናገሩ

የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ በጽሑፍ ባስተላለፉት መልዕክት አባታቸው ላይ ለተፈጸመው ግድያ “የበቀል እርምጃ” መወሰድ እንዳለበት አሳስበዋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ኢራን ግድያ ልትፈጽምባቸው የምትሞክር ከሆነ ከፍተኛ ጥቃት እንደሚደርስባት ዝተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

  • ትራምፕ "የተኩስ አቁሙ አብቅቷል" ካሉ በኋላ ዛሬ ምሽት በድጋሚ በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት እንደሚፈፅሙ ዛቱ
  • መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዳያቋርጡ ማሳሰቢያ ተሰጠ
  • በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦች መመታታቸውን ተከትሎ አሜሪካ ኢራን ላይ ጥቃት ከፈተች
  • ኢራን በ85 የአሜሪካ ዒላማዎች ላይ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች
  • የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት በሶርያ ጉብኝት ላይ ሳሉ በደረሰ ፍንዳታ 18 ሰዎች ተጎዱ
  • ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ላይ ላለመተኮስ በይፋ ቃል እንድትገባ አሜሪካ ጠየቀች
  • ትራምፕ፤ ኢራን ልትገድላቸው ከሞከረች ከፍተኛ ጥቃት እንደሚፈጸምባት ተናገሩ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኢራን ጠቅላይ መሪ ለአባታቸው ግድያ “የበቀል እርምጃ” እንደሚወሰድ ተናገሩ

    የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ በጽሑፍ ባስተላለፉት መልዕክት አባታቸው ላይ ለተፈጸመው ግድያ “የበቀል እርምጃ” መወሰድ እንዳለበት አሳሰቡ።

    የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት በከፈቱበት የመጀመሪያው ቀን መገደላቸው ይታወሳል።

    የአባታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለተገኙ ሰዎች ምስጋና ያቀረቡት ሞጅታባ ኻሜኒ “ንጹህ ደምን ለመበቀል ቃል እንገባለን” ብለዋል።

    “ወንጀለኛ እና የተዋረዱ ገዳዮች በከፈቷቸው ሁለት ጦርነቶች ለተገደሉ ሰማዕታትም የበቀል እርምጃ ይኖራል” ሲሉም አክለዋል።

    አዲሱ ጠቅላይ መሪ “ይህ በቀል የአገራችን ፍላጎት ነው። እንደምንፈጽመው ጥርጥር የለም” ብለዋል።

    የአባታቸው አያቶላህ ዓሊ ኻሜኒን ግድያ ተከትሎ አዲሱ ጠቅላይ መሪ ኃላፊነቱን ተረክበዋል።

    እስካሁን ድረስ በይፋ ያልታዩ ሲሆን በቪድዮ እና በድምጽም መልዕክት አላስተላለፉም።

    በአባታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ያልተገኙት ሞጅታባ ኻሜኒ መልዕክት የሚያደርሱት በጽሑፍ ብቻ ነው።

  2. ኢራን እና ኦማን ስለ ሆርሙዝ ወሽመጥ ሊወያዩ ነው

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከኦማን ባለሥልጣናት ጋር ለመወያየት ሙስካት መግባታቸው ተገለጸ።

    ኢራን እና ኦማን የሆርሙዝ ወሽመጥን ጨምሮ ቀጣናዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ውይይት እንደሚያደርጉም ተገልጿል።

    በኢስላማባድ ስምምነት አንቀጽ 5 መሠረት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል “ተገቢውን መተላለፊያ” ለማበጀት እንደሚወያዩ ተዘግቧል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይ በኢራን እና አሜሪካ መካከል ከፍተኛ ውጥረት አስከትሏል።

    የኳታር ልዑካን ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር ለመወያየት ወደ ቴህራን አምርተዋል።

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ፣ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር፣ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮም ወደ ኦማን እንደሚሄዱ የሚጠቁሙ መረጃዎች ወጥተዋል።

  3. ኢራን ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር አለመጠየቋን አስታወቀች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ፤ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር ጥያቄ አለማቅረቧን ተናገሩ።

    ነገር ግን ድርድር ለማድረግ ከቀጣናዊ አሸማጋይ የቀረበላቸውን ጥያቄ ተቀብለዋል። አሸማጋዮች ወደ ቴህራን አቅንተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

    “ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር አልጠየቅንም። ሆኖም ግን ሁልጊዜም ኃላፊነት ስለሚሰማን ቀጣናዊ አደራዳሪዎችን አሻፈረኝ አላልናቸውም” ብለዋል ቃል አቀባዩ።

    የመግባቢያ ሰነዱ ከተፈረመ ሳምንታት ብቻ ቢቆጠሩም “አሜሪካ ብዙ የስምምነቱን ክፍል መጣሷን” ተናግረዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድርድሩ እንዲቀጥል መስማማታቸውን ገልጸዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ድርድራቸውን ለመቀጠል መስማማታቸውን ትራምፕ ያሳወቁት ኳታር ከአሜሪካ ጋር በመቀናጀት አሸማጋዮችን ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር እንዲነጋገሩ ወደ ቴህራን ከላከች በኋላ ነው።

  4. ትራምፕ፤ ኢራን ልትገድላቸው ከሞከረች ከፍተኛ ጥቃት እንደሚፈጸምባት ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን ግድያ ልትፈጽምባቸው የምትሞክር ከሆነ ከፍተኛ ጥቃት እንደሚደርስባት ዛቱ።

    በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “አንድ ሺህ ሚሳዔሎች ኢራን ላይ አነጣጥረው እየጠበኩ ነው” በማለት ጽፈዋል።

    የኢራን መንግሥት የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ለመግደል ከሞከረ “ተጨማሪ አንድ ሺህ ሚሳዔሎች በፍጥነት እንደሚዘጋጁ” አስጠንቅቀዋል።

    “ኢራንን ሙሉ በሙሉ ለማውደም” ትዕዛዝ እንደተሰጠ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ የአሜሪካ ወታደሮች በተጠንቀቅ መቆማቸውን አክለዋል። የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክታቸውንም “አላህ ይመስገን” በሚል ጽሑፍ አጠናቀዋል።

    ኢራን ትራምፕን ለመግደል አሲራለች የሚል የስለላ መረጃ እስራኤል ለአሜሪካ አቀብላለች።

    በቀድሞው ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ትራምፕ እንዲገደሉ የሚጠይቁ መፈክፎች ታይተዋል፤ ተደምጠዋል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ፕሬዝዳንቱን ለመግደል መወጠኑን አስተባብሏል።

  5. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ላይ ላለመተኮስ በይፋ ቃል እንድትገባ አሜሪካ ጠየቀች

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደሚከፈት እና በወሽመጡ የሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደማታደርስ በይፋ ቃል እንድትገባ እንደምትፈልግ አሜሪካ አስታወቀች።

    የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ማንነታቸው ያልተገለጸ ባለሥልጣንን ጠቅሰው እንደዘገቡት፤ ቴህራን ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካሪዎች በግል በሰጠችው ማብራሪያ መርከቦች ላይ መተኮሷ ስህተት መሆኑን አምናለች።

    ኢራን ጥቃቱ የተፈጸመው ከቁጥጥር ውጭ በሆኑ ውስጣዊ ኃይሎች መሆኑን አስታውቃለች።

    ባለፉት ቀናት የተኩስ ልውውጥ ቢያደርጉም ሁለቱም ወገኖች ንግግራቸውን ለመቀጠል መስማማታቸውን ትራምፕ ተናግረዋል።

    ኢራን እና አሜሪካ የፈረሙት የመግባቢያ ሰነድ፤ ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ታደርጋለች።

    ከሰሞኑ የተነሳው ግጭት የመግባቢያ ሰነዱን ያፈረሰ መሆኑን ሁለቱም አገራት ገልጸዋል።

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል መስማማታቸውን የገለጹት ትራምፕ፤ ቀደም ሲል የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ግን ማብቃቱን ለቴህራን ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።

    ቴህራን በመሠረተ ልማቶቿ ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ አጸፋውን እንደምትመልስ አስጠንቅቃለች።

  6. ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ድርድር ለመጀመር መስማማታቸውን ገለጹ

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል መስማማታቸውን፤ ነገር ግን ቀደም ሲል የነበረው የተኩስ አቁም ማብቃቱን ለኢራን እንዳረጋገጡላቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ።

    "የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ድርድሩን እንድንቀጥል ጠይቀውናል። እኛም ይህንን ለማድረግ ተስማምተናል” በማለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    አክለውም "ነገር ግን አሜሪካ ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ማብቃቱን በማያሻማ ሁኔታ አሳውቃቸዋለች” ብለዋል።

    ለወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም ሁለቱ አገራት ከሳምንታት በፊት የመግባቢያ ስምምነት ደርሰው ግጭቱ ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም ካላፈው ማክሰኞ ጀምሮ አሜሪካ በከፈተችው ጥቃት ጦርነቱ ዳግም ተቀስቅሷል።

    አሜሪካ እና ኢራን ድርድራቸውን ለመቀጠል መስማማታቸውን ትራምፕ ያሳወቁት ኳታር ከአሜሪካ ጋር በመቀናጀት አሸማጋዮችን ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር እንዲነጋገሩ ወደ ቴህራን ከላከች በኋላ ነው።

    አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለሲኤንኤን እንደተናገሩት የትራምፕ አስተዳደር ስትራቴጂ በኢራን ላይ ጥቃት በመሰንዘር ግጭቱ እንዳይባባስ ጋብ በማድረግ ለዲፕሎማሲያዊ ጥረት በር መክፈት ነው።

  7. የኻሜኒ ድረ ገጽ የቀድሞውን ጠቅላይ መሪ የመቃብር ቦታ ምሥል ይፋ አደረገ

    የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ የኻሜኒ ድረ ገጽ የኢራንን እስላማዊ ሪፐብሊክ የቀድሞ መሪ የመቃብር ሥፍራን የሚያሳይ ምሥል ይፋ አደረገ።

    ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከሌሎች አራት የቤተሰብ አባሎቻቸው ጋር ሐሙ ዕለት በሰሜን ምሥራቅ ኢራን ውስጥ በምትገኘው ቅዱስ ከተማ ማሻድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገኙበት ተፈፅሟል።

    የቀድሞው ጠቅላይ መሪ በመጀመሪያው ቀን የእስራኤል እና የአሜሪካ የተቀናጀ ጥቃት የተገደሉት ከአራት ወራት በፊት ነበር።

    ከእርሳቸውም ጋር በርካታ የኢራን ወታደራዊ እና የፖለቲካ ባለሥልጣናት እንዲሁም ሴት ልጃቸው ቡሽራ ኻሜኒ፣ የልጅ ልጃቸው ዛህራ ሞሃመዲ፣ የልጃቸው ሞጅታባ ኻሜኒ ሚስት ዛህራ ሃዳድ እና የልጃቸው ሆዳ ኻሜኒ ባል ኢስባህ ኡል ሃዳ ባጌሪ ተገድለዋል።

    በቀድሞው ጠቅላይ መሪ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የአገራት መሪዎች እና ባለሥልጣናት የተገኙ ሲሆን እርሳቸውን የተካው ልጃቸው ሞጅታባ ኻሜኒ አልተገኘም።

    የኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት የተፈፀመው ፕሬዝደንት ትራምፕ "ተኩስ አቁሙ አብቅቷል" ካሉ በኋላ አሜሪካ በኢራን ላይ የከፈተችው ጥቃት ለሁለተኛ ቀን በቀጠለበት ጊዜ ነበር።

  8. ኢራን መሠረተ ልማቶቿ ከተመቱ በአሜሪካ እና በእስራኤል ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም አስታወቀች

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ግጭቱ ካገረሸ በኋላ በመሠረተ ልማቶቿ ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ አጸፋውን እንደምትመልስ እና እስራኤልም ከኢራን የአጸፋ ጥቃት እንደማትተርፍ የኢራን የብሔራዊ ደኅንነት የበላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አስጠነቀቁ።

    ዋና ፀሐፊው ሞሐመድ ባቂር ዞልቃድር በአገሪቱ ቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው "ቀደም ሲል እንዳስታወቅነው በመሠረተ ልማቶቻችን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች አጸፋን የሚያስከትሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ክፋቶች ጀርባ ያለው ወንጀለኛው ጽዮናዊ መንግሥትም ተዋጊዎቻችን ከሚፈጽሙት ጥቃት የሚያመልጥ አይሆንም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ተኩስ አቁም አድርገው የነበሩት አሜሪካ እና ኢራን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሚተላለፉ መርከቦች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ወደ ግጭት ተመልሰዋል።

    አሜሪካ፣ ኳታር እና ሳዑዲ አረቢያ በሦስት መርከቦች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ ሲያደርጉ ኢራን ግን አስተባብላለች።

    በመርከቦቹ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ አሜሪካ ከማክሰኞ ሌሊት ጀምራ ኢራን ውስጥ በሚገኙ በርካታ ዒላማዎች ላይ ጥቃት ስትፈጽም፣ ኢራን ደግሞ በፋርስ ባሕረ ሰላጤው አገራት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች።

  9. ሜክሲኮ በአሜሪካ ይዞታ ሥር ሆነው የሞቱ ዜጎቿን በተመለከተ ክስ ልትመሠርት ነው

    ሜክሲኮ በአሜሪካ ይዞታ ሥር እያሉ የሞቱ ዜጎቿን በተመለከተ የወንጀል ክስ እንደምትመሠርት አስታወቀች።

    የሜክሲኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮቤርቶ ቬልሳኮ እንደተናገሩት ብዙ ዜጎቻቸው በአሜሪካ ይዞታ ሥር ሳሉ በመሞታቸው “የሕግ እርምጃ” ይወስዳሉ።

    በአሜሪካ የስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን (አይስ) ተይዘው የነበሩ 14 የሜክሲኮ ዜጎች መሞታቸውን ገልጸዋል። ሦስት ተጨማሪ ዜጎቻቸው ደግሞ “በእስር ሒደት ላይ” መሞታቸውን ተናግረዋል።

    ሜክሲኳውያኑ መሞታቸው በአገሪቱ ካስነሳው ተቃውሞ በተጨማሪ ያለፈው ረቡዕ በአሜሪካ ሂዩስተን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተቃውሞ ሰልፍ አድገዋል።

    የተቃውሞ ሰልፍ ከመካሄዱ አንድ ቀን አስቀድሞ ሎሬንዞ ሳልጋዶ አሩጆ የተባለ የሜክሲኮ ዜጋ በስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ባልደረባ ተገድሏል።

    የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት (ዲኤችኤስ) በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ “አይስ [የስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን] ሕገ ወጥ ሰውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ መኪና ለማስቆም ሞክሯል” ብሏል።

    ግለሰቡ የተገደለው “ከመያዝ ለማምለጥ ሲሞክር” እንደሆነም ገልጿል።

    ቤተሰቦቹ እንዳሉት ግን ሎሬንዞ ተተኩሶበት የተገደለው ወደ ሥራ እየሄደ ሳለ ነው።

  10. በስፔን ሰደድ እሳት ቢያንስ 11 ሰዎች ሲሞቱ፣ 19 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም

    በደቡብ ስፔን፣ አንዳሉሲያ ግዛት በተነሳው ሰደድ እሳት ምክንያት ቢያንስ 11 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

    የግዛቱ አስተዳዳሪ ጁአናማ ሞሬኖ እንዳሉት 19 ሰዎች እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም።

    በወደቀ የኤሌክትሪክ መስመር ምክንያት ሰደድ እሳቱ እንደተነሳ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስርጭቱን ለመቆጣጠር እየሞከሩ እንደሚገኙ ተገልጿል።

    በደቡብ አውሮፓ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስ የሙቀት ወጀብ መከሰቱ በተለያዩ አካባቢዎች ሰደድ እሳት እያስከተለ ነው።

    በፈረንሳይ፣ ፖርቹጋል እና ስፔን የእሳት አደጋ ሠራተኞች አደጋዎችን ለመቆጣጠር እየሞከሩ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

    በስፔን በሰደድ እሳት የሞቱ 11 ሰዎች አስከሬን ቤዳር በተባለች አነስተኛ መንደር ውስጥ ተገኝቷል። አብዛኞቹ ሰዎች የውጭ አገራት ዜጎች መሆናቸውን የግዛቱ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።

  11. ቻይና በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል ሮኬት አስወነጨፈች

    ቻይና በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ሮኬት ማስወንጨፏ ተገለጸ።

    በአገሪቱ የሕዋ ሳይንስ ዘርፍ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ተመልክቷል።

    ዛሬ አርብ፤ ሎንግ ማርች 10ቢ የተባለው ሮኬት ከደቡባዊ ቻይና ሀይናን ተወንጭፎ ወደ ምድር መመለሱ ተገልጿል።

    አሜሪካ በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሮኬቶች በማምረት በሕዋ ሳይንስ ያላትን ሥፍራ ቻይና መገዳደር የምትችልበት መንገድ ነው።

    የኢሎን መስክ ‘ስፔስ ኤክስ’ እና የጄፍ ቤዞስ ‘ብሉ ኦሪጅን’ እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ ሮኬቶች ያመርታሉ።

    ሮኬቶች አንዴ ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ መልሰው አገልግሎት እንደማይሰጡ ይታመናል።

    ከምድር ሮኬቶች ሲወነጨፉ ጉዳት ስለሚደርስባቸው እና በድጋሚ ጥቅም ላይ ስለማይውሉ የጠፈር መንኮራኩር መላክ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል።

    ሮኬቶችን ለማስወንጨፍ የሚያስችለው ክፍል ዳግመኛ ጥቅም ላይ እንዲውል ማስቻል በከፍተኛ መጠን ወጪውን ይቀንሳል።

  12. የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከአሜሪካ ጋር በማበሯ ዋጋ ትከፍላለች - ኢራን

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለወራት ጥቃት እየፈጸመች ካለችው አሜሪካ ጋር የምታደርገው ትብብር ዋጋ ያስከፍላትል ሲሉ አንድ የኢራን የምክር ቤት አባል ተናገሩ።

    በኢራን ፓርላማ ውስጥ የብሔራዊ ደኅንነት ኮሚሽን አባል የሆኑት ኢስማኤል ኮዋሳሪ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አሜሪካ በአገራቸው ላይ እንደ አዲስ ከከፈተችው ጥቃት ጀርባ አለች ሲሉ ከስሰዋል።

    በዚህም ምክንያት አሜሪካ እየፈጸመችው ላለው ጥቃት ኤምሬትስ “ከዋሽንግተን ጋር ባላት ትብብር የተነሳ ዋጋ ትከፍላለች” ሲሉ የባሕረ ሰላጤዋን አገር አስጠንቅቀዋል።

    አስማኤል በተጨማሪም በኢራን ላይ እየተፈጸመ ካለው ጥቃት ጋር በተያያዘ "እየወሰደችው ባለቻቸው እርምጃዎች የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከኢራን ጠላቶች ጋር ተሰልፋለች፤ ለዚህም የሚያስከፍላት ዋጋ በጣም ከባድ እንደሚሆን ልታውቀው ይገባል” ብለዋል።

    የኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ቀደም ሲል እንዳስታወቁት “ለወራሪ” ኃይሎች ማንኛውንም ድጋፍ የሚሰጥ ከኢራን የአጸፋ ቅጣት ይጠብቀዋል በማለት ያስተላለፉትን ማስጠንቀቂያ የምክር ቤት አባሉ አጽንኦት ሰጥተው ጠቅሰዋል።

    ስለዚህም ኤምሬትስ በቀጣናው ያሉትን ለአሜሪካ ጦር ሰፈሮች በምትሰጠው ድጋፍ ምክንያት “የባሕር እንቅስቃሴ መስመሯ፣ የባቡር እና የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማቶቿ እንዲሁም የነዳጅ እና የጋዝ ተቋማቷ የኢራን ጦር ሠራዊት እርምጃ በሚወስዱበት ጊዜ ዋነኛ ዒላማዎች ይሆናሉ” በማለት አስጠንቅቀዋል።

  13. ‘ዶናልድ ትራምፕን ለመግደል አዲሱ የኢራን ዕቅድ’

    ኢራን ከወራት በፊት በተከፈተባት ጦርነት ጠቅላይ መሪዋን እና ከፍተኛ ባለሥልጣናቷን የገደሉባትን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለመበቀል አዲስ ዕቅድ ማውጣቷ ተዘገበ።

    ኢራን በፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ ግድያ ለመፈጸም አዲስ ዕቅድ ማዘጋጀቷን በተመለከተ እስራኤል ለአሜሪካ መረጃ መስጠቷን ዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ዘግቧል።

    "የአሜሪካን መሪ፣ እኔን ሊገድሉ ይፈልጋሉ” እና “ስሜ በሁሉም ዝርዝራቸው ውስጥ ይገኛል” በማለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ መረጃው እንዳሳሰባቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጉዳዩን በይፋ አንስተው በተደጋጋሚ መናገራቸውን እንደሚያመልክት ጋዜጣው ዘግቧል።

    እስራኤል የኢራንን ዕቅድ በተመለከተ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ የሰጠችው መረጃ ከሁለት ዓመት በፊት ፔንሲልቬኒያ ውስጥ የተደረገባቸውን የግድያ ሙከራ የሚያካትት ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱም መረጃውን ከደኅንነት ስጋት ባሻገር ለፖለቲካ ዓላማቸው እየተጠቀሙበት መሆኑን አመልክቷል።

    የትራምፕ ተቺዎች መረጃውን ትራምፕ ከሕዝቡ ድጋፍ ለማግኘት የሚጠቀሙበት ነው ቢሉም፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በቀድሞው የትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በነበሩት ጆን ቦልተን ላይ አድርጎታል የተባለው የግድያ ሙከራ በትራምፕም ላይ ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

    ከአውሮፓውያኑ 1950 ወዲህ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ላይ ከተፈጸመው ግድያ አንስቶ በትሩማን፣ በፎርድ እና በሬጋን ላይ ያልተሳኩ የግድያ ሙከራዎች ተፈጽመዋል።

    አንዳንዶች የግድያ ሙከራዎች የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት ጥቅም ላይ ይውላል ቢሉም ፕሬዝዳንት ትሩማን እና ፎርድ ከተሞከረባቸው ግድያ በኋላ በሕዝብ ዘንድ የነበራቸው ተቀባይነት ሲያሽቆለቁል፣ ሮናልድ ሬጋን ግን ከተሞከረባቸው ግድያ በኋላ ተቀባይነታቸው ጨምሯል።

  14. ኢራን እና አሜሪካ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት መጀመሩ ተዘገበ

    ኳታር፣ ፓኪስታን እና ሌሎችም ቀጣናዊ አደራዳሪዎች አሜሪካ እና ኢራንን ወደ ውይይት ለመመለስ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ተዘገበ።

    የአሜሪካው አክሲዮስ እንደዘገበው አሸማጋዮቹ አሜሪካ እና ኢራን እንደ አዲስ የገቡበትን ግጭት አቁመው ኒውክሌርን የተመለከተ ውይይት እንዲቀጥሉ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።

    አክሲዮስ በአሜሪካ እና በአሸማጋዮቹ አገራት የሚገኙ ሁለት ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ውይይቶች እንዲቀጥሉ ጥረቶች ተጀምረዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከትናንት በስትያ ከኢራን ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ እንዲሁም የተኩስ አቁሙ “አብቅቶለታል” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በኢራን ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ሁለቱ አገራት ወደ ግጭት ተመልሰዋል።

    ትራምፕ ትኩረታቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን ማስከፈት መሆኑን ተናግረዋል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ የሆርሙዝ ወሽመጥ በአገሪቱ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ ገልጿል።

    አክሲዮስ እንደዘገበው ትራምፕ አሁንም ቢሆን የለየለት ጦርነት ውስጥ ተመልሰው መግባት አይፈልጉም።

    የአሜሪካ ጦር ለሁለት ተከታታይ ቀናት በፈጸመው ጥቃት በኢራን ወደ 90 ዒላማዎችን መምታቱን አስታውቋል። የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በኩዌት፣ በባሕሬን እና በኳታር የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የድሮን ድብደባ መፈጸሙን ገልጿል።

  15. የአሜሪካ እና ኢራን ግጭት ዋና ዋና ክስተቶች

    አሜሪካ እና ኢራን ወደ ጦርነት መመለሳቸው መካከለኛው ምሥራቅን በውጥረት ሞልቶታል።

    በሁለቱ አገራት መካከል የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ ከባድ የተኩስ ልውውጥ የተደረገው ያሳለፍነው ማክሰኞ ነው።

    የኢራን የጤና ሚኒስቴር ማክሰኞ እና ረቡዕ በተፈጸሙ ጥቃቶች 14 ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጧል።

    ረቡዕ እና ዛሬም ተከታታይ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል። የግጭቱ ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦

    • የአሜሪካ ጦር ለሁለት ተከታታይ ቀናት በፈጸመው ጥቃት በኢራን ወደ 90 ዒላማዎችን መምታቱን አስታውቋል።
    • የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ ቢቢሲ ቬሪፋይ ያረጋገጣቸው ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በደቡብ ምሥራቅ ኢራን ቻባሀር ከተማ የመቆጣጠሪያ ማማ ላይ የደረሰ ጉዳትን ያሳያሉ።
    • በሰሜናዊ የኢራን ክፍል አቃላ ከተማ የባቡር ሃዲድ በተዘረጋበት ድልድይ ላይ ጉዳት መድረሱንም ማረጋገጥ ተችሏል።
    • የኢራን መገናኛ ብዙኃን የኒውክሌር ማብላያ ላይ ዛሬ ከሰዓት ጥቃት መፈጸሙን ዘግበዋል።
    • ኢራን በኩዌት፣ በባህሬን እና በኳታር የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የድሮን ድብደባ መፈጸሟን አስታውቃለች።
    • ባህሬን ከኢራን የተሰነዘሩባትን ጥቃቶች ማክሸፍ መቻሏን ስትገልጽ፤ በኩዌት በተተኮሰ የሚሳዔል ስብርባሪዎች አንድ ሰው ላይ ጉዳት መድረሱ ይፋ ተደርጓል።
    • የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በዮርዳኖስ የሚገኝ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈር ላይ 10 ሚሳዔል መተኮሱን ገልጿል። ዮርዳኖስ በበኩሏ ስምንት ሚሳዔሎችን መትታ መጣሏን አስታውቃለች።
  16. የአሜሪካ ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ ኢራን እራሷን እንደምትከላከል አስታወቀች

    ለተከታታይ ሁለት ቀናት በአሜሪካ ጥቃት የተሰነዘረባት ኢራን ጥቃቱ የሚቀጥል ከሆነ እራሷን የመከላከል እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች።

    የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ባወጡት መግለጫ አሜሪካ በተከታታይ በተለያዩ የኢራን ክፍሎች ላይ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት “በጽኑ የሚወገዝ” መሆኑን አመለክተዋል።

    ጥቃቶቹን ከሳምንታት በፊት ባለፈው ሰኔ ወር በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰውን ባለ 14 ነጥብ የመግባቢያ ስምምነትን የሚጥስ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰውን ስምምነት ዋነኛ አሸማጋይ ለሆኑት ለፓኪስታኑ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ለሆኑት ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር እንደተናገሩት “የአሜሪካ ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ ኢራን እራሷን ትከላከላለች” ብለዋል።

    በተጨማሪም አራግቺ ከኦማን እና ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር መወያየታቸው የተነገረ ሲሆን፣ አገራት በባሕረ ሰላጤው የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

  17. አሜሪካ እና ኢራን ወደ ጦርነት ሲመለሱ፣ ኢራናውያን አደባባይ ወጥተው የኻሜኒን ቀብር እየፈጸሙ ነው

    አሜሪካ በኢራን ላይ ለሁለተኛ ቀን የምትፈጽመው ጥቃት በቀጠለበት እና ኢራን የአጸፋ እርምጃ በጎረቤቶቿ ላይ እየወሰደች ባለበት በአሁኑ ጊዜ በጦርነቱ ጅማሬ ላይ የተገደሉት የቀድሞው ጠቅላይ መሪ የመጨረሻ የቀብር ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።

    ላለፉት ቀናት በተለያዩ አገራት እና ከተሞች ውስጥ ሲዘዋወር የነበረው የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ወደ ትውልድ ከተማቸው ማሻድ ተወስዶ ዛሬ ግብአተ መሬቱ ይጠናቀቃል።

    በሰሜን ምሥራቃዊ ኢራን ውስጥ በምትኘው ቅዱስ ከተማ ማሻድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አደባባይ ወጥተው ጎዳናዎች በሐዘንተኞች መጨናነቃቸው ተዘግቧል።

    የካቲት ወር ማብቂያ ላይ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት በከፈቱበት የመጀመሪያ ዕለት የተገደሉት ኻሜኒ የስንብት እና ቀብር ሥነ ሥርዓት ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ የሚጠናቀቅ ይሆናል።

  18. የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሆርሙዝ ወሽመጥ በቁጥጥሩ ሥር መሆኑን አስታወቀ

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሆርሙዝ ወሽመጥ በአገሪቱ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ አስታወቀ።

    የሆርሙዝ ወሽመጥን ደኅንነት “በቁጥጥሩ ሥር እንዳዋለ” እና በቀጣይ ሁለት ሳምንታት “ቀስ በቀስ” መተላለፊያው እንደሚከፈት ይፋ አድርጓል።

    ለኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቅርብ የሆነው ታስኒም የዜና ምንጭ እንደዘገበው፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለው እንቅስቃሴ ከጦርነቱ በፊት ከነበረው አንጻር “ወደ 50 በመቶ እንደሚደርስ" ተገልጿል።

    ከኢራን “ፈቃድ ያገኙ” መርከቦች እንቅስቃሴ “እየጨመረ” መሆኑን አስታውቋል።

    “የውጭ ኃይሎች በዚህ መሬት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መብት እንደሌላቸው በድጋሚ እንገልጻለን” ሲል የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ተናግሯል።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ጣልቃ መግባት “አውዳሚ ምላሽ የሚያስከትል” ነው ሲልም አስጠንቅቋል።

    የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ ቢቢሲ ቬሪፋ ባገኘው መረጃ መሠረት ትናንት ረቡዕ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል 23 መርከቦች አልፈዋል።

  19. ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ አሜሪካ “ግልጽ ጥሰት” ፈጽማለች ስትል አሜሪካን ከሰሰች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት አሜሪካ ሰኔ ላይ የተፈረመው እና ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ያስገኘው የመግባቢያ ስምምነት ክፍሎች ላይ “ግልፅ ጥሰት” ፈጽማለች ሲል ከሰሰ።

    “ወታደራዊ ዘመቻዎች በአስቸኳይ እና በቋሚነት እንዲቆሙ” የጠየቀው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፤ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል “የሚደረግ የንግድ መርከቦች ጉዞን ደኅንነት ለማስጠበቅ የተቻላትን እንደምታደርግ” ገልጿል።

    ሁለቱ ወገኖች የመግባቢያ ስምምነቱን የሚተረጉሙበት መንገድ የዚህ ግጭት ቁልፍ የውጥረት ምንጭ ሆኗል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ አሜሪካ በወሽመጡ “ትዕዛዝ ባላከበሩ በርካታ መርከቦች ጋር ተፈጽሟል ለተባለ ክስተት” ምላሽ እሰጣለሁ በሚል “ሐሰተኛ ምክንያት” ጥቃት እንደፈጸመች በመግለጽ ከስሷል።

    አሜሪካ ከዚህ ቀደም ኢራን በወሽመጡ የሚጓዙ ሦስት መርከቦች ላይ ጥቃት በመፈጸም “የተኩስ አቁሙ ላይ ግልጽ ጥሰት” ፈጽማለች የሚል ክስ አቅርባ ነበር። ኢራን መርከቦቹ ላይ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን አልወሰደችም።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አክሎም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን መሪዎች “ዋልጌ” በማለት “ያልተገራ ንግግር” አድርገዋል በማለት ወቅሷል።

    በተጨማሪም አሜሪካ ሁለት የባቡር ድልድዮችን ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን ዒላማ በማድረግ "ከባድ የጦርነት ወንጀል" ፈጽማለች ሲል ከስሷል።

  20. በአሜሪካ የሁለት ቀናት ጥቃቶች 14 ሰዎች መገደላቸውን ኢራን ገለጸች

    አሜሪካ ማክሰኞ እና ረቡዕ ዕለት ኢራን ውስጥ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች 14 ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም 78 ሰዎች መቁሰላቸውን የአገሪቱ የጤና እና ህክምና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ከሳምንታት በፊት የተኩስ አቁም እንዲደረስ ያደረገው የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው የነበሩት አሜሪካ እና ኢራን ከማክሰኞ አንስቶ በተከታታይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው።

    አሜሪካ ማክሰኞ ዕለት ጥቃት የፈጸመችው በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲጓዙ በነበሩ ሦስት ጭነት መርከቦች ተመትተዋል በሚል ነበር። ኢራን በምላሹ የባሕረ ሰላጤው አገራትን አጥቅታለች። ይህ የጥቃት ምልልስ ትናንትም ረቡዕ ሌሊትም ቀጥሏል።

    አሜሪካ ማክሰኞ እና ረቡዕ ዕለት በኢራን አምስት ግዛቶች ውስጥ ጥቃት መፈጸሟን የኢራን የጤና እና ህክምና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆስኒ ኬርማንፑር ገልጸዋል።

    በእነዚህ ጥቃቶች 14 ሰዎች ተገድለው፤ 78 ሰዎች እንደሰቆሉ ኃላፊው በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል። ከቆሰሉት ውስጥ 47 ያህሉ አሁንም ሆስፒታል ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    በደቡባዊ ኢራን የሚገኘው ኢራንሻህር ግዛት ገዥ በበኩላቸው አሜሪካ የአየር ማረፊያ ሕንጻ ላይ በፈጸመችው ጥቃት አንድ ሰው መገደሉን አስታውቀዋል።