ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ መንግሥት ከምርጫው አስቀድሞ መገናኛ ብዙኃን ላይ "የከፈተው የአፈና ዘመቻ" እንዲቆም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በዚህ የምርጫ ወቅት በመገናኛ ብዙኃን ላይ አጠናክረውታል ያለውን "አፈና እንዲቀለብሱ" ጠየቀ።
አምነስቲ፤ "የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት አካላትም" ስለዚህ "ስልታዊ" እርምጃ ድምጻቸውን እንዲያሰሙም ጥሪ አቅርቧል።
የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ተቋም ዛሬ አርብ ግንቦት 21/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በመጪው ሰኞ ከሚካሄደው ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ አስቀድመው "ትችቶችን ለማፈን" ሲሉ "የፕሬስ ነጻነት ላይ የሚወስዱትን እርምጃ አጠናክረዋል" ሲል ከስሷል። የመገናኛ ብዙኃን የምዝገባ ፈቃድ እንዲሁም የጋዜጠኞች የዘገባ ፈቃድ እንደተሰረዘም አክሏል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ "በገለልተኛ መገናኝ ብዙኃን ላይ የዘፈቀደ እስር፣ የግዳጅ ስወራ እና ጋዜጠኞች ላይ ሕገ ወጥ ክትትል" በመፈጸም "የአፈና ዘመቻ" ተከፍቷል በማለትም ወንጅሏል።
አምነስቲ ያነጋገራቸው ስድስት የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች "የመጪው ምርጫ ዘገባቸው ሚዲያ ላይ እየተካሄደ ባለው ጠበኛ እርምጃ ምክንያት ክፉኛ መጎዳቱን" እንደተናገሩ በመግለጫው ጠቅሷል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላይ የሚታየው "የግልጽነት አለመኖርም" የምርጫ ዘገባዎች ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ተቋሙ ገልጿል። ምርጫ ቦርድ የዘገባ ፈቃድ በሚሰጥበት ወቅት ጋዜጠኞች እንዲገቡ የሚያደርገውን "ቃለ መሃላ" በማንሳትም "ስለ ምርጫው በሕዝብ ውይይት የሚደረግባቸው ጉዳዮችን ለመቆጣጠር [የሚውል] ግልጽ መሣሪያ ነው" ብሏል።
የአምነስቲ የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ፤ "[ቃለ መሃላው] ቦርዱ የማይመቹ መረጃዎችን ሳንሱር ለማድረግ ወይም የትኛው እውነት የትኛው ደግሞ ሐሰት እንደሆነ ለመወሰን ሥልጣን ይሰጠዋል" ሲሉ ተችተዋል።
"የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እየጨመሩ የመጡትን እነዚህን የአምባገነንነት ዝንባሌዎች መቀልበስ እና መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚካሄደውን የአፈና ዘመቻ ማብቃት አለባቸው" ብለዋል።
ዳይሬክተሩ፤ "ዜጎች ለመምረጥ እየተዘጋጁ ባለበት በዚህ ወቅት፤ የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች እንዲሁም የሚመለከታቸው ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች አካላት የአገሪቱን ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን ስለሚካሄደው ስልታዊ መበታተን ድምጻቸውን ማሰማት አለባቸው" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ መገናኛ ብዙኃንን እና ትርክትን በተመለከተ በሚያዝያ መጨረሻ በተካሄደ አንድ ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር ሚዲያዎችን "አርዕስተ ዜና በመሸጥ" ወቅሰው ነበር። "ጉዳይን መሸጥ ሳይሆን፤ ርዕሰ ጉዳይን መሸጥ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች አንዱ ስንክሳር ይሄ ነው" በማለት ተናግረዋል።
ከስምንት ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን ሲመጡ የመገናኝ ብዙኃንን ነጻነትን ለማስጠበቅ የወሰዷቸውን እርምጃዎች ያስታወሱት ዐቢይ፤ ይሁን እንጂ ሚዲያው ነጻነት ሲያገኝ "ሥነ ምግባር የሚባል ነገር ያልተከተሉ፤ ነጻነትን በቅጡ ማስተደዳር ያልቻሉ ሰዎች ነበሩ" ሲሉ ተደምጠዋል።
ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ያለው የመገናኝ ብዙኃን ሥነ ምዳር "አልፎ አልፎ የሚናገሩ ሰዎችን ማግለል" ጨምሮ ችግሮች እንዳሉበትም ተናግረዋል። ይሁን እንጂ "በንጽጽር የተከፈቱ ጉዳዮች አሉ" ብለዋል።
ዓመታዊው የዓለም አገራትን የፕሬስ ነጻነት ደረጃ የሚያወጣው ዓለም አቀፉ የድንበር የለሽ ጋዜጠኞች ቡድን፤ ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በ2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ደረጃ ከ180 አገራት 110ኛ ላይ አስቀምጦት ነበር። ቡድኑ ዘንድሮ ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ደረጃ አሽቆልቁሎ 148ተኛ ላይ ተቀምጧል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የአዲስ ስታንዳርድ እና የዋዜና ሬዲዮን የምዝገባ ፈቃዶች መሰረዙን አስታውሷል። የሮይተርስ ጋዜጠኞች የዘገባ ፈቃድም መሰረዙን ጠቅሷል።