ቀጥታ, በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመራ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን አዲስ አበባ ገባ

በመጪው ሰኞ ሰባተኛውን አጠቃላይ ምርጫን የሚታዘቡ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች አዲስ አበባ መግባታቸውን ኅብረቱ አስታወቀ። በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመራው የኅብረቱ ታዛቢዎች ከ37 አገራት የተውጣጡ እና 73 አባላትን የያዘ መሆኑን በመግለጫው ላይ ተገልጿል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረገው ድርድር “እስካሁን አልተሳካም” አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር “እስካሁን አልተሳካም” አሉ።

    ድርድሩ “ገና ደስተኛ አላደረገንም” ያሉት ትራም “ነገር ግን [ደስተኛ] እንሆናለን” ብለዋል።

    ትራምፕ በአስተዳደራቸው ሥር ካሉ ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ “መሆን ያለበት በዚህ መንገድ ነው፤ አለበለዚያ ግን እንጨርሰዋለን” ሲሉም ገልጸዋል።

    የኢራን ባለሥልጣናት ድርድሩን እያካሄዱ ያሉት “ደካማ ሆነው ነው” ብለዋል።

    “ምን እንደሚሆን እናያለን። ተመልሰን ሥራውን መጨረስ ይኖርብን ይሆናል። ወይም አይኖርብንም” ሲሉም አክለዋል።

    የኢራን መሪዎች “ስምምነት ላይ ለመድረስ ይፈልጋሉ” ሲሉም ትራምፕ ተደምጠዋል።

    የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚፈልጉ ገልጸው “ካልተሳካ ግን ፕሬዝዳንቱ አማራጭ አላቸወ” ብለዋል።

    በሌላ በኩል ኢራን ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ድርድር፤ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኝ፣ ይፋዊ ያልሆነ፣ የመግባቢያ ሰነድ ማዕቀፍ ረቂቅ እንደደረሳት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ቢዘግቡም ዋይት ሀውስ ግን ይሄንን "ፍጹም ፈጠራ" ሲል አስተባብሏል።

  2. ኢራን "የመግባቢያ ሰነድ ረቂቅ” ደርሶኛል ብትልም አሜሪካ አስተባበለች

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ድርድር፤ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኝ፣ ይፋዊ ያልሆነ፣ የመግባቢያ ሰነድ ማዕቀፍ ረቂቅ እንደደረሳት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ቢዘግቡም ዋይት ሀውስ ግን ይሄንን "ፍጹም ፈጠራ" ሲል አስተባብሏል።

    የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ኦሊቪያ ዌልስ “ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንደተናገሩት ድርድሩ እየተሻሻለ ነው። [ፕሬዝዳንቱ] ቀይ መስመሮቻቸውን በግልጽ አስምረዋል” ብለዋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ ቴህራን በአንድ ወር ውስጥ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ያለውን የጉዞ መጠን ከጦርነቱ አስቀድሞ ወደነበረው ትመልሳለች። በምላሹ አሜሪካ ወታደሮቿን ከኢራን ዙርያ ታስወጣለች፤ በባሕር ኃይሉ ላይ የጣለችውን ማዕቀብም ታነሳለች።

    የመርከቦችን ጉዞ ማስተዳደሪያ መንገድ የሚወሰነው በኢራን እና ኦማን እንደሆነ ተገልጿል።

    ነገር ግን “ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለአሜሪካ ሕዝብ የሚጠቅም እና ኢራን መቼም ቢሆን ኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት የሚያግድ ስምምነት ብቻ ነው የሚቀበሉት” ብለዋል።

    የኢራን የብሔራዊ ደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ እና የዓለም አቀፍ ደኅንነት ምክትል ዳይሬክተር አሊ ባግሪ፤ ቴህራን ከዋሽንግተን ጋር እያደረገችው ባለው ድርድር የዩራኒየም ጉዳይ በአጀንዳነት እንዳልቀረበ ተናግረዋል።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን በማስተዳደር ረገድ ኢራን እና ኦማን ሚና እንዲኖራቸው እየተደራደሩ መሆኑን አረጋግጠዋል።

    “በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የማለፍ ሁኔታ እና አካሄድ የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ከነበረው ፈጽሞ የተለየ ይሆናል” ብለዋል።

    “ሁሉም ነጥቦች ላይ ካልተስማማን በስተቀር ስምምነት ላይ ደርሰናል ብለን አናምንም” ሲሉም አክለዋል።

  3. ኢራን በዩራኒየም ይዞታዋ ላይ እንደማትደራደር አስታወቀች

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር እያደረገችው ባለው ድርድር የዩራኒየም ጉዳይ በአጀንዳነት እንዳልቀረበ በኢራን የብሔራዊ ደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ እና የዓለም አቀፍ ደኅንነት ምክትል ዳይሬክተር አሊ ባግሪ ተናገሩ።

    ባለሥልጣኑ ይህንን ያሉት በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ ውስጥ እየተካሄደ ባለው 14ኛው ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣናት ስብሰባ ወቅት በተጓዳኝ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ቀደም ሲል የዳበረው የኢራን ዩራኒየም ክምችት፤ በሚደረስ ስምምነት ወደ አሜሪካ ተወስዶ ወይም በሌላ ስፋራ ላይ እንዲወድም እንደሚደረግ ተናግረው ነበር።

    የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ ለወራት ያለመቋጫ እየተካሄደ ያለው የኢራን እና የአሜሪካ ድርድር ወደ ስምምነት መቃረቡን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ባለፉት ቀናት ሲናገሩ ቆይተዋል።

    የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ዋነኛ መነጋገሪያ ቢሆንም አሳልፋ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኗን እና የድርድሩ ቀይ መስመር መሆኑን በተደጋጋሚ ስትገልጽ ነበር።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን ኢራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ የቀረበላትን ሃሳብ የማትቀበል ከሆነ ሌላ ዙር ከባድ ጥቃት እንደሚጠብቃት እያስጠነቀቁ ነው።

  4. የኮንጎ ግጭት ኢቦላን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እንዳሰናከለ ዶ/ር ቴድሮስ ገለጹ

    በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለው ግጭት የኢቦላን ሥርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ላይ ጫና ማሳደሩን የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ገለጹ።

    በአገሪቱ “ግጭት እና አደገኛ በሽታ” መደራረባቸውን የተናገሩት ዶ/ር ቴድሮስ፤ በኢቱሪ ግዛት በሽታውን የመከላከል እንቅስቃሴ ማድረግ መስተጓጎሉን አክለዋል።

    ኃላፊው በኤክስ ገጻቸው ባወጡት መግለጫ የዓለም ጤና ድርጅት “ቦምብ እየዘነበ የማኅበረሰቡን እምነት ማግኘት ወይም ታማሚዎችን መለየት አይችልም”

    ዶ/ር ቴድሮስ ቫይረሱን በቁጥጥር ሥር የማዋል ጥረቱን ለመምራት ዛሬ ኮንጎ እንደሚገቡ ተገልጿል። በኢቦላ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 220 ደርሷል።

    የአገሪቱ መንገዶች አመቺ ባለመሆናቸው የእርዳታ ሠራተኞች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመሥራት ተቸግረዋል። ግጭት እና መፈናቀልም የጤና ሥርዓቱን አናግተዋል። በተጨማሪም ዓለም አቀፍ እርዳታ ተቋርጧል።

    ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት ኢቱሪ ግዛት ከአውሮፓውያኑ 2021 አንስቶ በወታደራዊ አስተዳደር ሥር ናት።

  5. ኢራን እና አሜሪካ ልዩነቶቻቸውን ያጠብባሉ ብላ ተስፋ እንደምታደርግ ቻይና ገለጸች

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ የኢራን ጦርነት ተፋላሚ ወገኖች የተኩስ አቁሙን ለማስቀጠል ቁርጠኛ ሆነው እንደሚቀጥሉ እና ልዩነቶቻቸውን ያጠብባሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገለጹ።

    አሜሪካ በደቡብ ኢራን የመከላከል ያለችውን ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ቴህራን ማክሰኞ ዕለት ዋሺንግተንን የተኩስ አቁሙን በመጣስ ከስሳለች።

    ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም የሚደረገው ድርድር “የተወሰነ ቀናት ሊወስድ ይችላል” ብለዋል።

    ዋንግ በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በተገኙበት ወቅት "ሰላም በተቻለ ፍጥነት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲመለስ ተፋላሚ አካላት የተኩስ አቁምን ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንደሚቆዩ እና ልዩነቶቻቸውን ለማጥበብ ግማሽ መንገድ እንደሚገናኙ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

    ዋንግ አክለውም ሁሌም እንደምንለው ሰላም እና መፍትሄ ለማምጣት ጊዜ ይፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ “ለረዥም ጊዜ የቆዩ ችግሮች ቶሎ አይፈቱም” ብለዋል።

    “ይሁን እንጂ በድርድሩ የሚደረግ እያንዳንዱ እርምጃ የበለጠ ተስፋን ይሰጣል፤ እንዲሁም ግጭቱ ቶሎ በተቋጨ ጊዜ የሰላማዊ ዜጎችን ጉዳት መቀነስ ይቻላል” ብለዋል።

  6. የዩኬ የደህንነት ተቋም ሩሲያ ወሳኝ የመሠረተ ልማቶችን እና ዲሞክራሲን “ያለመታከት ዒላማ እያደረገች” ነው ሲል ወነጀለ

    የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ፣ ደህንነት እና ሳይበር ኤጀንሲ ሩሲያ ያለ መታከት ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን እና አገልግሎቶችን ማጥቃት በመቀጠሏ አገሪቱ አሳሳቢ እና ወሳኝ ጊዜ ላይ እንደምትገኝ ገለጸ።

    የዩኬ የስለላ ተቋም ኃላፊ የሆኑት አኔ ኪአስት በትለር ረቡዕ ዕለት የሩሲያ እርምጃ ለዩናይትድ ኪንግደም የሚኖረውን ስጋት በሚመለከት እንዲሁም እንዴት መመከት እንዳለባት የሚገልጽ ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል።

    ከኃላፊዋ ንግግር ተቀንጭቦ የተጋራው መልዕከት ላይ ሩሲያ “ወሳኝ የሆነ መሠረተ ልማቶችን፣ የዲሞክራሲ ሂደቶችን፣ የአቅርቦት ሰንሰለቶችን እና የሕዝብ እምነትን ዒላማ አድርጋለች” ብለዋል።

    ሩሲያ በብሪታኒያ ግዛት ውስጥ የአገር ክህደት ወንጀልን በማበረታታት የምትወቀስ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዩኬ እና የኔቶ አባል አገራት ላይ በይፋ ያልታወጀ ‘የተቀናጀ ጦርነት’ ከፍታለች በሚል ትከሰሳለች።

    ክሬምሊን ውንጀላውን ያስተባብላል።

    በትለር ተቋማቸው “ግድየለሽነት የተሞላበት” ያሉትን የሳይበር ጥቃቶች ለመመከት እንዲሁም “የግድያ ሙከራዎችን” ለመከላከል ያለ እረፍት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

    አክለውም “በእንዲህ ዓይነት ጠብ አጫሪት እና ግርግር ውስጥ ተቋማችን ያለመታከት ከደህንነት እና መከላከያ አጋሮቻችን ጋር በመሆን የሩሲያን ስጋት ለመቀነስ ይሰራል” ብለዋል።

    ክሬምሊን የኬጂቢ ባልደረባ የነበረውን አሌክሳንደር ሊትቪኔንኮን በለንደን ሆቴል ውስጥ ሳለ በጠጣው ሻይ ውስጥ መርዛማ ኬሚካል በመጨመር ለመግደል ሙከራ አድርጓል መባሉን አስተባብሏል።

    እአአ በ2018 የቀድሞው የሩሲያ ወታደራዊ ደህንነት ባልደረባ የነበረውን ሰርጌይ ስክሪፓልን ለመግድል ሙከራ በማድረግ ተከስሷል።

    ሩሲያ እአአ በ2022 ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደም ከኪየቭ ጎን በመቆሟ በምዕራባውያን አገራት ላይ “የተቀናጀ ጦርነት” በመክፈት ትወነጀላለች።

  7. በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመራ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን አዲስ አበባ ገባ

    በመጪው ሰኞ ሰባተኛውን አጠቃላይ ምርጫን የሚታዘቡ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች አዲስ አበባ መግባታቸውን ኅብረቱ አስታወቀ።

    በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመራው የኅብረቱ ታዛቢዎች ከ37 አገራት የተውጣጡ እና 73 አባላትን የያዘ መሆኑን በመግለጫው ላይ ተገልጿል።

    ይህ አምባሳደሮችን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ተወካዮች፣ የምርጫ ባለሙያዎች፣ የሰብኣዊ መብት፣ የሥርኣተ ፆታ፣ የወጣቶች እና የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮችን ያከላተተ መሆኑ ተገልጿል።

    የአፍሪካ ኅብረት ማክሰኞ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የምርጫ ታዛቢዎች በምርጫው ዕለት የድምጽ አሰጣጥ ሂደትን እና ቆጠራን ለመታዘብ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚሰማሩ መሆኑ አስታውቋል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመላ አገሪቱ ሰኞ ግንቦት 24 የሚደረገው ሰባተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ለመታዘብ ከአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች በተጨማሪ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ታዛቢዎች እንደሚገኙ አስታውቋል።

    የአፍሪካ ብረት እና የኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በኢትዮጵያ መንግሥት ግብዣ መሠረት መሆኑን የምርጫ ቦርድ እና ኅብረቱ አስታውቀዋል።

    የምርጫ ታዛቢ ቡድኑ ግምገማውን በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ፣ በአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም አስፈላጊ በሆኑ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ በተቀመጡ መስፈተርቶች ላይ በመመሥረት ግምገማውን እንደሚያደርግ ተገልጿል።

    ታዛቢዎቹ ከምርጫ ቦርድ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከዕጩዎች፣ ከመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ከሌሎች የምርጫ ታዛቢዎች ጋር በትብብር እንደሚሠሩ ተጠቅሷል።

    ታዛቢ ቡድኑ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ግንቦት 26/2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይፋ የሚያደርግ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የመጨረሻ ሪፖርቱን ደግሞ ከምረጫው በኋላ በሁለት ወር ውስጥ ያቀርባል ተብሏል።

    የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበራት ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ ከ500 በላይ የሚሆኑ የረጅም ጊዜ ታዛቢዎችን ማሰማራታቸውን አስታውቀዋል።

  8. እስራኤል በጋዛ ከተማ በፈጸመችው ጥቃት አዲሱን የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ መግደሏን አስታወቀች

    እስራኤል ማክሰኞ ዕለት በጋዛ ከተማ በፈጸመችው ጥቃት በዲሱን የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ መግደሏን አስታወቀች።

    የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ በተጨናነቀ የገበያ ስፍራ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ በፈጸመው ከፍተኛ የአየር ድብደባ ቢያንስ ሦስት ፍልስጤማውያን መሞታቸውን የሕክምና ባለሙያዎችና የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

    ጥቃቱ የኢድ አል-አድሃ በዓል ከመከበሩ በፊት ጎዳናዎች በገበያተኞች ተጨናንቀው ባለበት ወቅት በጋዛ ከተማ መሃል በሚገኘው የአል-ካያሊ ሕንፃ የላይኛውን ሦስት ፎቅ ዒላማ ማድረጉ ተገልጿል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቢሮ ቀደም ሲል የእስራኤል ጦር የሐማስን የጦር ክንፍ አዛዥ መሐመድ ኦዴህን ዒላማ እንዳደረገ አስታውቋል። ይህም የቀድሞው የጦር አዛዥ በተመሳሳይ ጥቃት ከተገደለ ከጥቂት ቀናት በኋላ የተፈጸመ ነው።

    ይህ እስራኤል ከሐማስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ካደረገች በኋላ በጋዛ የተፈጸመ የቅርብ ጊዜ ከባድ ጥቃት ነው።

    ኦዴህ በጥቃቱ መገደሉን በተመለከተ የእስራኤል መንግሥት ሲያስታውቅ ሐማስ ግን ምንም አስተያየት አልሰጠም።

    የነፍስ አድን ሠራተኞች በስፍራው ሲደርሱ በአካባቢው በደረሰው ከባድ ጉዳት እና በነበረው መጨናነቅ ምክንያት ወደ ላይኛው ፎቅ ለመውጣት ተቸግረዋል።

    የዓይን እማኞች ቢያንስ አምስት ሚሳኤሎች ሕንፃውን ከተለያየ አቅጣጫ በተመሳሳይ ጊዜ መምታታቸውን ተናግረዋል።

    አንድ ነዋሪ ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት የሄሊኮፕተር ድምፅ መስማቱን ተናግሯል።

    ከቦታው የተገኘ ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው አምቡላንሶች እና የሲቪል መከላከያ ሠራተኞች በተመታው ሕንፃ ውስጥ የተረፉ ሰዎች ካሉ ሲፈልጉ የሚያሳይ ሲሆን በአቅራቢያው በርካታ ሰዎች ተሰብስበው ነበር።

    የኔታንያሁቢሮ የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ሐማስ የፈጸመውን ጥቃት “ካቀነባበሩ ሰዎች መካከል አንዱን” መሐመድ ኦዴህን ዒላማ እንዳደረገውአስታውቋል።

    “ኦዴህ በበርካታ የእስራኤልዜጎችን እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ግድያ፣ ጠለፋ እና መቁሰል ተጠያቂ ነው” ሲል መግለጫውአክሏል።

    የቡድኑ ታጣቂ ክንፍ አዛዥ የነበሩት ኢዝ አድ-ዲን አል-ሃዳድ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በእስራኤል የአየር ጥቃት ተገድለዋል።

    ይህ ጥቃት በአንድ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ቢያንስ ሦስት ሰዎችን ገድሏል ሲሉ የዓይን እማኞች እና የአካባቢው ምንጭ ተናግረዋል።

    እስራኤል የተኩስ አቁም ከተደረሰበት እአአ ከጥቅምት 10 ጀምሮ በጋዛ ዙሪያ ጥቃቶችን ስትፈጽም ቆይታለች።

    ሐማስ እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ እና ሲቪሎችን በማጥቃት በተደጋጋሚ ሲከስ ቆይቷል።

    የጋዛ የጤና ሚኒስቴር በተኩስ አቁም ስምምነቱ ወቅት በእስራኤል በተሰነዘረው ጥቃት ከ800 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።

  9. እስራኤል በሊባኖስ በተከታታይ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ቢያንስ 31 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    እስራኤል በተከታታታይ በምሥራቃዊ እና ደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት በርካታ ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 31 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    የእስራኤል ጦር በሊባኖስ የሚፈጽመውን ከባድ ጥቃት የቀጠለው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሄዝቦላህ ላይ የሚወሰደው ወታደራዊ እርምጃ እንዲጠናከር ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ ነው።

    የእስራኤል መከላከያ ከ100 በላይ የሄዝቦላህ መሠረተ ልማቶችን እና ተዋጊዎችን ዒላማ አደርጎ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    ኔታንያሁ ሰኞ ምሽት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፤ እስራኤል “ከሄዝቦላህ ጋር ጦርነት ላይ” እንደሆነች ተናግረው ሠራዊቱ “አድቃቂ ምት” እንዲፈጽም ማዘዛቸውንም ገልጸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እስራኤል በከፈተችው ወታደራዊ ዘመቻ "ከ600 በላይ አሸባሪዎች” መገደላቸውንም ተናግረዋል። "አሁን ከእኛ የሚጠበቀው ጥቃቱን ማጠናከር እና ጥንካሬውን ይበልጥ መጨመር ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

    ኔታንያሁ ማክሰኞ ዕለት በደህንነት ካቤኔ ስብሰባቸው ላይ “በሊባኖስ የምናካሄደውን ዘመቻ እያሰፋ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    “የእስራኤል ጦር በምድር ከፍተኛ ኃይል አሰማርቶ ዘመቻ እያካሄደ እና ገዢ መሬቶችን እየተቆጣጠረ ነው” ብለዋል።

    አክለውም በሰሜን እስራኤል የሚገኙ እስራኤላውያንን ከሄዝቦላህ ጥቃት ለመከላከል “የደህንነት ቀጣናዎች እየመሰረተ ነው” ብለዋል።

    በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በተደጋጋሚ ተጥሷል።

    እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በየዕለቱ የአየር ድብደባ የምትፈጽም ሲሆን ሄዝቦላህም ሮኬቶችን እና ድሮኖችን ይተኩሳል።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በምሥራቅ ሊባኖስ በሚገኘው ቤካ ሸለቆ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ጥቃት በመክፈት ሄዝቦላህን እየመታ መሆኑን ይናገራል።

    የተወሰኑ ጥቃቶች በተባበሩት መንግሥታት በቅርስነት የተመዘገበ እና የ900 ዓመት እድሜ እንዳለው የሚገመት ቤተ መንግሥት ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  10. በኢራን ለሦስት ወራት ተቋርጦ የነበረው የኢንተርኔት አገልግሎት ተጀመረ

    በኢራን ለሦስት ወራት ያህል ተቋርጦ የቆየው የኢንተርኔት አገልግሎት ዳግም መጀመሩን የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት አስታወቁ።

    ሞሃማድ ሬዛ አረፍ ማክሰኞ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ “ነጻ እና ቁጥጥር የሚደረግበት የኢንተርኔት አገልገሎት ለመስጠት የመጀመርያ እርምጃ ወስደናል” ብለዋል።

    ኔትብሎክስ እና ኬንቲክ የተባሉ የዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ግንኙነትን የሚከታተሉ ተቋማት በኢራን ዛሬ ከምሳ ሰዓት ጀምሮ “በከፊል” የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩን ተናግረዋል።

    በኢራን የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠው አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በአገሪቱ ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ ነበር።

    የኢራን ባለሥልጣናት በጦርነቱ ወቅት ኢንተርኔት የተዘጋው ከደኅንነት ጋር በተያያዙ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። ይህንን በማድረግ ክትትል፣ ስለላ እና የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል እንዳሰቡ ጠቁመዋል።

    በቴህራን የሚገኝ አንድ ግለሰብ ዛሬ የዋይፋይ አገልግሎት መጀመሩን ለቢቢሲ ተናግሯል።

    ኔትብሎክስ የኢንተርኔት አገልግሎት “የሚቀጥል” ስለመሆኑ “ግልጽ አይደለም” ብሏል።

  11. እስራኤል በሊባኖስ መንደሮች ላይ በፈጸመችው ጥቃት አስራ አንድ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    እስራኤል በሄዝቦላህ ላይ የምትወስደውን ወታደራዊ እርምጃ እንደምታጠናክር ከገለጸች በኋላ በደቡብ እና ምሥራቃዊ ሊባኖስ በርካታ ድብደባዎችን መፈጸሟ ተገለጸ።

    የእስራኤል ጦር ከ100 በላይ የሄዝቦላህ መሠረተ ልማቶችን እና ተዋጊዎች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙን ተናግሯል።

    በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል በአሜሪካ አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ተደርሷል።

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር በቤካ ቫሊ በሚገኝ ማሽጋሃራ በተሰኘ መንደር በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ 11 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

    የእስራኤል ጦር ግን “የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ” በታየበት አካባቢ ጥቃት መፈጸሙን ተናግሯል።

    የእስራኤል ጦር ጥቃቱን አጠናክሮ የቀጠለው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሄዝቦላህ ዒላማዎች ላይ “ጠንከር ያለ ጥቃት” እንዲፈጸም ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ ነው።

    በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በተደጋጋሚ ተጥሷል።

    እስራኤል በተለይ በደቡባዊ ሊባኖስ በተደጋጋሚ የአየር ድብደባ የምትፈጽም ሲሆን ሄዝቦላህም ሮኬቶችን እና ድሮኖችን በሰሜን እስራኤል ወደሚገኙ አካባቢዎች ይተኩሳል።

  12. ኢራን፣ አሜሪካ የፈጸመችው አዲስ ጥቃት የተኩስ አቁሙን የጣሰ ነው አለች

    አሜሪካ ራስን መከላከል በሚል አዲስ ጥቃት በደቡባዊ ኢራን ከፈጸመች በኋላ ቴህራን ዋሺንግተን የተኩስ አቁሙን ጥሳለች ስትል ከሰሰች።

    የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ድርድር “ጥቂት ቀናት ሊወስድ ይችላል” ብለዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ በደቡባዊ ኢራን ሆርሞዝጋን አውራጃ ጥቃት መፈጸሟን አስታውቆ የተኩስ አቁሙ “ግልጽ ጥሰት ነው” ሲል ተናግሯል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አሜሪካ “ጠብ አጫሪ እና ተቀባይነት ለሌለው ድርጊቷ” ተጠያቂ ትሆናለች ብሏል።

    አሜሪካ ጥቃት የፈጸመችበት ሆርሞዝጋን ክልል ከሆርሙዝ ወሽመጥ ጋር የሚዋሰን ነው።

    ኢራን በመግለጫው “ያለምንም ጥርጥር የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ምላሽ ሳይሰጥ የሚተወው ምንም ክፋት የለም እንዲሁም የኢራን ዜጎችን ከመከላከልም ወደ ኋላ አይልም” ብላለች።

    ሁለቱ አገራት እስከ ትናንት ሰኞ ድረስ በመግባቢያ ሰነዱ ዙሪያ የሚደረገው ንግግር ለውጥ ማሳየቱን ሲናገሩ ነበር።

    አሜሪካ እና ኢራን የሚያደርጉት ንግግር በስምምነት ከተቋጨ ለሦስት ወር የዘለቀውን ጦርነቱን ያስቆማል፣ የሆርሙዝ ወሽመጥን ያስከፍታል እንዲሁም የተኩስ አቁሙን በ60 ቀናት ይራዘማል ተብሎ ነበር።

    የአሜሪካ ጦር በደቡብ ኢራን የሚገኙ የሚሳዔል ማከማቻዎች እና ፈንጂ የሚጥሉ ጀልባዎችን ዒላማ በማድረግ አዲስ ዙር ጥቃት መክፈቱን አስታወቋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ “ራስን መከላከል” እንደሆነ አስታውቋል። ዓላማውም “በኢራን ኃይሎች ስጋት የተጋረጠባቸው ወታደሮቻችንን መከላከል ነው” ብሏል።

  13. የኢራኑ ጠቅላይ መሪ “ባሕረ ሰላጤው ከዚህ በኋላ የአሜሪካ ጦር ሰፈር መጠለያ አይሆንም” አሉ

    የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ ለኢድ አል አድሃ በዓል ባስተላለፉት መልዕክት እስራኤልን “አደገኛ” በማለት ከዚህ በኋላ የፋርስ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች መቀመጫ አይሆንም ሲሉ ገለጹ።

    ጠቅላይ መሪው በጽሁፍ ባስተላለፉት እና በመንግሥት ቴሌቪዥን በተነበበው መልዕክታቸው ላይ እስራኤልን “በቀጣናው አደገኛ እና ገዳይ ህመም” በማለት “መወገድ ይገባታል” ማላታቸውን ኢራኑ ዜና ወኪል ታስኒም ዘግቧል።

    ሞጅታባ የአባታቸው መገደል ተከትሎ የጠቅላይ መሪነቱን ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ እስካሁን ድረስ ለሕዝብ በይፋ ያልታዩ ሲሆን፣ መልዕክታቸውን በጽሁፍ ሲያስተላልፉ ቆይተዋል።

    በአሁኑ መልዕክታቸው በኢራን ላይ ጦርነት ከተከፈተ በኋላ ነገሮች እየተቀያየሩ መሆናቸውን በማንሳት የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች በባሕረ ሰላጤው አገራት ውስጥ ቦታ እንደማይኖራቸውን ገልጸዋል።

    ጠቅላይ መሪው "ጊዜን ወደ ኋላ መመለስ እንደማይቻል እርግጥ እንደሆነው ሁሉ፤ በቀጣናው ያሉ አገራት እና መሬት ከዚህ በኋላ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች መጠለያ አይሆኑም” ሲሉ የአሜሪካ ሚና በአካባቢው እንደማይኖር አመለክተዋል።

    ጨምረውም "በቀጣናው ለክፉ ተግባር መጠለያ የሆኑት ጦር ሰፈሮች አይኖሩም እንዲሁም ተጨማሪ ወታደራዊ ሰፈሮች አይመሠረቱም” በማለት “አሜሪካ ከቀን ወደ ቀን ከዚህ በፊት ከነበረችበት ደረጃ እየወረደች ነው” ብለዋል።

    ጠቅላይ መሪው ባለፉት ወራት በተካሄደው ጦርነት አሜሪካ እና እስራኤል ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው በመጥቀስ “በኢራን ከባድ ምት እስራኤል አቅመ ቢስ” እንደሆነች እና አሜሪካም “ከባድ ጥፊ እንደቀመሰች” ገልጸዋል።

  14. ኢራን “የአጸፋ እርምጃ መውሰድ ተገቢ እና የማይቀር” መሆኑን ገለጸች

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ፤ በአሜሪካ ጦር ለሚፈጸም ማንኛውም የተኩስ አቁም ጥሰት “የአጸፋ እርምጃ መውሰድ ተገቢ እና የማይቀር” እንደሆነ አስታወቀ።

    እስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ አሜሪካ በደቡብ ኢራን የከፈተችውን ጥቃት ሳይጠቅስ በሕዝብ ግንኙነቱ በኩል ባወጣው መግለጫ “የአሜሪካ ጦር በቀጣናው ጣልቃ ገብነቱን እና ጠብ ጫሪነቱን ቀጥሎ በፐርዥያ ባሕረ ሰላጤ ወደ ኢራን የአየር ክልል እና ወደ እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ መከላከያ ሰፈር ገብቷል” ብሏል።

    “በጥንቃቄ የደኅንነት ቅኝት ካደረግን በኋላ የግዛት ሉዓላዊነታችንን ለመከላከል ኤምኪው-9 ድሮን መትተን ጥለናል” ሲልም አክሏል።

    አርኪው-4 ድሮን እና ኤፍ-35 ተዋጊ ጄት እንደመታ እና እርምጃው “በውሃ የተሸፈነውን አካባቢ ጥለው እንዲሸሹ እንዳስገደዳቸው” አስታውቋል።

    እነዚህ ጥቃቶች መቼ እና የት እንደተፈጸሙ በግልጽ አላስቀመጠም።

    የአሜሪካ ጦር ባወጣው መግለጫ በደቡብ ኢራን የሚገኙ የሚሳዔል ማከማቻዎች እና ፈንጂ የሚጥሉ ጀልባዎችን ዒላማ በማድረግ አዲስ ዙር ጥቃት መክፈቱን ይፋ አድርጓል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ጥቃቱ “ራስን መከላከል” እንደሆነ ገልጾ፤ ዓላማውም “በኢራን ኃይሎች ስጋት የተጋረጠባቸው ወታደሮቻችንን መከላከል ነው” ብሏል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን ትናንት ምሽት በባንደር አባስ የወደብ ከተማ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ፍንዳታ መሰማቱን ዘግበዋል።

  15. ኳታር ለኢራን 12 ቢሊየን ዶላር ልትሰጥ ነው መባሉን አስተባበለች

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር ከስምምነት እንድትደርስ ለማድረግ 12 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ሃሳብ አቅርባለች መባሉን መሠረተ ቢስ በማለት ኳታር አስተባበለች።

    የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማጂድ አል እንሳሪ በኤክስ የሶሻል ሚዲያ መድረክ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ የአገራቸው ዲፕሎማሲያዊ ሚና በግልጽ የሚታወቅ መሆኑን በመጥቀስ የወጡ ዘገባዎች ያላትን “ታማኝ ዓለም አቀፍ የሰላም ጥረቶች አመቻችንት የሚያጠለሽ ነው” ብለዋል።

    ይህ የሚኒስትሩ አስተያየት የተሰማው በርካታ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ጋር የሚደረገውን ድርድር ለመቋጨት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኳታርን እየጎበኙ ባለበት ጊዜ ነው።

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር በኳታር ያለውን ጨምሮ በውጭ አገራት እንዳይንቀሳቀስ የታገደባት ሃብቷ እንዲለቀቅ እየጠየቀች ነው። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት አገሪቱ በኳታር ውስጥ 12 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ ታግዶባታል።

    በኒውክሌር መረሃ ግብሯ ምክንያት ከምዕራበባውያን በተለይም ከአሜሪካ ጋር በገባችው እሰጣ ገባ ተደራራቢ ዕቀባ የተጣለባት ኢራን ባለፈው የካቲት ወር በአሜሪካ እና በእስራኤል በተከፈተባት ጥቃት ጦርነት ውስጥ ገብታለች።

    ለጥቂት ወራት የዘለቀው ጦርነት በተኩስ አቁም ጋብ ብሎ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ድርድር እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ ኢራን ከስምምነት ለመድረስ በቅድመ ሁኔታ ካቀረበቻቸው ነጥቦች መካከል በውጭ ያለው ሃብቷ እንዲለቀቅላት የሚጠይቀው ይገኝበታል።

  16. በኢራን ጦርነት ምክንያት በመላው ዓለም የሚሳዔል መከላከያ ሥርዓት መዳከሙን ዘለንስኪ ተናገሩ

    የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ “በኢራን ጦርነት ምክንያት በመላው ዓለም የባለስቲክ ሚሳዔል መቃወሚያ ሥርዓት እጥረት ተፈጥሯል” አሉ።

    ለተፈጠረው እጥረት “መፍትሔ መገኘት አለበት” ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።

    ዘለንስኪ አክለውም “የዩክሬንን የአየር መከላከያ ለማጠናከር ከሁሉም አካላት ጋር እየሠራን እንገኛለን። ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው” ብለዋል።

    በዩክሬን መዲና ኪቭ “ስልታዊ ጥቃቶች” እንደምትሰነዝር ያስታወቀችው ሩሲያ በበኩሏ የውጭ አገራት ዜጎች ከተማዋን ለቅቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ ሰጥታለች።

    የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ፤ አሜሪካ ለአገራቸው ተጨማሪ ድጋፍ የምታደርግበትን መንገድ በተመለከተ ውይይቶች ይቀጥላሉ ብለዋል።

    አውሮፓ በቂ የሚሳዔል መቃወሚያ ሥርዓት እንዲኖራት በሚል ዩክሬን መሣሪያውን የምታመርትበትን ፍጥነት መጨመሯንም ገልጸዋል።

  17. ማርኮ ሩቢዮ ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ የመድረስ ዕድል መኖሩን በድጋሚ ገለጹ

    ዋሽንግተን ቴህራን ላይ አዲስ ጥቃት ብትከፍትም ስምምነት ላይ መድረስ የሚቻልበት ዕድል “አሁንም እንዳለ” የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስር ማርኮ ሩቢዮ ተናገሩ።

    አሜሪካ ያደረሰችው ጥቃት የኢራን የሚሳዔል ሥርዓት እና ጀልባዎች ላይ ጉዳት ቢያደርስም ሩቢዮ ዛሬ ባደረጉት ንግግር የስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል ብለዋል።

    “በኳታር በሚደረገው ውይይት ለውጥ የሚመጣ ከሆነ እናያለን” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ፕሬዝዳንቱ ግሩም ስምምነት ላይ ይደርሳሉ፤ አልያም ስምምነት አይኖርም” ሲሉ ገልጸዋል።

    በኳታር በሚደረገው ውይይት ላይ የቀረበው የሰላም ዕቅድ ውስጥ ያለው “የቃላት አጠቃቀም እና ምርጫ መታየት ስላለት” ንግግሩ ቀናት ሊወስድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት እንዳለበት አስረግጠው የተናገሩት ማርኮ ሩቢዮ “እየሆነ ያለው ነገር ሕገ ወጥ ነው። ዓለም ላይ አለመረጋጋት ፈጥሯል፤ ተቀባይነትም የለውም” ሲሉ አክለዋል።

  18. በኪቭ “ስልታዊ ጥቃት” ለመሰንዘር የዛተችው ሩሲያ የውጭ ዜጎች ከከተማዋ እንዲወጡ አሳሰበች

    በዩክሬን መዲና ኪቭ አዲስ “ስልታዊ ጥቃቶች” እንደምትሰነዝር ያስታወቀችው ሩሲያ፤ የውጭ አገራት ዜጎች ከተማዋን ለቅቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ ሰጠች።

    ሩሲያ ከቀናት በፊት በዩክሬን መዲና ከፍተኛ ጥቃት ያደረሰች ሲሆን፤ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የከፋው ነው ተብሏል።

    ሩሲያ በቀጣይ የምትፈጽመው ጥቃት “ውሳኔ የሚሰጥባቸው ማዕከላት ላይ ያነጣጠረ” መሆኑን አስታውቃለች።

    የሰው አልባ አውሮፕላን ማምረቻ ፋብሪካዎችን ጨምሮ ሌሎችም ተቋማት ዒላማ እንደሚደረጉ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    የውጭ አገራት ዜጎች እና ዲፕሎማቶች ኪቭን “በተቻለው ፍጥነት” ለቅቀው እንዲወጡም መሥሪያ ቤቱ አሳስቧል።

    ዩክሬናውያን ከአስተዳደራዊ እና ወታደራዊ ተቋማት ሕንጻዎች እንዲርቁም አስጠንቅቋል።

    ዩክሬን በበኩሏ የሩሲያ ዛቻ “ሃፍረተ ቢስ የሆነ ጫና ማሳደሪያ መንገዷ ነው” ስትል አጣጥላለች።

    የዩክሬን አጋር አገራት ሞስኮ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ እንዲጨምሩም ጠይቃለች።

    ሩሲያ ለውጭ አገራት ዜጎች ማስጠንቀቂያ መስጠቷ “የውጭ ዲፕሎማቶች መቀመጫዎች ከዒላማዎቿ መካከል እንደሚገኙበት ያሳያል” ስትልም ዩክሬን ስጋቷን ገልጻለች።

  19. እስራኤል ሄዝቦላህ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት እንደምታጠናክር ኔታንያሁ ተናገሩ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሄዝቦላህ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ጦር በመላው ሊባኖስ አዲስ ዙር ጥቃት ማድረስ መጀመሩን አስታወቀ።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በምስራቅ ሊባኖስ በሚገኘው ቤካ ሸለቆ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ጥቃት በመክፈት ሄዝቦላህን እየመታ መሆኑን ገልጿል።

    ሄዝቦላህ በበኩሉ የእስራኤል ወታደሮች፣ ታንኮች፣ የጦር ሰፈሮች፣ ሕንፃዎች እና ሌሎች ስፍራዎችን ዒላማ ያደረጉ 22 የድሮን እና የሮኬት ጥቃቶችን በመፈጸም አጸፋውን መመለሱን አስታውቋል።

    ሊባኖስ እና እስራኤል በዚህ ወር መጀመሪያ የደረሱበትን ተኩስ አቁም በ45 ቀናት ለማራዘም ስምምነት ቢፈጽሙም ውጊያው ቀጥሏል።

    ኔታንያሁ ሰኞ ምሽት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፤ እስራኤል “ከሄዝቦላህ ጋር ጦርነት ላይ” እንደሆነች ተናግረዋል። ሠራዊቱ “አድቃቂ ምት” እንዲፈጽም ማዘዛቸውንም ገልጸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እስራኤል በከፈተችው ወታደራዊ ዘመቻ "ከ600 በላይ አሸባሪዎች” መገደላቸውንም ተናግረዋል። "አሁን ከእኛ የሚጠበቀው ጥቃቱን ማጠናከር እና ጥንካሬውን ይበልጥ መጨመር ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

    ቤዛልል ስሞትሪች እና ኢታማር ቤን ግቪር የተባሉት ሁለት ቀኝ አክራሪ የእስራኤል ሚኒስትሮች ሊባኖስ ውስጥ የሚካሄደውን ጨምሮ የጦሩ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲስፋፋ ጠይቀዋል።

    ሰኞ ዕለት ድሮኖች እና ሮኬቶችን በመጠቀም በደቡብ ሊባኖስ እንዲሁም በሰሜን እስራኤል የሚገኙ ስፍራዎችን ማጥቃቱን የገለጸው ሄዝቦላህ፤ እርምጃውን የወሰደው በእስራኤል “የተኩስ አቁም ጥሰት” ምክንያት እንደሆነ ተናግሯል።

    ይፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሌላቸው ሊባኖስ እና እስራኤል በሚቀጥለው ሳምንት ዋሽንግተን ውስጥ ተጨማሪ ድርድር ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል። የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን፤ የእስራኤል ጦር ከደቡብ ሊባኖስ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

  20. የአሜሪካ ጦር በደቡብ ኢራን አዲስ ጥቃት መክፈቱን አስታወቀ

    የአሜሪካ ጦር በደቡብ ኢራን የሚገኙ የሚሳዔል ማከማቻዎች እና ፈንጂ የሚጥሉ ጀልባዎችን ዒላማ በማድረግ አዲስ ዙር ጥቃት መክፈቱን አስታወቀ።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ “ራስን መከላከል” እንደሆነ አስታውቋል። ዓላማውም “በኢራን ኃይሎች ስጋት የተጋረጠባቸው ወታደሮቻችንን መከላከል ነው” ብሏል።

    የማዕከላዊ ዕዙ ቃል አቀባይ ካፕቴን ቲም ሀውኪንስ “የአሜሪካ ጦር በተኩስ አቁሙ መሠረት ቢታቀብም ወታደሮችን ይከላከላል” ብለዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጊ ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ድርድር መሻሻል ቢያሳይም ግጭቱን የሚያስቆም ስምምነት ላይ “በቅርብ ጊዜ እንደማይደረስ” መግለጻቸው ይታወሳል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት እንደ አዲስ የተከፈተው ጥቃት የተፈጸመው በደቡባዊ የኢራን ግዛት የምትገኘው ባንዳር አባስ የወደብ ከተማ ላይ ነው።

    የወደብ ከተማዋ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኘው የኢራን ባሕር ኃይል መቀመጫ መሆኗን የኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ ይጠቁማል።

    የኢራን ብሔራዊ ጣቢያ እንደዘገበው የከተማዋ ባለሥልጣናት ፍንዳታ መስማታቸውን ተከትሎ ምርመራ ማካሄድ ጀምረዋል።

    ኢራን ከአሜሪካ ለተከፈተባት ጥቃት እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም። የአሁኑ ጥቃት በሁለቱ አገራት የሰላም ድርድር ላይ ምን ጫና እንደሚያሳድርም ግልጽ አይደለም።

    ጥቃቱን ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ “አሁንም ቢሆን ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል” ብለዋል።

    ትናንት የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ውይይት አድርገዋል።