ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ልጆች እንደተወለዱ ሲፀዳዱ ስለወደፊት ጤናቸው ምን ይነግረናል?
ጨቅላ ሕጻናት በተወለዱ በቀናት ውስጥ ሲፀዳዱ ስለወፊት ጤናቸው ለማወቅ እንደሚረዳ ጥናቶች ያሳያሉ።
እአአ በ2017 በክውኒስ ሆስፒታል ሁለት ተመራማሪዎች የልጆች ሰገራ ላይ ምርምር አድርገዋል።
ስለ ልጆች የአንጀት ጤና ለመረዳት ለአንድ ዓመት የሰገራ ናሙናዎች ሰብስበዋል። ከ3,500 ጨቅላዎች የተገኘ ናሙና ላይ ነበር ጥናት ያካሄዱት።
የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ ናይጅል ፊልድ እንደሚሉት ሕጻናት በተወለዱ ከሦስት እስከ አራት ቀናት ባለው ውስጥ ሲፀዳዱ ስለ አንጀታቸው ጤና ለማወቅ ይቻላል።
አንጀት ውስጥ ማይክሮባዮም (gut microbiome) መፈጠር የሚጀምረው በተወለዱ በቀናት ውስጥ ነው።
የባክቴሪያ፣ ፈንጋይ እና ቫይረስ ስብስብ በጤና ውስጥ የጎላ ሥፍራ ይይዛሉ። ምግብን ለማብላላት የሚያስፈልግ ኢንዛየም ያመነጫሉ።
ሰውነትን ከበሽታ በመከላከል ረገድም ከፍተኛ ሚና አላቸው።
ጤናማ የአንጀት ባክቴርያ ሰውነት ውስጥ ሲኖር ጭንቀት፣ ድባቴ እና አልዛይመርን ጨምሮ ሌሎችም ሕመሞችን መከላከል እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ።
ጤናማ ያልሆነ የአንጅት ውስጥ ባክቴርያ የአንጀት ካንሰር፣ የልብ ሕመም፣ የኩላሊት ሕመም፣ ስኳር፣ ከልክ ያለፈ ውፍረትና ሌሎችም በሽታዎች ያስከትላል።
በአውስትራሊያ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሲድኒ ተመራማሪ የሆኑት አርቺታ ሚሽራ "ለመጀመሪያ ጊዜ ልጆች ሲፀዳዱ ስለ ወደፊት ጤናቸው ለማወቅ የሚቻልበት ናሙና ይገኛል" ይላሉ።
ይህ የሰገና ናሙና የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ለማወቅም የሚረዳ ነው።
ማይክሮባዮም ሰውነት በሽታ የመከላከል አቅሙን የሚያዳብርበትን መንገድ እንዴት እንደሚለውጥ ጥናት የሚያደርጉት አርቺታ እንደሚሉት፤ ሰውነት ጤናማ የሆነውን እና ጎጂ የሆነውን እንዲለይ የሚማረው በማይክሮባዮም አማካይነት ነው።
ልጆች ከተወለዱ ከስድስት ሳምንት እስከ 12 ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ሰውነታቸው የሚፈጥረው ባክቴርያ የአለርጂ ተጋላጭነትን እንዲሁም ሰውነታቸው እንዴት ለክትባት ምላሽ እንደሚሰጥ ማወቅ የሚቻልበት መንገድ ነው።
አንጀት ከሌሎች የሰውነት ክፍሎች ጋር እንዴት ሥራውን እንደሚያከናውን ለማወቅም ይረዳል።
ሰገራ ስለ ልጆች ጤና ምን ይነግረናል?
እትብት ውስጥ ባክቴርያ ስለሌለ ልጆች ሲወለዱ የአንጀት ማይክሮባዮም እንደሌላቸው ማወቅ ይቻላል። ልጆች ከእናታቸው አንጀት ባክቴርያ ያገኛሉ።
በሲድኒ በሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኒው ሳውዝ ዌልስ የአንጀት ባክቴርያ ላይ ምርምር የሚያደርጉት ስቲቨን ሌክ "ተፈጥሮ በጨቅላዎች የአንጀት ማይክሮባዮም የሚፈጥርበት አስደናቂ መንገድ አለው" ሲሉ ያስረዳሉ።
ልጆች ከማሕጸን ሲወጡ መጀመሪያ የሚታየው ጭንቅላታቸው ነው። የእናታቸው አንጀት ያለበትን አካባቢ ያልፋሉ ማለት ነው።
ሲወለዱ የሚፀዳዱበት ምክንያትም ይህ እንደሆነ ባለሙያው ያስረዳሉ።
ጨቅላ ሕጻናት ከተወለዱበት ቅጽበት ጀምሮ የአንጀት ውስጥ ባክቴርያ በጤናቸው ላይ ሚና ይኖረዋል።
በተወለዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ጤናማ ባክቴርያ በሰውነታቸው ውስጥ ካለ ለቫይረስ ኢንፌክሽን የመጋለጥ ዕድላቸው የጠበበ መሆኑን ይጠቁማል።
ልጆች ዕድሜያቸው ሲጨምር ለቫይረስ ኢንፌክሽን እንዳይጋለጡም ይከላከላል።
ከተለወዱ አራት፣ ሰባት እና 21 ቀናት ከሆናቸው 600 ልጆች የተወሰደው ናሙና ልጆቹ ስድስት ወር እና አንድ ዓመት ሲሆናቸው ካላቸው ጤና ጋር እንዲመሳካር ተደርጓል።
"በምጥ የተወለዱ እና በቀዶ ሕክምና የተወለዱ ልጆች ላይ የምናየው ውጤት የተለያየ ነው" ሲሉም ተመራማሪው ያስረዳሉ።
ልጆች በቀዶ ሕክምና ሲወለዱ በእናታቸው አንጀት በኩል አያልፉም። ስለዚህም ከመተንፈሻ አካላት ሕመም የሚከላከላቸውን ጠቃሚ ባክቴርያ ላያገኙ ይችላሉ።
እአአ በ2019 የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው ልጆች በተወለዱ በመጀመሪያው ሳምንት ውስጥ አንጀታው ውስጥ የተለያዩ ዓይነት ባክቴርያዎች ይፈጠራሉ።
እነዚህ የባክቴርያ ዓይነቶች (Bifidobacterium longum ወይም B. Longum፣ Bifidobacterium breve ወይም B. Breve እንዲሁም Enterococcus faecalis ወይም E .faecalis) የልጆችን የወደፊት ጤና እንደሚወስኑ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።
"የትኛውን ባክቴርያ ልጆች ያገኛሉ የሚለው የሰውነታቸውን ሁኔታ የሚወስን ነው" ሲሉ ስቲቨን ያስረዳሉ።
በቀዶ ሕክምና እና በምጥ የተወለዱ ልጆች የባክቴርያ ልዩነት
በምጥ የተወለዱ ልጆች በሰባተኛ ቀን ቢ ሎንጉም ወይም ቢ ብሪቭ የተባለ ባክቴርያ በአንጀታቸው ውስጥ ይኖራል።
በቀዶ ሕክምና የተወለዱ ልጆች ደግሞ ኢ ፋሲልስ የተባለ ባክቴርያ በአንጀታቸው የሚገኝ ይሆናል።
በምጥ የሚወለዱ ሕጻናት በእናታቸው አንጀት ውስጥ ካለው ባክቴርያ ጋር ተመሳሳይ ባክቴርያ ይኖራቸዋል።
በቀዶ ሕክምና የተወለዱ ልጆች በሆስፒታል ውስጥ ያለው ባክቴርያ ዓይነት በሰውነታቸው ይገኛል።
በምጥ እና በቀዶ ሕክምና የተወለዱ ልጆች የባክቴርያ ልዩነት የሚታየው አንድ ዓመት ሲሞላቸው ነው።
ጤናማ ባክቴርያ ያላቸው ሕጻናት ጤናቸው የተሻለ ሆኖ ይገኛል።
በጨቅላ ሕጻናት ሰገራ ላይ ጥናት ያደረገው ቡድን 1,000 ያህሉ ዕድሜያቸው ሲጨምር ወደ ሆስፒታል ተወስደው እንደሆነ ክትትል አድርጓል።
"ቢ ሎንጉም ባክቴርያ ያላቸው ልጆች እስከ ሁለት ዓመታቸው በመተንፈሻ አካል ሕመም የመያዝ ዕድላቸው በከፊል ቀንሷል" በማለት ዋና ተመራማሪው ያስረዳሉ።
እንደ ቢ ሎንጉም ያሉ ባክቴርያዎች በምጥ የተወለዱ ልጆችን ከመተንፈሻ አካል ሕመም ይከላከላሉ።
አስም፣ አለርጂ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረትና የሌሎችም ሕመሞች ተጋላጭነት በተወሰነ መጠን በቀዶ ሕክምና የተወለዱ ልጆች ላይ ጎልቶ የሚታየውም ለዚህ ነው።
እነዚህ የባክቴርያ ዓይነቶች በወተት ውስጥ የሚገኘውን ስኳር (oligosaccharides) ሰባብሮ በማብላላት ረገድ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው።
በጡት ወተት ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር በልጆች ኢንዛየም ብቻ አይብላላም።
ቢ ሎንጉም ስኳሩን አብላልቶ ወደ ሞለኪውል ይለውጣል። ይህም የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ያሳድጋል።
የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም
የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም ሲጎለብት ጤናማ የሆነ እና ጎጂ የሆነን ንጥረ ነገር በመለየት ሰውነት የሚያስፈልገውን እንዲወስድ ያግዛል።
የአንጀት ባክቴርያ ላይ ምርምር የሚያደርጉት ስቲቨን እንደሚሉት በተለይም በምዕራባውያን አገራት የአደገኛ ባክቴርያ ተጋላጭነት ውስን እየሆነ መጥቷል።
"ለአደገኛ ባክቴርያዎች ያለው ተጋላጭነት ቀንሷል። ስለዚህም ሕመም የሚከሰተው ከሰውነት የበሽታ መከላከል አቅም መዳከም ጋር በተያያዘ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።
በሽታ የሚያስከትል ባክቴርያን (pathogenic) የማስወገድ አቅም መገንባት አንደኛው መንገድ ነው።
ልጆች እንደተወለዱ አንጀታቸው አሲድ አያመነጭም። በአንጀታቸው ውስጥ የሚገኘው ከአዋቂዎች የተለየ ኦክስጅን ነው።
"ባይፊዶባክቴርየም (Bifidobacterium) በፍጥነት ኦክስጅንን ተጠቅሞ የፒኤች መጠንን ለመቀን የሚረዳ ባክቴርያ ነው። ጎጂ ባክቴርያ እንዳያድግም ያደርጋል" ይላሉ ተመራማሪው።
ሁሉም በምጥ የተወለዱ ሕጻናት ጠቃሚ የባክቴርያ ዓይነቶችን ያገኛሉ ማለት አይደለም።
በቀዶ ሕክምና የተወለዱ ልጆች ጠቃሚ ባክቴርያ ሊሰጣቸው ይገባል? የሚለው አጠያያቂ ነው።
በአውስትራሊያ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሲድኒ ተመራማሪ የሆኑት አርቺታ ሚሽራ እንደሚሉት፣ ልጆችን በቀዶ ሕክምና መውለድ ነፍስ አድን በሚሆንበት ጊዜ የሚከናወን ሲሆን፤ የልጆች ሰውነት የሚያጣውን የባክቴርያ ዓይነት እንዲገነቡ ማድረግ ይቻላል።
ከእናቶች ማሕጸን ፈሳሽ በመውሰድ የጨቅላ ሕጻናትን ቆዳ እና ከንፈር መቀባት (vaginal seeding) አንደኛው መንገድ ነው።
በልጆች አንጀት ውስጥ ጠቃሚ ባክቴርያ እንዲፈጠር የሚያግዝ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ሆኖም ግን ልጆች ለጎጂ ባክቴርያም ሊጋለጡ ይችላሉ። አንድ አራተኛ የሚሆኑ ሴቶች በመራቢያ አካላቸው ላይ 'group-B strep' የሚባል ባክቴርያ ያለ ሲሆን፤ ይህም ጨቅላ ሕጻናትን ሊጎዳ ይችላል።
እአአ በ2019 የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው ከእናቶች ማሕጸን የሚገኘው ፈሳሽ ላይ ጠቃሚ ባክቴርያ ማግኘት አልተቻለም።
ሌላው አማራጭ መንገድ ከእናቶች ሰገራ ናሙና በመውሰድ በጨቅላ ሕጻናት አንጀት ውስጥ መክተት ነው።
ይህ 'microbial transplants' በመባል የሚታወቀው መንገድ ጥቂት ሙከራ ብቻ የተደረገበት በመሆኑ በባለሙያዎች አይመከርም።
"ከእናት መራቢያ አካል ወይም ከሰገራ ባክቴርያ ወስዶ ለልጆች መስጠት ይጠቅማል? የሚለውን አሁን ላይ ማወቅ አንችልም። ጨቅላ ሕጻናትን ሊጎዳቸው ይችላል" ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።
ተጨማሪ የባክቴርያ እንክብሎች (Probiotic supplements) መውሰድ የተሻለው መንገድ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።
ከዘጠኝ ወር በፊት ለሚወለዱ እና የሰውነት ክብደታቸው ከመጠን በታች ለሆነ ጨቅላ ሕጻናትም ይህ ተጨማሪ ባክቴርያ ይሰጣል።
ተመራማሪዎች ለወደፊት ተስፋ የጣሉበት ጥናት የልጆችን ዘረ መል እና በሽታ የመከላከል አቅም በማጥናት ለእያንዳንዱ ልጅ የሚስማማ ባክቴርያ ሠርቶ መስጠትን ነው።