ቀጥታ, ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ዛሬም ኢራንን ክፉኛ እንመታለን” አሉ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ሌሊት ከተፈጸመው በተጨማሪ ጦራቸው ረቡዕም በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት እንደሚፈጸም ዛቱ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ዛሬም ኢራንን ክፉኛ እንመታለን” አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ረቡዕ ባደረጉት ንግግር ኢራንን “ክፉኛ እንመታለን” ሲሉ ዛቱ።

    ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ “ቢቃረቡም” ኢራን “መዘግየቷን” ጠቅሰዋል።

    “ትናንት በጣም ደብድበናቸዋል። ዛሬም ክፉኛ እንመታቸዋለን” በማለት ፕሬዝዳንቱ አስጠንቅቀዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ “የትኛውንም ጥቃት ወይም ዛቻ ችላ ብለን አናልፍም” ብለዋል።

    ትራምፕ ግን ኢራን ድርድሩን “በጣም በማጓተቷ አሁን ዋጋውን ትከፍላለች” ሲሉ ተናግረዋል።

    “የኢራን ጦር ተዳክሟል። የባሕር እና የአየር ኃይላቸው አለ ለማለት አያስደፍርም። ሙሉ በሙሉ ወድቀዋል” በማለት በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።

    ኢራን የአሜሪካ ተዋጊ ሄሊኮፕተርን መትታ መጣሏን ተከትሎ አሜሪካ የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች።

    በምላሹም ኢራን በባሕረ ሰላጤው አገራት የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ዒላማ ያደረጉ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን መፈጸሟን አስታውቃለች።

  2. እስራኤል በሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 17 ሰዎች መገደላቸው ተዘገበ

    እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 17 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    የሊባኖስ ብሔራዊ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው ታይር ዳባ በተባለ አካባቢ በተከታታይ በተፈጸመ ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል።

    ኢራን የምትደግፈው ሄዝቦላህ በደቡብ ሊባኖስ የእስራኤል ወታደሮች በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ተጨማሪ ጥቃቶች መፈጸሙን አስታውቋል።

    ትናንት ማክሰኞ እስራኤል በሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት 15 ሰዎች መገደላቸውም ተዘግቧል።

    እስራኤል በሄዝቦላህ ላይ የከፈተችውን ዘመቻ እንዳትገፋበት ኢራን ብታሳስብም እስራኤል ጥቃት መፈጸሟን ቀጥላለች።

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር ያለው ጦርነት የሚያከትመው ስምምነታቸው ሊባኖስን የሚያካትት ከሆነ ብቻ መሆኑን ገልጻለች። ድርድሩን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውስብስብ አድርገውታል ስትልም ከስሳለች።

    ትራምፕ በበኩላቸው ኢራን ድርድሩን “በጣም በማጓተቷ አሁን ዋጋውን ትከፍላለች” ሲሉ ዝተዋል።

    ኢራን የአሜሪካ ተዋጊ ሄሊኮፕተርን መትታ መጣሏን ተከትሎ አሜሪካ የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች።

    በምላሹም ኢራን በባሕረ ሰላጤው አገራት የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ዒላማ ያደረጉ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን መፈጸሟን አስታውቃለች።

  3. ኢራን ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው ድርድር የሚቀጥልበትን መንገድ እንደምታጤን አስታወቀች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፤ ቴህራን ከዋሽንግተን ጋር የምታደርገው ድርድር የሚቀጥልበትን መንገድ እንደምታጤነው አስታወቁ።

    ኢራን የአሜሪካን ሄሊኮፕተር መትታ መጣሏን ተከትሎ አሜሪካ የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች።

    ቃል አቀባዩ ኢስማኤል ባጋይ፤ ኢራን እና አሜሪካ የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ተከትሎ “ዲፕሎማሲ በባቦ ሜዳ አይከናወንም። የዲፕሎማሲ ሒደት እንዲቀጥል ለማስቻል በተወሰነ መጠን ለእንቅስቃሴ ክፍተት መስጠት ያስፈልጋል” ብለዋል።

    አሜሪካ “የሚቃረኑ መልዕክቶች በማስተላለፍ የድርድር ሒደቱን እየጎዳች ነው” ሲሉ ወንጅለዋል። “አቋም እና ፍላጎት በመለወጥ” እንዲሁም “በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም በመጣስም” አሜሪካን ከስሰዋል።

  4. ኢራን “ድርድሩን በማጓተቷ ዋጋ ትከፍላች” ሲሉ ትራምፕ አስጠነቀቁ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ድርድሩን “በጣም በማጓተቷ አሁን ዋጋውን ትከፍላለች” ሲሉ አስጠነቀቁ።

    “የኢራን ጦር ተዳክሟል። የባሕር እና የአየር ኃይላቸው አለ ለማለት አያስደፍርም። ሙሉ በሙሉ ወድቀዋል” በማለት በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።

    ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ኢራን ታወራለች እንጂ ምንም አትከውንም። የመካከለኛዋ ምሥራቅ ጉልበተኛ ሞታለች” ብለዋል።

    “እነሱን የሚጠቅም ስምምነት ላይ ለመድረስ ለድርድር በጣም ረዥም ጊዜ ወስደዋል። አሁን ዋጋውን ይከፍላሉ” በማለትም ዝተዋል።

    ኢራን በባሕረ ሰላጤው አገራት ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ዒላማ እንደምታድርግ አስጠንቅቃለች።

    ኢራን የአሜሪካን ሄሊኮፕተር መትታ መጣሏን ተከትሎ ዋሽንግተን የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች።

  5. አሜሪካ እንዳይገባ የተከለከለው ሶማሊያዊ የዓለም ዋንጫ ዳኛ ሞቃዲሾ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት

    የዓለም ዋንጫን እንዲዳኙ ከተመረጡት ዳኞች ማከከል አንዱ ሆነው ሶማሊያዊ ዳኛ ኦማር አርታን አሜሪካ እንዳይገባ ከተከለከለ በኋላ ወደ አገሩ ሲመለስ ደመቅ አቀባበል ተደረገለት።

    በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያው ሶማሊያዊ ዳኛ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው አርታን ሞቃዲሾ ሲደርስ ሶማሊያውያን የአገራቸውን ስም እንዲከላከሉ ጥሪ አቀረበ።

    አርታን ሞቃዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የአገሪቱ ባለሥልጣናት፣ የብሔራዊ እግር ኳስ ፌደሬሽን ተወካዮች እና የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል።

    በአውሮፕላን ማረፊያው ከተገኙ ሰዎች መካከል የቤተሰብ አባላቱም ይገኙበታል ተብሏል።

    በአውሮፕላን ማረፊያው አጭር ንግግር ያደረገው ዳኛው ለተደረገለት አቀባበል አመስግኖ በሚቀጥለው ዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ያለውን ተስፋ ገልጿል።

    “ቃል የምገባላችሁ ነገር ፈጣሪ ካለ በሚቀጥለው እሳተፋለሁ። እናም ሶማሊያውያን በዚያ ደስተኛ ይሆናሉ፤ ሁላችንም የሶማሊያን ስም መከላከል አለብን” ብሏል።

    አርታን በዓለም ዋንጫ ላይ ዳኛ ሆኖ የተመረጠ የመጀመሪያው ሶማሊያዊ ሲሆን፣ ሰኞ ዕለት ማያሚ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሰ በኋለ እንዳይገባ በመከልከሉ በሌላ ሰው ተተክቷል።

    አርታን ወደ አሜሪካ እንዳይገባ ለምን እንደተከለከለ በይፋ ባይገለጽም፤ ነገር ግን የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የጉዞ እገዳ ከጣለባቸው በርካታ አገራት መካከል ሶማሊያ አንዷ ናት።

    በአውሮፕላን ማረፊያው ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ወጣቶች በአገራቸው ተስፋ እንዳይቆርጡ መክሯል።

    “ሶማሊያ ጥሩም ሆነች መጥፎ የኛ ናት፤ ፓስፖርቱ የኛ ነው፤ የምንጋራው እኛው ነን። በጋራ ሆነን እንከላከለዋለን” ብሏል።

    ዓለም አቀፉ ዳኛ የተሰማውን ከመግlጽ ውጪ በስፋረው ከተገኙ ጋዜጠኞች ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ አልሰጠም።

    ኦማር አርታን ዛሬ ከሰዓት በሞቃዲሾ ውስጥ የሚያካሄድ ጨዋታ ላይ ተገኝቶ አቀባበል ይደረግለታል እንዲሁም ግጥሚያውን ይመለከታል ተብሎ ይጠበቃል።

  6. ኢራን የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች የሚገኙባቸው የባሕረ ሰላጤው አገራትን ዒላማ እንደምታድርግ አስጠነቀቀች

    ኢራን በባሕረ ሰላጤው አገራት ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ዒላማ እንደምታድርግ እና አገራቱ ግዛታቸውን አሜሪካ ለምትፈጽምባት ጥቃት እንዳይፈቅዱ አስጠነቀቀች።

    አሜሪካ እና ኢራን የአጸፋ ጥቃት እየፈጸሙ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ረቡዕ እንዳለው ጎረቤቶቿ የፋርስ ባሕረ ሰላጤው አገራት አሜሪካ እና እስራኤል ከቀጣናው አገራት በመነሳት የሚፈጽሙባትን ጥቃት የማስቀረት “ሕጋዊ እና ሞራላዊ ኃላፊነት” አለባቸው ብላለች።

    በፕሬዝዳንት ትራምፕ ትዕዛዝ የአሜሪካ ኃይሎች በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ኢራን በምላሹ በፋርስ ባሕረ ሰላጤው አገራት ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን መፈጸሟን አስታውቃለች።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እንዳለው በዛሬው ጥቃት በባህሬን የሚገኘው አምስተኛው የአሜሪካ ባሕር ኃይል ምድብን፣ ኩዌት የሚገኘውን አሊ አል ሳሌም የአየር ኃይል ሰፈርን እና ዮርዳኖስ ውስጥ የሚገኘውን አል አዝራቅ የአየር ኃይል ሰፈርን በድሮን እና በሚሳዔሎች መትቷል።

    የዮርዳኖስ ጦር ኃይል ስለጥቃቱ ባወጣው መግለጫ የአየር መከላከያ ሥርዓቱ አምስት ሚሳዔሎችን አየር ላይ በመምታት ማክሸፉን እና በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት አለመድረሱን አስታውቋል።

    አሜሪካ ማክሰኞ ዕለት ለተመታባት ሄሊኮፕተር አጸፋ በደቡባዊ ኢራን የፈጸመችው ጥቃት የኮሚዩኒኬሽን ማማዎችን እና የውሃ ማከማቻ ግድቦችን ማውደሙን የኢራን አብዮታዊ ዘብ ገልጿል።

  7. ኔታንያሁ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ዳግም እንደሚወዳደሩ ፓርቲያቸው አስታወቀ

    ትራምፕ ቤንያሚን ኔታንያሁ ዳግም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ለመወዳደር የሚችሉ እንደማይመስላቸው ቢገልጹም በዚህ ዓመት ለዳግም ምርጫ እንደሚወዳደሩ ፓርቲያቸው አስታወቀ።

    የኔቴንያሁ ሊኩድ ፓርቲ ባወጣው አጭር መግለጫ "በምርጫው ይሳተፋሉ፤ ከፈጣሪ ጋር ያሸንፋሉ" ሲል አስታውቋል።

    ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ በይፋ ባይገለጽም በጥቅምት ወር እንደሚሆን ተገምቷል።

    ቀደም ሲል የኤቢሲ የዋሺንግተን ዘጋቢ ጆናታን ካርል በኤክስ ገጹ ላይ ትራምፕ ኔታንያሁ ስለመወዳደራቸው እርግጠኛ አለመሆናቸውን እንደነገሩት ጽፎ ነበር።

    “አላውቅም፤ በጣም አስደናቂ የሥልጣን ጊዜ ነበረው፤ መቀጠል ይፈልጋል?” ማለታቸውን ጋዜጠኛው በማኅበራዊ ድረ ገፁ ላይ አጋርቶ ነበር።

    እስራኤል የምታካሄደው ይህ ምርጫ የአገሪቱ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ውድቀት ነው ከተባለው የመስከረም 26/2016 ዓ.ም. የሐማስ ጥቃት ወዲህ ሲካሄድ የመጀመሪያው ነው።

    ኔታንያሁ ወደ ሥልጣን በአውሮፓውያኑ 2022 ታኅሣሥ ወር ከመጡ ወዲህ ከፍተኛ መንገጫገጭ አጋጥሟቸዋል።

    በጋዛ፣ በሊባኖስ እና በኢራን ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት የፀረ መንግሥት ተቃውሞዎች ተካሄደውባቸዋል።

    የሕዝብ አስተያየት መስጫ መድረኮች አገሪቱን ለመምራት ከሌሎች ጋር ጥምረት የመሠረተው ፓርቲያቸው ያለው ተቀባይነት እየቀነስ መምጣቱን ያሳያሉ።

    ኔታንያሁ ከአሜሪካ ጋር በመሆን ኢራን ላይ ጦርነት ቢከፍቱም በቅርብ ጊዜ ግን ሁለቱ መሪዎች የተካረረ የሰልክ ምልልስ አድርገዋል።

    ሁለቱ መሪዎች አሁንም የቅርብ አጋር ቢሆኑም ትራምፕ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትወስደውን ወታደራዊ እርምጃ እንድታቆም ይፈልጋሉ።

    ለዚህ ምንክያታቸው ደግሞ ከኢራን ጋር እያደረጉት ያለው ድርድር ነው።

    ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የቀረበባቸው የሙስና ክስ እንዲነሳላቸው ሲጠይቁ ተሰምተዋል።

  8. የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ከኢራን ጋር በሳምንታት ወይም በመጪዎቹ ወራት ከስምምነት እንደሚደረስ ተናገሩ

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄ.ዲ ቫንስ አገራቸው ከቴህራን ጋር በምታደርገው ድርድር የኢራንን የኒውክሌር መረሃ ግብርን ጉዳይ “በዘለቄታው” የሚፈታ ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረቧን ተናገሩ።

    ሁለቱ አገራት ላለፉት ወራት አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ጎን ለጎን ጦርነቱን ለማስቆም ድርድር እያደረጉ ቆይተው ነው አሁን ወደ መቋጫው መደረሳቸውን ምክትል ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት።

    በድርድሩ ወቅት የኢራን የኒውክሌር ይዞታ ያላስማማ ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ አሁን ቫንስ እንዳሉት ወደ መግባባት መቃረባቸውን እና በቀጣይ ሳምንታት ወይም ወራት ከስምምነት እንደሚደረስ ገልጸዋል።

    "በአሁኑ ጊዜ ከኢራን ጋር ለአሜሪካ ምጣኔ ሀብት ጥሩ የሆነው ስምምነት ላይ ለመድረስ እየተቃረብን እንደሆነ ይሰማኛል። ስምምነቱ የኢራን የኒውክሌር ጉዳይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሥልጣን ላይ አስከሚቆዩበት ጊዜ ድረስ ብቻ የሚፈታ ሳይሆን በዘላቂነት አገሪቱ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት የሚያደርግ ነው” ሲሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ቫንስ ለሲቢኤስ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

    ይህም የመንግሥታቸው የፖሊሲ ግብ መሆኑን የገለጹት ቫንስ “ያንን ግብ ለማሳካት በጣም የተቃረብን ይመስለኛል። ነገር ግን ሌሎች በርካታ የቀሩ ጉዳዮች አሉ። ለእነዚያም መቋጫ ለማበጀት ጥረታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር በአሜሪካ ከሚካሄደው ወሳኙ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በፊት ከስምምነት እንደሚደረስ እርግጠኛ መሆናቸውን አመልክተዋል።

  9. ኢራን ሌሊቱን ለተፈጸመባት ጥቃት አጸፋ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን መታች

    አሜሪካ ተመትቶ ለወደቀው ሄሊኮፕተሯ አጸፋ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ በባሕረ ሰላጤው አገራት ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን መፈጸሙን የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አስታወቀ።

    ሠራዊቱ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው በቀጣናው የሚገኙ የአሜሪካ “አምስተኛው ምድብ ባሕር ኃይል” የራዳር ሥርዓትን እና ጦር ሰፈሮችን በበርካታ ድሮኖች መምታቱን አስታውቋል።

    የኢራን ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው የአገሪቱ ሠራዊት ጥቃቱን አሜሪካ በደቡባዊ ኢራን ውስጥ በሚኖሩ ዜጎች ላይ ለፈጸመችው “ጥቃት” የተሰጠ “የአጸፋ ምላሽ” በማለት በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

    የአሜሪካ ምንጮች ጥቃቱን በተመለከተ ባወጡት ዘገባ ኢራን በአራት ሚሳዔሎች እና በበርካታ ድሮኖች በባህሬን፣ በኩዌይት እና በዮርዳኖስ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት ፈጽማለች ብለዋል።

    ለኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቅርብ የሆነው ታስኒም የዜና ወኪል እንደዘገበው ኢራን በዮርዳኖስ በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ፈጽማለች። በዚህም ዋነኛ ዒላማ የነበረው እጅግ ዘመናዊ የሆኑት የአሜሪካ ኤፍ-35 ተዋጊ ጀቶች የሚቀመጡበት መጠለያ መሆኑን ዘቡን ጠቅሶ ዘግቧል።

    በተጨማሪም ፋርስ የተባለው የኢራን ዜና ወኪል አብዮታዊ ዘቡ በፋርስ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ የሚገኙ "21 የአሜሪካ የአየር እና የባሕር ኃይል ጦር ሰፈሮች ዒላማ ተደርገዋል” ማለቱን ገልጿል።

  10. አሜሪካ ለተመታባት ሄሊኮፕተር አጸፋ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ሠራዊቷ አስታወቀ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቴህራን የአሜሪካ ሄሊኮፕተርን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መትታ ጥላለች በማለት ከከሰሱ በኋላ ሠራዊታቸው በኢራን ላይ ጥቃት ፈጸመ።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) እንዳስታወቀው ለተመታው አፓቼ ሄሊኮፕተር አጸፋ ማክሰኞ ሌሊት በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸም ጀምሯል።

    ዕዙ "ዘመቻው በኢራን ለተፈጸመው ተቀባይነት የሌለው ጠብ አጫሪነት ተመጣጣኝ ምላሽ ነው" ያለ ሲሆን፣ በባሕረ ሰላጤው ዳርቻዎች እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ፍንዳታዎች መሰማታቸው ተዘግቧል።

    የተመታው ሄሊኮፕተር ሁለት አብራሪዎች በአሜሪካ የባሕር ላይ ድሮን አማካይነት መትረፋቸው እና ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ገልጸዋል።

    ኢራን ሄሊኮፕተሩን በድሮን መምታቷን የአሜሪካ ባለሥልጣናት የተናገሩ ሲሆን፣ ነገር ግን ጥቃቱ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም ብለዋል።

    ክስተቱ ማጋጠሙ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ቢዘገብም የአገሪቱ መንግሥት ግን ተመትቶ ለወደቀው የአሜሪካ ሄሊኮፕተር ኃላፊነቱን አለመውሰዳቸውን ሜህር የተባለው የኢራን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

    የአሜሪካው የዜና ድረ ገጽ አክሲዮስ እንደዘገበው በጥቃቱ ዒላማ የሆኑት የኢራን የአየር መከላከያ እና የራዳር ሥርዓቶች ናቸው። የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ፍንዳታዎች በፋርስ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ በሚገኙ የአገሪቱ ግዛቶች ላይ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ዘግበዋል።

    ከኤቢሲ ኒውስ ጋር በስልክ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦራቸው ለፈጸመው ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አድርገው ከስሰዋታል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጥቃቱን ተከትሎ በኤክስ ገጻቸው ላይ “አሜሪካ በጦር ሜዳው ላይ ሽንፈት ቢገጥማትም ቁርጠኝነታችንን እየተፈታተነች ነው” በማለት አገራቸውለሚፈጸምባት ጥቃት አጸፋ እንደምትሰጥ ዝተዋል።

    ሚኒስትሩ ጨምረውም "ሰላም የምትፈልጉ ከሆነ ቀጣናውን ለቅቃቸው ውጡ” በማለት ለአሜሪካ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተመትቶ የወደቀውን የሠራዊታቸውን አፓቼ ሄሊኮፕተርን በተመለከተ አስተያየት ከመስጠታቸው ቀደም ብሎ የኢራን ዋነኛ ተደራዳሪ እና የአገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐመድ ባጊር ጋሊባፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መልዕክት አስተላልፈው ነበር።

    "እኛ የዲፕሎማሲ ቋንቋን ነው የምንርጠው፣ ነገር ግን ሌሎች ቋንቋዎችንም አቀላጥፈን እንናገራለን። ቃላችሁን የማታከብሩ ከሆነ በደምብ ወደምንችለው የንግግር መድረክ ፊታችንን እናዞራለን” በማለት አሜሪካን በምትፈልገው መልኩ እንደሚያስተናግዷት አስጠንቅቀዋል።

  11. ፈረንሳይ የእስራኤል ፋይናንስ ሚኒስትር ወደ አገሯ እንዳይገቡ አገደች

    ፈረንሳይ ማክሰኞ ዕለት ቀኝ አክራሪው የእስራኤል የፋይናንስ ሚኒስትር ባዛሌል ስሞትሪች ወደ አገሯ እንዳይገቡ አግዳ ጋዛን “ዳግም ቅኝ የመግዛት” አጀንዳን ያራምዳሉ ስትል ኮነነች።

    የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማዕቀቡ የተጣለው ከሌሎች አገራት ጋር በመተባበር መሆኑን ገልጸው በፍልስጤማውያን ሰፋሪዎች ላይ በሚደርስ ጫና የተነሳ እገዳው መጣሉን ገልጸዋል።

    ፈረንሳይ ማዕቀቡን የጣለችው ከብሪታኒያ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ኖርዌይ እና ኒው ዚላንድ ጋር በመተባባር ነው።

    “የሰፈራ እንቅስቃሴዎችን እና በዌስት ባንክ ግጭትን በማቀጣጠል ረገድ ተጠያቂ የሚሆኑ” አካላት ላይ ማዕቀቡ መጣሉን የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ኖኤል ባሮት በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    ሚኒስትሩ፣ ስሞትሪች “ዌስት ባንክን ወደ እስራኤል መጠቅለልን በይፋ ይደግፋሉ፣ በዌስት ባንክ ተጨማሪ ሰፈራዎች እንዲካሄዱ በይፋ ይንቀሳቀሳሉ” ሲሉ ኮንነዋቸዋል።

    አክለውም “ጋዛን ዳግም ቅኝ መግዛት፣ የፍልስጤም ባለሥልጣን ኢኮኖሚያዊ ድቀት እንዲገጥመው፣ እንዲሁም በፍልስጤም ሕዝብ ላይ ጎጂ ተግባራትን “ በመፈጸም ከስሰዋቸዋል።

    ስሞትሪች ወደ ፈረንሳይ እንዳይገቡ ከተከለከሉ የእስራኤል ባለሥልጣናት መካከል ሁለተኛው ናቸው።

    ከአዚህ ቀደም የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትሩ ኢታማር ቤን ግቪር ወደ ፈረንሳይ እንዳይገቡ ታግደዋል።

    ፈረንሳይ አራት የሰፋሪዎች ድርጅት መሪዎችን እና 21 አመጸኛ ሰፋሪዎችን ላይ እገዳ ትላለች።

  12. የኢራን የቀድሞው ጠቅላይ መሪ የቀብር ሥነ ስርዓት በሰኔ ወር አጋማሽ እንደሚካሄድ ተገለጸ

    የኢራን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ስርዓት ሰኔ 18 ወይንም 19 2018 ዓ.ም. ሊካሄድ እንደሚችል የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    መገናኛ ብዙኃኑ የበዓሉ አዘጋጆችን በመጥቀስ ስለ ቀብር ስነ ሥርዓቱ ሂደት ዝርዝሮችን ማውጣት ጀምረዋል።

    ኻሜኒ የተገደሉት የኢራን ጦርነት በተጀመረበት ዕለት የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ነው።

    ኢራን እስካሁን ድረስ የቀብር ሥነ ስርዓታቸውን አልፈጸመችም። ልጃቸው ሞጅታባ ኻሜኒ የእርሳቸውን ሥልጣን እንዲረከቡ በመጋቢት ወር ተመርጠዋል።

    ከዚህ ቀደም የኢራን መገናኛ ብዙኃን የቀብር ሥነ ስርዓታቸው የሚከናወነው በትውልድ ስፍራቸው ማሻድ እንደሚሆን ዘግበው ነበር።

    ከዚያ ውጪ በዋና ከተማዋ ቴህራን፣ በሃይማኖታዊ ከተማዋ ቆም እና በትውልድ ስፍራቸው ለሟች መታሰቢያ በዓላት ይከናወናሉ ተብሏል።

    የኻሜኒ የቀብር ሥነስርዓት ከጸጥታ ስጋት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ሲተላለፍ ቆይቷል። የካቲት 21 እርሳቸው በተገደሉበት ሕንጻ ላእ በተፈጸመው ጥቃት በርካታ ወታደራዊ አዛዦች ተገድለዋል።

  13. በሆርመዝ አቅራቢያ የተከሰከሰውን የአሜሪካ ሄሊኮፕተር አብራሪዎች በድሮን ማውጣት መቻሉ ተገለጸ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ አካባቢ ሰኞ ዕለት የተከሰከሰው የአሜሪካ ጦር ሂሊኮፕተር ሁለት አብራሪዎችን በድሮን ማውጣት መቻሉን የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ዘገበ።

    የአሜሪካ ጦር የባሕር ላይ ድሮኖችን ተጠቅሞ እንዲህ ዓይነት ዘመቻ ሲያካሄድ ይህ የመጀመርያው ነው ተብሏል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ኤች-64 የተሰኘው ሂሊኮፕተር ከተከሰከሰ በኋላ “ወታደሮቹ በሁለት ሰዓት ውስጥ ማውጣት የተቻለ ሲሆን በደህና ሁኔታ ላይ ናቸው” ብሎ ነበር።

    ሂሊኮፕተሩ “የቀጣናውን ውሃ ቅኝት በሚያደርጉበት ወቅት በኦማን ባሕር ዳርቻ አቅራቢያ” መከስከሱን ዕዙ ጨምሮ አስታውቋል።

    ሂሊኮፕተሩ የተከሰከሰው በብልሽት ምክንያት ስለመሆኑ ወይም በኢራን ተመትቶ ለጊዜው ግልጽ አልሆነም።

    የአደጋው መንስዔ ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

    ለሲቢኤስ መረጃ የሰጡ ወታደራዊ ባለሥልጣናት አብራሪዎቹ በሰው አልባ አውሮፕላን አማካኝነት ማውጣት እንደተቻለ ተናግረዋል።

  14. የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉታሬዝ በመካከለኛው ምሥራቅ ዳግም ባገረሸው ግጭት “በጣም እንዳሳሰባቸው” በመግለጽ እስራኤል የዘጋችውን የጋዛ መተላለፊያ እንድትከፍት ጠይቀዋል።

    “ሁሉም ጥቃቶች አሁኑኑ መቆም አለባቸው። በሊባኖስ፣ በኢራን፣ በጋዛ ያለው የተኩስ አቁም ሙሉ በሙሉ መከበር አለበት” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።

    በሚያዚያ ወር የተኩስ አቁም ከተደረሰ በኋላ ቴህራን ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን ካስወነጨፈች በኋላ በኢራን የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎችን ለመጀመርያ ጊዜ ደብድባለች።

    እስራኤል እና ኢራን ሰኞ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት መታኮሳቸውን እንዲያቆሙ ከነገሯቸው በኋላ ተኩስ ማቆማቸውን አስታውቀዋል።

    ዋሺንግተን ሦስት ወር በሞላው የኢራን ጦርነትን ለማስቆም ከስምምነት ለመድረስ የምታደርገውን ጥረት የሁለቱ አገራት ዳግም ወደ ግጭት መግባት አደጋ ላይ ጥሎታል።

    ጉታሬዝ እስራኤል የዘጋችውን የጋዛ መተላለፊያ በመክፈት የሰብዓዊ እርዳታ ፍሰቱ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

    "በተጨማሪም እስራኤል ወደ ጋዛ የሚወስዱትን መተላለፊያዎች ለመዝጋት መወሰኗ በጣም አሳስቦኛል። በመላው ጋዛ የሚደርሰውን ፈጣን እና ደህንነቱ የተጠበቀ የሰብዓዊ ርዳታ መጓጓዙን ለማረጋገጥ ሁሉም መተላለፊያዎች በአስቸኳይ እንዲከፈቱ ጥሪዬን በድጋሚ አቀርባለሁ" ብለዋል።

  15. እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ የምትፈጽመውን ጥቃት መቀጠሏ ተነገረ

    እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የምትፈጽመዋን ጥቃት ዛሬም መቀጠሏን ተከትሎ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    የአገሪቱ ብሔራዊ ዜና አገልግሎት የእስራኤል ጦር በታየር ምሥራቃዊ አካባቢ በርካታ ሕንጻዎች ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋለ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ከፍርስራሽ ውስጥ የሰዎችን አስከሬን ማውጣታቸውን ዘግቧል።

    ሎሪየንት የተባለው ድረ ገጽ በበኩሉ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ከጥቃቱ በኋላ ያሉበት አለመታወቁን ጽፏል።

    ብሔራዊ የዜና አገልግሎቱ እስራኤል በታየር ተራራማ አካባቢ በማለዳ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

    የተኩስ አቁም ስምምነት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ከተደረሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እሁድ ዕለት ቴህራን እና እስራኤል የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል።

    የእስራኤል ጦር በሄዝቦላህ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጽማቸውን ጥቃቶች ዛሬም መቀጠሉን አስታውቋል።

    በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል እንደ አውሮፓውያኑ ከሚያዝያ 16 ጀምሮ የተኩስ አቁም ቢደረስም በሁለቱ አገራት መካከል የሚካሄደው ውጊያ አልቆመም።

    በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን እና ድሮኖችን ማስወንጨፉን ቀጥሏል።

    እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የምትፈጽምመውን ድብደባ በመቀጠል የእግረኛ ጦሯ መጀመሪያ ከነበረበት የሊታኒ ወንዝ ይዞታውን እያሰፋ የተለያዩ አካባቢዎችን መቆጣጠር ቀጥሏል።

    በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ለተኩስ አቁሙ ተፈጻሚነት ለመሥራት ቢስማሙም ይህ የሚሆነው ግን ሄዝቦላህ የሚፈጽማቸውን ጥቃቶች የሚያቆም ከሆነ ብቻ መሆኑ ተገልጿል።

    ሰኞ ዕለት የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር በደቡባዊ ሊባኖስ በተፈጸመ የአየር ድብደባ ቢያንስ 14 ሰዎች መገደላቸውን አስተውቋል።

  16. የአሜሪካ የጦር ሄሊኮፕተር በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ ተከሰከሰ

    የአሜሪካ ሄሊኮፕተር በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ መከስከሱን፤ ሆኖም አብራሪዎቹ መትረፋቸውን ትራምፕ ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ አብራሪዎቹ ደኅና ናቸው፤ በጥሩ ሁኔታም ላይ ይገኛሉ” ብለዋል።

    ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ሄሊኮፕተሩ በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ የተከሰከሰው ሰኞ ሲሆን አብራሪዎቹን መታደግ ተችሏል።

    የአደጋው ምክንያት እስካሁን አልታወቀም።

    ሆኖም ትራምፕ ክስተቱን በተመለከተ ዛሬ ሪፖርት እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

    በተጨማሪም ፕሬዚደንቱ ከኢራን ጋር እየተካሄደ ያለው የሰላም ስምምነት “የመጨረሻው ደረጃ” ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

    ቀደም ብሎ በተባበሩት መንግሥታት የኢራኑ አምባሳደር የሆኑት አሚር ሳኢድ ኢራቫኒ በስምምነት ለማጠናቀቅ ከአሜሪካ ጋር እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች መቀጠላቸውን ተናግረው ነበር።

  17. አሜሪካ ኢራንን በተመለከተ ከእስራኤል የተለየ ፍላጎት እንዳላት ምክትል ፕሬዚደንቷ ተናገሩ

    አሜሪካ እና እስራኤል የጋራ ፍላጎት ቢኖራቸውም ዋሽንግተን ከኢራን ጋር ያላት ግንኙነት ዶናልድ ትራምፕ ለአገራቸው ጥሩ ይሆናል ባሉት ሃሳብ እንደሚመራ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚደንት ጄዲ ቫንስ ሰኞ ዕለት ለፎክስ ኒውስ ተናገሩ።

    “እስራኤል እና አሜሪካ ብዙ የጋራ ፍላጎት አላቸው” ያሉት ምክትል ፕሬዚደንቱ፤ ነገር ግን “ፍላጎቶቻችን የሚለያዩበት ሁኔታዎችም አሉ” ብለዋል።

    ኢራንን በተመለከተ አሜሪካ ያላት ፖሊሲ ዋነኛ ግብ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት ማረጋገጥ እንደሆነም ቫንስ አስታውሰዋል።

    ምክትል ፕሬዚደንቱ “ ባለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ አስፈላጊ የሆነ ሁኔታን ፈጥረናል ብለው ፕሬዚደንቱ ያምናሉ፤ ትክክል ናቸው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ የኢራን ኒውክሌርን ጉዳይ በተመለከተ የረዥም ጊዜ ስምምነት ላይ መድረስ እንችላለን” ብለዋል።

    “አሁን እስራኤል ይህንን ልትወደው ወይም ላትወደው ትችላለች፤ ሆኖም በመሠረታዊነት ይህ የአሜሪካ ፍላጎት እንደሆነ እናስባለን”

    ምክትል ፕሬዚደንቱ ጄዲ ቫንስ ጨምረውም ዋሽንግተን ይህንን ግቧን ለማሳካት ሥራዋን ትቀጥላለች፤ ምክንያቱም የአሜሪካው ፕሬዚደንት የተመረጡት ይህንን ለማሳካት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

  18. አሜሪካ እና ኢራን ለስምምነት “የመጨረሻው ጥረት” ላይ እንደሆኑ ትራምፕ ተናገሩ

    አሜሪካ እና ኢራን የስምምነት “የመጨረሻው ጥረት” ላይ እንደሆኑ እና ስምምነቱ “በማንኛውም መንገድ፣ ቅርጽ ወይም ሁኔታ የኒውክሌር መሣሪያን እንደማይፈቅድ” ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    ሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም ካደረጉ በኋላ በነበሩ የተለያዩ የግጭቱ ምዕራፎች ወቅት ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባቸውን የሚጠቁም አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል።

    በጄኤፍኬ አውሮፕላን ማረፊያ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ፕሬዝዳንቱ ስምምነቱ “በጣም ድንቅ ይሆናል” ብለዋል።

    ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንደማይኖራት በድጋሚ ያስረገጡት ትራምፕ፤ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የሆርሙዝ ወሽመጥ “በአፋጣኝ እንደሚከፈት” ጠቁመዋል።

    “በሁለት ወይም በሦስት ቀናት ውስጥ” የሆርሙዝ ወሽመጥ ሊከፈት እንደሚችልም ተናግረዋል።

    ኢራን እና እስራኤል አንዳቸው ሌላቸው ላይ ጥቃት ማድረስ ለማቆም መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

    ትራምፕ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ካነጋገሩ በኋላ ኢራን ላይ ጥቃት ማድረስ ለማቆም መስማማታቸውን ተናግረዋል።

    “ለተጨማሪ አንድ ሳምንት ገደማ አይተነኳኮሱም” ሲሉም አክለዋል።

  19. ኢራን እና እስራኤል የተኩስ አቁም ካልተጣሰ በስተቀር ጥቃት እንደማይሰናዘሩ አስታወቁ

    ኢራን እና እስራኤል አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚሰነዝሩትን ጥቃት እንደሚያቆሙ አስታውቀዋል።

    ባለፈው ሚያዝያ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ግጭት ውስጥ የገቡት ሁለቱ አገራት ጥቃት መሰንዘር እንደሚያቆሙ ይፋ አድርገዋል።

    ሆኖም ግን የተኩስ አቁም የሚጣስ ከሆነ ጥቃት ማድረስ እንደሚጀምሩ ኢራንም እስራኤልም አስጠንቅቀዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው “ለአሁኑ” ጥቃት ከመሰንዘር እንደምትቆጠብ ጠቅሰው፤ ከኢራን እና ሄዝቦላህ ጋር የሚደረገው ትግል ግን “አላከተመም” ብለዋል።

    የኢራን ጦርም ለእስራኤል “የሚያም የአጸፋ ምላሽ” ከሰጠ በኋላ ጥቃት ማድረስ ማቆሙን አስታውቋል።

    ነገር ግን እስራኤል ጥቃት የምታደርስ ከሆነ “የከፋ እርምጃ” እንደሚወስድ ጦሩ አክሏል።

    እስራኤል በቤሩት ላይ ጥቃት በማድረሷ ኢራን እሑድ ዕለት እስራኤል ላይ የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች። እስራኤልም በምላሹ ትናንት ሰኞ የኢራን ወታደራዊ መቀመጫዎች ላይ ጥቃት አድርሳለች።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር “ከትዕዛዛቸው እንዳልወጡ” ተናግረዋል።

  20. የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢራን ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለጊዜው ማቆማቸውን አስታወቁ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በኢራን ላይ የሚያካሂዱትን ጥቃት “ለአሁን” መግታታቸውን ባደረጉት ንግግር አስታወቁ።

    በቴሌቪዥን በተላለፈው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የእስራኤል ሠራዊት በወሰዳቸው እርምጃዎች ኢራን እና ሄዝቦላህ ከመቼውም ጊዜ በላይ መዳከማቸውን አመልክተዋል።

    ኢራን እሁድ ሌሊት በእስራኤል ላይ የፈጸመችውን የሚሳዔል ጥቃት ተከትሎ በአጸፋው የቴህራንን ወታደራዊ ዒላማዎች መምታቷ ተዘግቧል።

    ይህ የእስራኤል ጥቃት በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጠያቂነት እንደሚቆም ከተነገረ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባረድጉት ንግግር ላይ ጥቃታቸውን ለጊዜው እንዲቆም ማድረጋቸውን ነገር ግን ውጊያው ገና አለማብቃቱን ገልጸዋል።

    ለኢራን ጥቃት ምላሽ በመሰጠቱ "አሁን ተኩሱ ተገትቷል” ሲሉ ኔታኒያሁ ተናግረዋል።

    ነገር ግን “ኢራን በድጋሚ ስህተት በመፈጸም ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ በከፍተኛ ኃይል ምላሽ እንሰጣለን” ሲሉ ያስጠነቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እስራኤል እራሷን ለመከላከል ሙሉ መብት ያላት ሲሆን፣ ይህንንም አስፈላጊ አስከሆነ ድረስ ሙሉ ለሙሉ እንጠቀምበታለን” ብለዋል።

    ኔታኒያሁ በተጨማሪም በኢራን እና በእስራኤል መካከል የጥቃት መመላለስ መከሰቱን ተከትሎ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል።