'በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ' በኤአይ ክትባት መሠራቱ ተገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ከተለያዩ የቫይረስ ዓይነቶች እንዲሁም ከወረርሽኞች የሚከላከል ክትባት መሠራቱን ተመራማሪዎች ገለጹ።

በኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ጥናት ያካሄደው ቡድን እንዳለው ለመጀመሪያ ጊዜ የክትባት ዋነኛ ክፍል በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ተሠርቶ ውጤታማነቱ በሰዎች እንዲፈተሽ ተደርጓል።

ክትባቱ ሁሉንም የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች አንዲሁም ቀጣዩን ወረርሽኝ የሚያስነሱ እንሰሳትን የሚያጠቁ ቫይረሶች መከላከል እንዲችል ተደርጎ እንደተሠራ ሳይንቲስቶቹ አስታወቀዋል።

የክትባት ምርምሩ ገና መጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን የምርምር ቡድኑ ለጉንፋን እና ኢቦላ ክትባቶች ለመሥራት ሙከራ እያደረገ ነው። ክትባቶች ሰውነት ኢንፌክሽንን ለይቶ እንዲዋጋ ያስችላሉ።

አንዳንድ ቫይረሶች ባህሪያቸውን ስለሚለዋውጡ ክትባቶች ውጤታማ ሳይሆኑ ይቀራሉ። ስለዚህም በየጊዜው ክትባቶችን ማሻሻል ያስፈልጋል።

የኮቪድ እና ጉንፋን ክትባቶች ላይ በየጊዜው ማሻሻያ የሚደረገውም ለዚህ ነው።

ከተመራማሪዎቹ አንዱ ፕ/ር ጆናታን ሄኒ "ሁሌም ወደኋላ እንቀራለን። አሁን ግን ቀድመን ለመገኘት እየሞከርን እንገኛለን" ብለዋል።

የሳይንቲስቶቹ ግብ ወረርሽኞች ከመነሳታቸው በፊት ማስቆም እንደሆነ አስረድተዋል።

ብዙውን ጊዜ ክትባቶች በመሰራጨት ላይ ያለ ቫይረስን ለመከላከል ይሠራሉ።

አጥኚዎቹ ከኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች የሚታወቁትን የዘረ መል ዓይነቶች በመውሰድ ባህሪውን ለመገንዘብ ሞክረዋል።

የዘረ መል ዓይነቶቹ ላይ ምርምር የተደረገው በኤአይ ነው። በተገኘው ውጤት መሠረት ሁሉንም የቫይረሱን ዝርያዎች የሚያክም "ልዕለ ኃያል" መከላከያ ክትባት ለመሥራት ተሞክሯል።

ቫይረሱ አዳዲስ ዝርያዎችን ቢፈጥር ወይም አዲስ ዓይነት ኢንፌክሽን ከእንስሳት ወደ ሰዎች ቢሻገር ማከም የሚቻልበት መንገድ ነው።

የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚያዳብረው የክትባት ክፍል አንቲጀን (Antigen) ይባላል።

ፕ/ር ጆናታን እንደሚሉት፤ በኤአይ የተሠራ አንቲጀን በሰዎች ሙከራ ሲደረግበት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

"ቴክኖሎጂው ሁላችንንም አስደንቆናል። ለሰው ልጆች ትልቅ አስተዋጽኦ እናበረክታለን" ብለዋል።

"ዓላማችን ከለላ የሚሰጡን ክትባቶች መሥራት ነው። የሚጠብቁን አሁን ካሉት ቫይረሶች ብቻ ሳይሆን ለወደፊት ከሚነሱትም ጭምር ነው" ሲሉም አክለዋል።

የወረርሽኝ ቅድመ መከላከል መንገድን የለወጠ አካሄድ መሆኑን ፕ/ር ጆናታን አስረድተዋል።

በ39 ሰዎች ላይ የተደረው ሙከራ ክትባቱ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ፈትሿል።

ሁለተኛው ዙር ሙከራ 200 ሰዎችን ያሳተፈ ሲሆን፤ ክትባቱ ከሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም ጋር ያለው ትስስር ተጠንቶበታል።

በ 'ጆርናል ኦፍ ኢንፌክሽን' መጽሔት የወጣው የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው፤ በሽታን በመከላከል ረገድ "መጠኑን የጠበቀ" ውጤት አሳይቷል።

ሙከራውን ካደረጉት ሳይንቲስቶች አንዱ የሆኑት ፕ/ር ሶል ፋውስት "ኤአይ ክትባት የመሥራት አቅም አለው። በጣም ያስደስታል" ብለዋል።

"ወረርሽኞችን ለመግታት እና ባህሪያቸውን የሚለዋውጡ የቫይረስ ዓይነቶችን ለማከም መዋል ይችላል" በማለትም አክለዋል።

በየዓመቱ መሻሻል የሚጠበቅበት ወቅትን ጠብቆ ለሚነሳ ጉንፋን የተሠራ ክትባት በእንሰሳት ላይ ተሞክሯል።

አእዋፋትን የሚያጠቃው ኤች5ኤን1 የወፍ ጉንፋን (H5N1-bird flu) ወደ ሰዎች ሊሻገር ይችላል በሚልም በሙከራው ተካትቷል።

የኢቦላ ዝርያዎችን ጨምሮ ለሌሎችም ተመሳሳይ ሕመሞች ክትባት ለማግኘት ሙከራው ቀጥሏል።

አሁን ላይ በዴሞክራቲክ ኮንጎ እየተሰራጨ ያለው የኢቦላ ዝርያ ገና ክትባት አልተገኘለትም።

የኦክስፎርድ ቫክሲን ግሩፕ ኃላፊ ፕ/ር አንዲ ፖላርድ እንደሚሉት፤ እየተሠሩ ያሉት ምርምሮች በእንሰሳት ላይ የሚደረግ ጥናትን ለውጠዋል።

"አስደናቂ ነው። ሰዎች እንዲህ ባለ መንገድ በሽታን መከላከል እንደሚችሉ አይታወቅም ነበር" ብለዋል።

የክትባቱ ውጤታማነት በትክክል የሚታወቀው በሰዎች ላይ ሙከራ ሲደረግ መሆኑን ፕ/ር አንዲ ጠቅሰዋል።

ኤአይ በክትባት ምርምር "ታሪክ ለዋጭ" እንደሚሆንም ተናግረዋል። ክትባቶች በፍጥነት እንዲሠሩ በማገዝ "ሕይወት እንደሚታደግ" ገልጸዋል።

የናሽናል ኢንስቲትዩት ፎር ኸልዝ ኤንድ ኬር ሪሰርች ኃላፊ ፕር ማርቲን ናይት በበኩላቸው በኤይ ክትባት መሠራቱ "ታላቅ ስኬት ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።