ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንዲት ሴት በተመሳሳይ ወቅት እንዴት ከሁለት ወንዶች ልታረግዝ ትችላለች?
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2018 አንዲት እናት የመንታ ልጆቿን አባት ለማወቅ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ኮሎምቢያ ወደሚገኘው የዲኤንኤ ምርመራ ማዕከል አመራች።
ማዕከሉ የተለመደውን ናሙና ወስዶ ከመረመረ በኋላ ባገኘው ውጤት ስለተገረመ በድጋሚ ምርመራ አደረገ። ውጤቱ ስላለስገረማቸው እርግጠኛ መሆን ፈልገው ነበር።
መንትዮቹ ከአንድ እናት ቢወለዱም አባታቸው ግን የተለያየ ነበር።
ይህ አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ክስተት 'ሄትሮፓተርናል ሱፐርፌክዩንድ' (heteropaternal superfecundation) ይሰኛል።
በዩኒቨርስቲው ያሉት ባለሙያዎች ይህ ሊሆን እንደሚችል ቢያውቁም በተግባር ግን አጋጥሟቸው አያውቅም። ለዚያም ነው ወዲያውኑ ሳይንሳዊ ፍተሻ ለማካሄድ ፍላጎት ያሳዩት።
እንዴት አገኟት
በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የጄኔቲክስ ተቋም ውስጥ የሚሰሩ ተመራማሪዎች የአባትነት ምርመራ ለማድረግ 'ማይክሮሳተላይት ማርከርስ' የሚባል ቴክኖሎጂ ይጠቀማሉ።
በቀላል አነጋገር ይህ ከልጁ፣ ከእናትየው እና ከአባትየው የተወሰዱትን ጥቃቅን የዲኤንኤ ቅንጣቶች መተንተን እና ማወዳደርን ያካትታል።
"ከእያንዳንዱ ሰው ዲኤንኤ እንወስዳለን። ማይክሮሳተላይት የሚባሉትን ከ15 እስከ 22 ነጥቦች እንመረምራለን። እና አንድ በአንድ እናወዳድራቸዋለን" ሲሉ የላብራቶሪው ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዊሊያም ኡሳኩዌን ለቢቢሲ ሙንዶ ተናግረዋል።
ነገር ግን ሂደቱ ዲኤንኤ በማይክሮስኮፕ ስር ከማስቀመጥ የበለጠ ውስብስብ ነው።
ሳይንቲስቶች የደም ናሙናዎችን ከጣት ጫፍ ከወሰዱ በኋላ፣ ትንሹን የዲኤንኤ ቅንጣት ከሌሎች ክፍሎች ለመለየት የሚያስችል ኬሚካል ይጠቀማሉ።
ከዚያም ዲኤንኤውን ለማጉላት በልዩ መሳሪያዎች ላይ ያስቀምጣሉ።
የሚፈጠረውን ፈሳሽ ከሚያጎላ ኬሚካል ጋር በመደበላለቅ (ፍሎረሰንት ዳይስ) የተወሰነውን ዲኤንኤ በመተንተን ከ15 እስከ 22 የማይክሮሳተላይት ነጥቦችን ምልክት ያደርጋሉ።
ከዚያም በእያንዳንዱ ናሙና ውስጥ ያሉትን ማይክሮሳተላይቶች የሚያነብ እና ወደ ቁጥራዊ ቅደም ተከተል የሚቀይራቸው ሌላ ማሽን ውስጥ የሚያስገቡት ሲሆን ይህ ሂደት ኤሌክትሮፎረሲስ በመባል ይታወቃል።
በመጨረሻም፣ ተመራማሪዎች እነዚያን የቁጥር ቅደም ተከተሎች በመጠቀም፣ የተመረመረው ሰው የልጁ አባት የመሆን ዕድሉ ምን ያህል እንደሆነ ይወስናሉ።
ግማሹ የልጁ የጄኔቲክ መገለጫ ከእናቱ ጋር የሚዛመድ ሲሆን ሌላኛው ግማሽ ደግሞ ከአባትየው ጋር የሚዛመድ ከሆነ የአባትነት ማረጋገጫ ይረጋገጣል።
ያልተጠበቀው ውጤት
በኮሎምቢያ ምርመራ የተደረገላቸው መንትዮች ጉዳይ የተመለከቱ ሳይንቲስቶች ከእናቱ፣ ከሁለቱ ሕፃናት እና ለምርመራ ከመጣው አባት ከተወሰዱ ዲኤንኤዎች ውስጥ 17 ማይክሮሳተላይቶችን ተንትነዋል።
የሰውየው ዲኤንኤ ከልጆች ከአንዱ ጋር የሚዛመድ መሆኑን ደርሰውበታል፤ ሌላኛውን ግን አይመሳሰልም። ይህ እጅግ በጣም አስደናቂ ውጤት ነው።
ኡሳኩዌን "ለ26 ዓመታት የላቦራቶሪው ዳይሬክተር ሆኜ ሠርቻለሁ፤ እና ይህ እስካሁን ካየነው ሁሉ የተለየ ጉዳይ ነው፤ እና እስካሁን ድረስ ብቸኛው ጉዳይ ነው" ይላሉ።
"እነዚህ ጉዳዮች በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ትንሽ በሆነ ድግግሞሽ እንደሚከሰቱ ከሌሎች ሪፖርቶች ሰምተናል" ሲሉ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የጄኔቲክስ ተቋም የጄኔቲክስ ባለሙያ እና ተመራማሪ የሆኑት አንድሪያ ካሳስ አክለው ገልጸዋል።
ቡድኑ መመሪያውን በመከተል፣ ምንም ዓይነት ስህተቶች ሳይሰራ ወይም ናሙና ሳይቀይጥ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሙከራውን ደግሞታል። ውጤቱም ተመሳሳይ ነበር።
ለምን አልፎ አልፎ የሚከሰት ሆነ
በዩናይትድ ስቴትስ ባልቲሞር በሚገኝ አንድ ላቦራቶሪ ውስጥ ተመራማሪ የሆኑ ሳይንቲስቶች እአአ በ2014 ባሳተሙት ጽሑፍ መሠረት፣ ከ39,000 የአባትነት ምርመራዎች መካከል ሦስቱ ብቻ የተለያየ አባት እንዳላቸው ታውቋል።
ኡሳኩዌን ይህ ሥነ ሕይወታዊ ክስተት ለምን አልፎ አልፎ እንደሚከሰት ያብራራሉ።
"በመጀመሪያ ሴትየዋ ሁለት የወሲብ አጋሮች ሊኖሯት ይገባል። ሁለተኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሁለቱም ወንዶች ጋር ግንኙነት ማድረግ አለባት። በተጨማሪም ከአንድ በላይ እንቆላሎችን በተመሳሳይ ጊዜ መልቀቅ (ፖሊኦቩሌሽን) መኖር አለበት" ይላሉ።
ፖሊኦቩሌሽን በአንድ የወር አበባ ዑደት ውስጥ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ እንቁላሎችን መልቀቅ ማለት ነው።
"በመጨረሻም ሁለቱም እንቁላሎች ወደ ጽንስ መቀየር አለባቸው" ይላሉ ኡሳኩዌን።
አክለውም "ይህ ያልተለመደ ክስተት ሲሆን ሌላ ካልተለመደ ክስተት ሲደመር ሌላ ልዩ ያደርገዋል" ብለዋል።
የተለያዩ አባቶች ያሏቸው መንትዮች አንድ ዓይነት መንትዮች ሊሆኑ እንደማይችሉ ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ተመሳሳይ መንትዮች የሚወለዱት ከአንድ እንቁላል እና ከአንድ የወንድ የዘር ፍሬ ነው።
የግል ሕይወቶች
በአብዛኛዎቹ አንዲት ሴት ከአንድ በላይ እንቁላል የምትለቅ ከሆነ አንዱ እንቁላል ብቻ ይጸነሳል፤ ሌላኛው ወይም ሌሎች እንቁላሎች ያረጁ እና በፍጥነት ይሞታሉ።
ለዚህ ነው በአንድ ጊዜ ከሁለት የተለያዩ ወንዶች የሚጸነሱ መንታዎች እምብዛም የማይከሰቱት።
ሁለተኛው ጽንስ የሚፈጠረው እንቁላል ከመሞቱ በፊት መሆን አለበት።
እንደ የአሜሪካ ብሔራዊ የሕክምና ቤተ መጻሕፍት ዘገባ እንቁላል የሴትየዋን ኦቫሪ ከለቀቀ በኋላ የሚኖረው ዕድሜ ከ24 ሰዓታት ያነሰ ነው።
ይሁን እንጂ አንድሪያ ካሳስ እንቁላሎቹ በተመሳሳይ ጊዜ ሊለቀቁ እንደማይችሉ ያስረዳሉ።
"አንዳንድ ጊዜ አንድ ኦቫሪ አንድ እንቁላል ይለቅቃል፣ ከሁለት ወይም ከሦስት ቀናት በኋላ ደግሞ ሌላ እንቁላል ይለቅቃል" ብለዋል።
ይህም በተለያዩ ጊዜያት የመጸነስ ዕድልን ይጨምራል ሲሉ አክለዋል።
በጣም ጥቂት ጉዳዮች የሚታወቁበት ሌላው ምክንያት አብዛኛዎቹ ሰዎች የአባትነት ምርመራ የማያደርጉ መሆናቸው ነው።
ከተቋሙ የተውጣጡ ተመራማሪዎች እንደሚጠቁሙት "በአሁኑ ጊዜ የሞለኪውላር ዘዴዎች መገኘት እና የአባትነት ምርመራ ተፈላጊነት እየጨመረ በመምጣቱ" ይህ ክስተት ወደፊት ብዙም ያልተለመደ ሊሆን ይችላል።
ሳይንቲስቶች በተመሳሳይ ጊዜ ከተለያዩ ወንዶች በሚወለዱ መንትያዎች ላይ ብዙ የማወቅ ጉጉት ቢኖራቸውም የምርምር ሙያዊ ሥነ ምግባር ዝርዝር ነገሮችን ከመጠየቅ ይከለክላቸዋል።
ኡሳኩዌን "የአባትነት ምርመራዎች ሁልጊዜ የሚከናወኑት ለተሳተፉት ሰዎች ታማኝነት እና ግላዊነት ከፍተኛ አክብሮት በመስጠት ነው" በማለት ያስረዳሉ።