ኢራን በድጋሚ ሆርሙዝ ወሽመጥን ስትዘጋ፤ አሜሪካ ቴህራን ላይ አዲስ ዙር ጥቃት ከፈተች
ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችን መምታቷን ተከትሎ አሜሪካ ቴህራን ላይ አዲስ ዙር ጥቃት ከፈተች።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ፤ ቀጣይ መግለጫ እስከሚሰጥ ድረስ ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ ተዘግቶ እንደሚቆይ አስታውቋል።
ለአሜሪካ “ጥቃትም” ከባድ ምላሽ እንደሚሰጥ መግለጹን የኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
አብዮታዊ ዘቡ፤ ዋሽንግተን ጥቃት በፈጸመች በሰዓታት ልዩነት በዮርዳኖስ የሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር መምታቱን ገልጿል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ኳታር፣ ኩዌት እና ባህሬን በበኩላቸው ከኢራን ለተተኮሱባቸው ሚሳዔሎች እና ድሮኖች ምላሽ እየሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል።
ጋብ ብሎ የነበረው የሁለቱ አገራት ጦርነት በድጋሚ የተቀሰቀሰው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በሦስት ነዳጅ ጫኝ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ነው።
ለዚህ ጥቃት ምላሽ የሰጠችው አሜሪካ ኢራንን ከደበደበች በኋላ የጥቃት ልውውጡ አገርሽቷል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ በዚህ ሳምንት ሦስተኛ ዙር ጥቃት የከፈተው የኢራን አብዮታዉ ዘብ የቆጵሮስ ሰንደቅ ዓላማን እያውለበለበ በሆርሙዝ ወሽመጥ ይጓዝ የነበረ መርከብን "በግልጽ ስላጠቃ" እንደሆነ ገልጿል።
'ኤምቪ ጂኤፍኤስ ጋላክሲ' የተባለው መርከብ የሞተር ክፍሉ ላይ በደረሰው ከፍተኛ ጉዳት የተነሳ “ጉዞውን መቀጠል እንዳልቻለ” ማዕከላዊ ዕዙ አስታውቋል። አንድ ሲቪል የመርከብ ሠራተኛ መጥፋቱንም ገልጿል።
እንደ ዕዙ ገለጻ ኢራን ላይ በተፈጸመው ጥቃት የሚሳዔል እና ድሮን ሠፈሮች፣ የኮሚዩኒኬሽን ኔትዎርኮች እንዲሁም የባሕር ኃይል የክትትል ሥፍራዎችን ጨምሮ 140 የቴህራን ወታደራዊ ዒላማዎች ተመትተዋል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ የአሜሪካ ጥቃት "ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ ላይ የሚገኙ በርካታ የባሕር ዳርቻ የጦር ሰፈሮችን እና የቴሌኮሚዩኒኬሽን ማማዎችን" ዒላማ ማድረጉን አስታውቋል።
ለዚህ ጥቃት በተሰጠው “የመጀመሪያ ዙር” ምላሽ፤ ዮርዳኖስ ውስጥ የሚገኘውን ‘ፕሪንስ ሀሰን’ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር እንዲሁም ሌሎች ዒላማዎችን መምታቱን ገልጿል። እንደ ኢራን ገለጻ በጥቃቱ የጦር ሰፈሩ የዕዝ እና ቁጥጥር ማዕከል እንዲሁም የኤምኪው9 ድሮን ማቆሚያዎች ወድመዋል።
ከዚህ አስቀድሞ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን የአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ዘገባዎቹ እንደሚያስረዱት መተላለፊያው የተዘጋው የኢራን ጦር ባልተፈቀደ መስመር ለመጓዝ በሞከረ መርከብ ላይ ክሩዝ ሚሳዔል ካስወነጨፈ በኋላ ነው።
እንደ አብዮታዊ ዘቡ ገለጻ፤ መርከቡ የተሰጡትን ትዕዛዞች በተደጋጋሚ ችላ በማለቱ “በማስጠንቀቂያ ተኩስ እንዲመታ እና እንዲቆም” ተደርጓል።
ሆርሙዝ በመዘጋቱ ምክንያት ለሚፈጸም ማንኛው የአሜሪካ “ጥቃት”፤ የሚሰጠው ምላሽ “ከባድ” እንደሚሆን እና በቀጣናው የሚገኙ አዲስ የጦር ሰፈሮች ዒላማ እንደሚደረጉ አስጠንቅቆ ነበር።