ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በበይነ መረብ የተዋወቃቸውን 14 ሴቶች አደንዝዞ በመድፈር የተጠረጠረው ጀርመናዊ ተከሰሰ
ማሳሰቢያ፡ ይህ ጽሑፍ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሽ የሚችል ይዘት አለው
የጀርመን ዐቃቤ ሕግ የ68 ዓመት ተጠርጣሪን 14 ሴቶችን አደንዝዞ በመድፈር ከሰሰ።
ተጠርጣሪው የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት በሚያስችሉ መተግበሪያዎች አማካኝነት የተዋወቃቸውን ሴቶች አደንዝዞ እንደደፈረ እና ድርጊቱንም ቪድዮ እንደቀረጸ ተገልጿል።
የበርሊን ዐቃቤ ሕግ ቢሮ እንዳለው ተጠርጣሪው ከ14 ሴቶች ጋር በተያያዘ በ22 የመድፈር ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን አጠቃላይ የደፈራቸው ሴቶች 58 ናቸው።
ምርመራ የተከፈተው በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2025 ነበር። ፖሊስ ምርመራ እያደረገበት ካለ ሌላ ግለሰብ ጋር በበይነ መረብ ሲነጋገር ተጠርጣሪው ተደርሶበታል።
ፖሊስ እየተከታተለው የነበረው ሌላኛው ግለሰብ ሞቷል። የ68 ዓመቱ ተጠርጣሩ ቤት ላይ አምና ፍተሻ ተደርጓል።
ከወራት በኋላ በፎረንሲክ ምርመራ ወሲባዊ ጥቃትን የሚያሳዩ ቪድዮዎች ተገኝተዋል።
ከመጋቢት 2026 ጀምሮ በቁጥጥር ሥር የሚገኘው ተጠርጣሪው ስለቀረቡበት ክሶች አስተያየት እንዳልሰጠ ዐቃቤ ሕግ ተናግሯል።
በበይረ መረብ የተዋወቃቸውን ሴቶች አልኮል መጠጥ እና ማደንዘዣ በመስጠት እንደደፈራቸው ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ዐቃቤ ሕግ ቪድዮዎቹን እስከሚያሳያቸወ ድረስ ሴቶቹ መደፈራቸውን አላወቁም ነበር።
በቪድዮ ላይ ከሚታዩት 58 ሴቶች መካከል 30 የሚሆኑን ማንነታቸውን መለየት ተችሏል። የተቀሩት 10 ሴቶች ማንነት ላይ ምርመራ እየተደረገ ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት የ32 ዓመት ቻይናዊ ዶክተር በመድፈር ወንጀል የአምስት ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።
ሴቶችን አደንዝዞ ስለመድፈር የሚነጋገሩ ሰዎች የበይረ መረብ ቡድን አባል መሆኑን የበርሊን ፍርድ ቤት ለማወቅ ችሏል።
የ32 ዓመቱ ዶክተር እንዴት ሴቶችን አደንዝዞ መድፈር እንደሚቻል ምክር ሲሰጥም ነበር።
ዳኛው "ወሲባዊ ጥቃት በድብቅ የሚፈጸም መሆኑ ቀርቷል። በበይነ መረብ በይፋ የሚነገር እና የሚያስመሰግን ድርጊት ሆኗል" ብለዋል።
የ68 ዓመቱን ተጠርጣሪ በተመለከተ ዐቃቤ ሕግ ከ2010 እስከ 2014 ድረስ አንድ ሴት ላይ ያደረሰውን 36 የመድፈር ወንጀል ወደ ፍርድ ቤት እንደማይወስድ አስታውቋል። ለዚህም ምክንያቱ ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ ለፍርድ መቅረብ ያለበት የአምስት ዓመት ጊዜ ገደብ በማለፉ ነው።
22 የመድፈር ክሶች በማስገደድ የተፈጸሙ ስለሆኑ ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ እስከ 20 ዓመት ድረስ ፍርድ መቅረብ ይችላል።
የጀርመን የፍትሕ ሚኒስትር ስቴፋኒ ሁቢግ ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ ለፍርድ መቅረብ ያለበት ጊዜ ገደብ ወደ 20 ዓመት መራዘም አለበት ብለዋል።
በማደንዘዝ የሚደፍሩ ወይም የሚዘርፉ ወንጀለኞች ቢያንስ በአምስት ዓመት እስራት መቀጣት እንዳለባቸውን ተናግረዋል።
ሴቶችን ለመድፈር መጠጥ ላይ የሚጨመሩ ማደንዘዣ መድኃኒቶች (date-rape drugs) "አደገኛ" መሆናቸውን የጀርመን ፍርድ ቤት ከሁለት ዓመት በፊት ወስኗል።
በዚህ መሠረት አነስተኛው ቅጣት የሦስት ዓመት እስራት እንደሚሆን የፍትሕ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
አዲስ በቀረበው የሕግ ማሻሻያ መሠረት "ወሲባዊ ጥቃት ወይም ዝርፊያ ለመፈጸም ጥቅም ላይ የሚውሉ አደገኛ መድኃኒቶች" በሌሎች የመሣሪያ ዓይነቶች ዝርዝር ውስጥ ይካተታሉ።