ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ባሕር ኃይል የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲዘጋ አዘዙ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች እንቅስቃሴን እንዲያግድ ማዘዛቸውን አስታወቁ። በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ለረጅም ሰዓታት ፓኪስታን ውስጥ የተካሄደው ድርድር ውጤት ሳያስገኝ ከቀረ በኋላ ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ረዘም ያለ ጽሁፍ ላይ በአንዳንድ ነጥቦች ላይ ስምምነት መደረሱን አመልክተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሰበር, ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ባሕር ኃይል የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲዘጋ አዘዙ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች እንቅስቃሴን እንዲያግድ ማዘዛቸውን አስታወቁ።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ለረጅም ሰዓታት ፓኪስታን ውስጥ የተካሄደው ድርድር ውጤት ሳያስገኝ ከቀረ በኋላ ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ረዘም ያለ ጽሁፍ ላይ በአንዳንድ ነጥቦች ላይ ስምምነት መደረሱን አመልክተዋል።

    "ውይይቱ በጥሩ ሁኔታ ተከናውኖ በአብዛኞቹ ነጥቦች ላይ ስምምነት ላይ ተደርሷል፤ ነገር ግን እጅግ አስፈላጊ በሆነው በኒውክሌር ጉዳይ ላይ ግን መስማማት አልተደረሰም” ብለዋል።

    ጨምረውም በሆርሙዝ በኩል የሚደረግ ነጻ እንቅስቃሴን በሚመለከት ከስምምነት ሊደረስ እንሚችል አመልክተው፤ ነገር ግን “ኢራኖች ከእነሱ ውጪ ማንም የማያውቃቸው ‘በባሕሩ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ፈንጂዎች ሊኖሩ ይችላሉ’ በማለት ፈቃደኛ አልሆኑም” ሲሉ አስፍረዋል።

    ስለዚህም ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ባሕር ኃይላችን በዓለም አቀፍ የውሃ አካል ላይ ለኢራን የመተላለፊያ ገንዘብ የከፍሉ መርከቦችን እንዲያስቆም” ማዘዛቸውን እና ባሕር ኃይላቸው “በኢራን የተጠመዱ የባሕር ላይ ፈንጂዎችን ማስወገድ ይጀምራል” ብለዋል።

    “ሕገወጥ የመተላለፊያ ክፍያውን የፈጸመ የትኛውም መርከብ እንዲያልፍ አይፈቀድለትም” በማለት “በእኛ ላይ ወይም በሰላማዊ መርከቦች ላይ የሚተኩስ ማንኛውም ኢራናዊ መአት ይወርድበታል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሜሪካ ባሕር ኃይል በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚዘጋም ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስታውቀዋል።

  2. ከአሜሪካ ጋር በተደረገው ንግግር የኢራን ልዑክ የመሩት አፈጉባኤ ማን ናቸው?

    ወግ አጥባቂው እና ወታደራዊ ዳራ ያላቸው ፖለቲከኛ ሞሐመድ ባገር ጋሊባፍ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ወግ አጥባቂው እና ወታደራዊ ዳራ ያላቸው ፖለቲከኛ ሞሐመድ ባገር ጋሊባፍ ነበሩ ወደ ኢዝላማባድ ከአሜሪካ ገር ለመደራደር ያቀናውን ልዑክ የመሩት።

    ባለቤትነቱ የኢራን መንግሥታዊ ብሮድካስተር የሆነው አል ዓላም የአረብኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ጋሊባፍ ከሃይማኖተኛ እና ሠራተኛ ቤተሰብ የተወለዱት በሰሜን ምሥራቅ ቶርጋቤህ ከተማ ውስጥ ነው።

    የትውልድ ከተማቸው የተወሰኑ የእስላማዊ አብዮቱ ስመ ጥር ግለሰቦች ለኖሩበት ማሻድ ከተማ ይቀርባል። 16 ዓመት ሲሆናቸው ማሻድ ውስጥ ወደሚገኙ ዋና ዋና መስኪዶች በመሄድ፤ ኋላ ላይ ጠቅላይ መሪ የሆኑትን አሊ ኻሜኔን ጨምሮ የሌሎችንም አብዮታዊ የሃይማኖት መምህራን ትምህርቶች ተከታትለዋል።

    ጋሊባፍ በአውሮፓውኑ 1979 እስላማዊው አብዮት ከፈነዳ ከአጭር ጊዜ በኋላ በኢራቅ ጦርነት ተዋግተዋል። የኢራን አብዮታዊ ዘብን የተቀላቀሉትም በ20 ዓመታቸው ነው።

    ከሁለት ዓመት በኋላ የአብዮታዊ ጦሩ አንድ የውጊያ ክፍል አዛዥ ሆነዋል። ጦርነቱ በ1988 እስከሚጠናቀቅ ድረስም በዚህ የኃላፊነት ደረጃ ላይ አገልግለዋል።

    ጋሊባፍ ትዳር የመሠረቱት የአብዮታዊ ዘብ አዛዥ በሆኑበት ዓመት ነው። የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን የመሩት የመጀመሪያው ጠቅላይ መሪ ሩሆላ ኻሜኒ እንደሆኑ የአል ዓላም ዘገባ ያመለክታል። በዚህ ትዳራቸው ሦስት ልጆችን አፍርተዋል።

  3. በኢራን የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ከ3500 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ

    በኢራን ከፍተኛ የሟች ቁጥር የተመዘገበው በቴህራን፣ ሆርሞዝጋን እና ኢስፋሃን ከተማዎች መሆኑ ተገልጿል።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በኢራን ከፍተኛ የሟች ቁጥር የተመዘገበው በቴህራን፣ ሆርሞዝጋን እና ኢስፋሃን ከተማዎች መሆኑ ተገልጿል።

    ለ40 ቀናት በዘለቀው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በኢራን ውስጥ 3753 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

    የኢራን ባለሥልጣናት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተደረጉ የአስከሬን ምርመራዎችን በመጥቀስ “2875 ወንዶች እና 496 ሴቶች” በጦርነቱ መገደላቸውን አስታውቀዋል።

    በኢራን ከፍተኛ የሟች ቁጥር የተመዘገበው በቴህራን፣ ሆርሞዝጋን እና ኢስፋሃን ከተማዎች መሆኑ ተገልጿል።

    በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት የተገደሉ ሲሆን ሰባቱ እድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች እንደሚሆናቸው 255ቱ ደግሞ ከአንድ ዓመት እስከ 12 ዓመታቸው መሆኑ ተጠቅሷል።

    121ዱ ደግሞ ከ13 እስከ 18 ዓመት ድረስ እንደሚሆናቸው መንግሥት ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል።

    በአሜሪካ እና በእስራኤል የአየር ድብደባዎች የተገደሉት ኢራናውያን ብቻ ሳይሆኑ በአገሪቱ የሚኖሩ የአፍጋኒስታን፣ ሶሪያ፣ ፓኪስታን፣ ቻይና፣ ኢራቅ እና ሊባኖስ ዜጎች ጭምር ናቸው ብዋል።

    የኢራን ባለሥልጣናት በጦርነት ወቅት ስለሚሞቱ ሰዎች የሚገልጽ መረጃ ይፋ የሚያደርጉት አልፎ አልፎ ነው።

    በእነዚህ ጊዜያትም ቢሆን የሟቾች ቁጥርን ሲገልጹ ሴቶች እና ሕጻናት ላይ ብቻ ያተኩራሉ።

    ከዚህ በፊት በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ውስጥ የኢራን ተወካይ 1500 ሰዎች መሞታቸውን ተናግረው ነበር።

    መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች አክቲቪስቶች ቡድን በበኩሉ 3400 ሰዎች መሞታቸውን ገልጾ ከእነዚህ መካከል 1600 ያህሉ ሰላማዊ ዜጎች ናቸው ብሎ ነበር።

  4. የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር አሜሪካ እና ኢራን ‘ከስምምነት ለመድረስ እንዲሠሩ’ ጥሪ አቀረቡ

    ኪር ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, PA Media

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በፓኪስታን ተካሂዶ ያልተሳካውን ውይይት ተከትሎ ኢራንም ሆነች አሜሪካ “አማራጭ መንገዶችን እንዲፈልጉ’ ጥሪ አቀረቡ።

    ስታርመር ከኦማን ሱልጣን ጋር ባደረጉት ውይይት የተኩስ አቁም ስምምቱ መቀጠሉ "አስፈላጊ" እንደሆነ እና "ሁሉም ወገኖች ተጨማሪ ግጭቶች እንዲያስወገዱ" ጠይቀዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የዩኬ የጤና ሚኒስትር ዌስ ስትሪትይንግ እሑድ ዕለት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ውይይት የኢራንን ጦርነት ለማስቆም የተደረገው የመጀመሪያ ውይይት አለመሳካቱ “አሳዛኝ" መሆኑን ከተናገሩ በኋላ ነው።

    ዩኬ በግጭቱ ላይ ላለመሳተፍ የወሰደችውን አቋም ስትራይቲንግ ተከላክለዋል።

  5. የኢራን ፓርላማ አፈጉባዔ አሜሪካ ‘የኢራናውያን ልዑክን እምነት ማግኘት አልቻለችም” አሉ

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ ከኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ (በስተግራ) ጋር ተገናኙ።

    የፎቶው ባለመብት, Reuters/ Pakistan’s Prime Minister Office

    የምስሉ መግለጫ, የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ ከኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ (በስተግራ) ጋር ተገናኙ።

    የቴህራንን ተደራዳሪ ልዑክ የመሩት የፓርላማው አፈጉባዔ ሞሐመድ ባገር ጋሊባፍ አሁን ጊዜው አሜሪካ “እምነታችንን ማግኘት ትችል እንደሆን ወይም እንዳልሆነ የምትወስንበት ነው” አሉ።

    ጋሊባፍ በኤክስ ገጻቸው ላይ ከድርድሩ በፊት ኢራን “ቀና ልቦና እና ፍላጎት” ነበራት ብለዋል።

    ነገር ግን ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ሁለት ጦርነቶች ጋር በተያያዘ ባለን ልምድ የተነሳ “በተቃራኒው ወገን ላይ እምነት የለንም” ብለዋል።

    የኢራን ልዑካን ቡድን “የፊቱን የሚመለከት ጉዳዮችነ አንስቶ ነበር፤ ነገር ግን ተቃራኒው ወገን በዚህ ድርድር የኢራናውያን ልዑክ እምነት ማግኘት ሳይችል ቀርቷል።”

    በመቀጠልም “በአርባ ቀናት የኢራን ብሔራዊ የመከላከያ ሰራዊት የተገኘውን ውጤት ለማጠናከር የምናደርገውን ጥረት ለአፍታ ሸብረክ አንልም።

    ድርድሩ “ውጥረት የተሞላው” እንደነበር ተናግረው ፓኪስታንን ይህንን ድርድር ስላመቻቸች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

  6. ‘የሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን ቁጥጥር ስር ነው እናም ቀረጥ መከፈል አለበት’ የፓርላማው ምክትል አፈ ጉባዔ

    የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የምትቀዝፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ በፓኪስታን የተደረገው የሰላም ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የሆርሙዝ ወሽመጥን አላነሱም።

    የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ መተላለፊያ የሆነው ይህ የባሕር መስመር በሁሉ አገራት የሰላም ንግግር ወቅት አከራካሪ ከሆኑ አጀንዳዎች መካከል አንዱ ነው።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የሰላም ስምምነት ሲደዕስ ቁልፉ ሃሳብ በወሽመጡ የሚያልፉ መርከቦች ያለምንም ችግር መተላለፍ እንዲችሉ የሚል ነበር።

    ሜኸርስ የዜና ወኪል የኢራን ፓርላማ ምክትል አፈጉባዔ ሃጂ ባቤይ ወሽመጡ ለኢራን ቀይ መስመር መሆኑን መናገራቸውን ዘግቧል።

    ወሽመጡ በኢራን ሙሉ ቁጥጥር ስር ነው ያሉት ምክትል አፈ ጉባዔው “ቀረጥ በሪያል [በኢራን መገበያያ ገንዘብ] መከፈል አለበት” ብለዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ የሆርሙዝ ወሽመጥ “በቅርቡ ይከፈታል” ሲሉ ጽፈው ነበር።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በበኩሉ ቅዳሜ ዕለት ሁለት ፈንጂ አምካኝ መርከቦች አካባቢውን ከፈንጂዎች ለማጽዳት “ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ተሰማርተዋል” ብሏል።

    ነገር ግን ኢራን ሁለቱ መርከቦች ወደ ወሽመጡ መምጣታቸውን አስተባብላለች።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ “በሆርሙዝ ባህር ለማለፍ ወታደራዊ መርከቦች የሚያደርጓቸው ማንኛውም ሙከራ ከባድ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ያደርጋል” ማለቱን ኢሪብ የዜና ወኪል ዘግቧል።

  7. ጦርነት በመቀጠል እና በድርድር ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት ትራምፕ

    ዶናልድ ትራምፕ በማያሚ ከሚገኘው ኤርፎርስ ዋን ሲወርዱ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት የፓኪስታኑን ድርድር መልካም እና መጥፎ ዜና ብለውታል። ከኢራናውያን ጋር ተጨባጭ ውይይቶች ማድረጋቸው መልካም ዜናው ሲሆን ስምምነት ላይ አለመድረሳቸው መጥፎው ዜና ነው።

    ይህ መጥፎ ዜና ለኢራን መሆኑን ተናግረዋል።

    ረዘም ላለ ጊዜ የተደረገው ድርድር ጉልህ እና አስገራሚ ቢሆንም ስምምነት ላይ አለመደረሱ ግን የሚያስደንቅ አይደለም።

    አሜሪካውያን ወደ ፓኪስታን የሄዱት በዚህ ጦርነት ኢራን በጣም ክፉኛ ስለተጎዳች ፈጣን ስምምነት ማድረግ ትችላለች በሚል ሃሳብ ነው።

    “ሃሳባችንን ለመቀበል አልፈልጉም” ሲሉ ቫንስ ተናግረዋል።

    ኢራን የራሷ ቀይ መስመሮች አሏት።

    ጠንካራ እጅ እንዳላት በማመን ነው ወደ ድርድሩ የቀረበችው። በወታደራዊ አቅሟ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስባትም አሁንም በጦርነቱ መቀጠል እንደምትችል ብቻ ሳይሆን ዝግጁም ናት።

    አሁንም ድረስ በሆርሙዝ ስትራቴጂካዊ የባህር ወሽመጥ ላይ ባላት ቁጥጥር ላይ ጉልህ የሆነ ተጽእኖ አላት።

    ቴህራን እና ዋሽንግተን ከአስር አመት በፊት የኒውክሌር ስምምነት ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የደረሱት 18 ወራት ከፈጀ ጉዞ በኋላ ነው።

    ትራምፕ አሁን ከባድ ምርጫ ከፊታቸው ተደቅኗል፤ ጥቃቱን አጠናክሮ መቀጠል ወይም መደራደር።

  8. የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ንግግሩ የተካሄደው አለመተማመን፣ ጥርጣሬ እና ጥያቄ ባንዣበበት ሁኔታ ውስጥ ነው” አሉ

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጌይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጌይ

    በፓኪስታን ኢዝላማባድ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረገውን ያልተሳካ ድርድር ተከትሎ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተያየቱን ሰጥቷል።

    ኢራን ቀደም ሲል አሜሪካ “ከተለጠጠ ፍላጎቷ” መታቀብ እንዳለበት ተናግራ ነበር።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጌይ አሜሪካ እና ኢራን ወዲያውኑ ከስምምነት ይደርሳሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ ተናግረዋል።

    ንግግሩ የተደረገው “አለመተማመን፣ ጥርጣሬ እና ጥያቄ በተሞላበት ከባቢ ውስጥ ነው” ሲሉ አክለዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት 40 ቀን ከሞላው በኋላ ነው ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ የተቻለው።

    ባጌይ ለኢራን የተማሪዎች ዜና ኔትወርክ “ከመጀመርያውም በአንድ ጊዜ ከስምምነት ላይ እንደርሳለን ተብሎ መጠበቅ የለበትም። ማንም ቢሆን እንደዚያ ያለ ግምት ያለው አይስለኝም” ብለዋል።

    አክለውም አሁንም “ዲፕሎማሲ ፈጽሞ አላበቃለትም” ብለዋል።

  9. ድርድሩ አልተሳካም፡ ቀጥሎስ ምን ይሆናል?

    ጄዲ ቫንስ እና የአሜሪካ ልዑካን ከኢራን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ከፓኪስታን ሲወጡ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን እንዳሸነፉ በመግለጽ ወደ ድርድሩ መድረሳቸውን ተከትሎ ስምምነቱ ሁልጊዜ አስቸጋሪ እንደሚሆን የተጠበቀ ጉዳይ ነው።

    በመጨረሻም የማይቻል መስሏል። ሁለቱም ወገኖች ላለመስማማታቸው ሌላኛውን አካል ተጠያቂ አድርገዋል።

    ዋናው ጥያቄ ቀጥሎ ምን ይፈጠራል የሚለው ሆኗል?

    ረቡዕ ዕለት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የተጀመረው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን ስልጣኔ እንደሚያጠፉ የሚገልጽ ዛቻ ከሰነዘሩ በኋላ ነው።

    በኢራን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እንደገና ይቀጥላሉ ወይ የሚለውን በተመለከተም እስካሁን ምንም መረጃ ባይገኝም ጥቃት የመቀጠሉ ዕድሉ ጨምሯል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥን በድርድር እንደገና የመከፈት ጉዳይም ከስምምነት ውጭ ይመስላል። ሁለት የአሜሪካ የጦር መርከቦች የባሕር ውስጥ ፈንጂን ለማጥራት ወደ ባሕረ ሰላጤው መሰማራታቸው አሜሪካ ሌላ መንገድ እንዳየች ያሳያል።

    ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ላለመታጠቅ ቃል መግባት አለመቻሏን ትልቁ እንቅፋት እንደሆነ አሜሪካ ጠቅሳለች። ኢራን ሁልጊዜም የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንደማትፈልግ ብትገልጽም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ጦርነቶች ውስጥ መግባቷ መሣሪያውን እንድትታጠቅ ለሚጠይቁ ሰዎች ተጨማሪ ማበረታቻ ሆኗቸዋል።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረገው የፊት ለፊት ውይይት ታሪካዊ ቢሆንም የዲፕሎማሲ ውድቀት ተደርጎ ሊታወስ ይችላል።

  10. የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነቱን ማክበራቸው “ወሳኝ ነው” አሉ

    የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰላም ድርድር መጠናቀቁን ተከትሎ ባወጡት መግለጫ ሁለቱም ወገኖች “ተኩስ ለማቆም የገቡትን ቁርጠኝነት መቀጠላቸው አስፈላጊ ነው” ሲሉ አሳሰቡ።

    ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት መግለጫ "ሁለቱም ወገኖች ለቀጣናው እና ከዚያም ባሻገር ዘላቂ ሰላም እና ብልጽግናን ለማስፈን በአዎንታዊ መንፈስ እንደሚቀጥሉ ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።

    ፓኪስታን በሁለቱ ወገኖች መካከል "በቀጣይ ቀናት" ውይይትን በማመቻቸት ረገድ የምታደርገውን ሚናዋን እንደምትቀጥል ሚኒስትሩ በልጥፋቸው ላይ አስታውቀዋል።

  11. በፓኪስታን እየተደረገ ስለነበረው እና ያለ ውጤት ስለተበተነው ድርድር አሜሪካ ምን አለች?

    የአሜሪካ ፕክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ በፓኪስታን የኢራንን ጦርነት ያስቆማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ድርድር ለረዥም ሰዓት ከተደረገ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

    ምክትል ፕሬዚዳንቱ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር አጅበዋቸው ነበር።

    ጄዲ ቫንስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት በርካታ ነጥቦችን አንስተዋል።

    • በኢዝላማባድ ለ21 ሰዓታት ከኢራን ጋር ንግግር ቢደረግም ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረስ ሳይቻል ቀርቷል።
    • "ከኢራናውያን ጋር በርካታ ተጨባጭ ውይይቶችን አድርገናል፤ ይህ ጥሩ ዜና ነው። መጥፎው ዜና ስምምነት ላይ አለመድረሳችን ነው፤ እናም ይህ ከዩናይትድ ስቴትስ የበለጠ ለኢራን መጥፎ ዜና ነው ብዬ አስባለሁ" ሲሉ ቫንስ ተናግረዋል።
    • “ኢራናውያን አቋሞቻችንን የሚቀበሉበት ሁኔታ ላይ አልደረሰንም”
    • ምክትል ፕሬዝዳንቱ ለፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ እና ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ያላቸውን አድናቆት ገልጸው በድርድሩ ላይ "ምንም ዓይነት ጉድለቶች ቢኖር ድንቅ ስራ በሰሩት ፓኪስታናውያን ምክንያት አልነበረም" ብለዋል።
    • ቫንስ ስለ ኢራን የኒውክሌር አቅም ተጠይቀው ሲመልሱ አገሪቱ አሁንም ሆነ ወደፊት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳትታጠቅ መግታት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ዋና ግብ" ነው ሲሉ መልሰዋል።
    • ትራምፕ በድርድሩ ላይ መሳተፋቸውን ገልፀው ንግግሩ እየተደረገ ባለበት ወቅት ከፕሬዚዳንቱ ጋር ከ"ግማሽ ጊዜ በላይ" ወይም “በርካታ ጊዜ" ተነጋግረናል ብለዋል።
    • “ከዚህ ስንሄድ ትተን የምንሄደው ቀላል ምክረሃሰብ ነው፤ ይህ የመጨረሻ እና ምርጡ መደራደሪያችን ነው። ኢራናውያን ይቀበሉት ከሆነ የምናየው ነው” ብለዋል።
  12. ኢራን በአሜሪካ አቋሞች ላይ መስማማት አለመቻሏን የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ አስታወቁ

    ጄዲ ቫንስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ከኢራን ጋር በፓኪስታን ያደረጉት ድርድር ያለ ውጤት መበተኑን ለጋዜጠኞች ተናገሩ።

    ምክትል ፕሬዚዳንቱ አሜሪካ “ቀይ መስመሮቿን” ግልጽ ማድረጓን አስታውቀው ኢራን ግን “ባስቀመጥናቸው ነጥቦች ላይ አልተስማማችም” ብለዋል

    አክለውም “ኢራናውያን ነጥቦቻችንን የሚቀበሉበት ሁኔታ ላይ መድረስ አልቻልንም” ብለዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጌይ በበኩላቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ድርድሩ “ውጥረት የተሞላበት" እነደነበር ገልጸው በቀጣይ የሚደረገው ድርድር የሚሳካው “ሌላኛው ወገን ባለው ቁርጠኝነት እና ቀና ልቦና ላይ የተመሰረተ ነው” ብለዋል።

    ቃል አቀባዩ ዋሺንግተን “የተለጠጠ ፍላጎቷን እና ሕጋዊ ያልሆኑ ጥያቄዎቿን” እንድትተው እንዲሁም የኢራንን “ሕጋዊ መብቶች እና ፍላጎቶች” እንድትቀበል ጠይቀዋል።

    ሁለቱ አገራት በድርድራቸው ወቅት ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የሆርሙዝ ወሽመጥ፣ የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም እና “በኢራን ላይ የተከፈተው ጦርነት ሙሉ በሙሉ መቆም” ናቸው።

    ጄዲ ቫንስ ለ21 ሰዓታት ሲነጋገሩ መቆየታቸውን አስታውሰው “መጥፎው ዜና ከስምምነት ላይ መድረስ አልቻልንም” ብለዋል።

    ከምክትል ፕሬዚዳንቱ ጋር የትራምፕ አማች እና አማካሪ ጃሬድ ኩሽነር እንዲሁም የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ተገኝተዋል።

    ቫንስ አሜሪካ ወደ ድርድሩ የመጣችው “በቀና ልቦና” መሆኑን ተናግረው ሁለቱ ወገኖች እንደ አለመታደል ሆኖ ከስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም ብለዋል።

    “ከዚህ ስንሄድ ትተን የምንሄደው ቀላል ምክረሃሰብ ነው፤ ይህ የመጨረሻ እና ምርጡ መደራደሪያችን ነው። ኢራናውያን ይቀበሉት ከሆነ የምናየው ነው” ብለዋል።

  13. ትራምፕ መርከቦች ከአሜሪካ ነዳጅ ለመጫን እየመጡ ነው አሉ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትናንትናው ዕለት ከልጃቸው ኤሪክ ጋር ከዋይት ሀውስ ሲወጡ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትናንትናው ዕለት ከልጃቸው ኤሪክ ጋር ከዋይት ሀውስ ሲወጡ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እና ሙሉ በሙሉ ባዶ የሆኑ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ከአሜሪካ ነዳጅ እና ጋዝ ለመጫን እየመጡ አሉ።

    ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሳፈሩት ጽሑፍ፤ ወደ አሜሪካ እየተጓዙ ያሉት “እጅግ ከፍተኛ ቁጥር” ያላቸው ባዶ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።

    “በዓለም የትኛውም ቦታ ከሚገኘው [ነዳጅ] ምርጥ እና ‘ጣፋጭ’ የሆነውን የነዳጅ ዘይት (እና ጋዝ!)” ይጭናሉ ሲሉም ተናግረዋል።

    አሜሪካ “ቀጣዮቹ ሁለት ትላልቅ የነዳጅ ባለቤት አገራት ተደምረው ካላቸው በላይ የሆነ እና ከፍተኛ ጥራት ያለው ነዳጅ አላት” በማለት ጽፈዋል። “እየጠበቅናችሁ ነው” ሲሉም አክለዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱበት ጊዜ አንስቶ የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። በጦርነቱ ምክንያት ለተቃወሰው የነዳጅ አቅርቦት መፍትሔ የሚመስሉ ዜናዎች ሲሰሙ ደግሞ ዋጋው ሲቀነስ ተስተውሏል።

    የነዳጅ ዋጋን ለማመልከት ጥቅም ላይ የሚውለው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ የአንድ ቤርሜል ዋጋው በሳምንቱ መጀመሪያ ከነበረበት 111 ዶላር በ15 በመቶ በመቀነስ 92 ዶላር ገብቷል።

    የነዳጅ ዋጋ የቀነሰው የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈትን የሚያካትተው የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም በመደረጉ ነው።

    ኢራን ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ የሆነውን ሆርሙዝ መዝጋቷን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ የጨመረ ሲሆን ይህ ጭማሪም የምግብ ዋጋን አንሯል።

    በዚህ ሳምንት የነዳጅ ዋጋ ላይ ቅናሽ ቢታይም አሁንም ከጦርነቱ በፊት ከነበረው አንጻር ከፍተኛ ነው። ከኢራን ጦርነት በፊት አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል 70 ዶላር ገደማ ነበር።

  14. አሜሪካ የያዘቻቸውን የኢራን ሀብቶች ለመልቀቅ ተስማምታለች መባሉን የዋሽንግተን ባለሥልጣናት አስተባበሉ

    የኢራንን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የኢራንን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ

    አሜሪካ ለዓመታት እንዳይንቀሳቀሱ ታግደው የቆዩትን የኢራን ሀብቶች ለመልቀቅ ተስማምታለች መባሉን የዋሽንግተን ባለሥልጣን ማስተባበላቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    አንድ ኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን አሜሪካ የቴህራን ሀብቶችን የመልቀቅ እርምጃ መውሰዷ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ መሆኗን የሚያሳይ ምልክት መሆኑን ለሮይተርስ ተናግረው ነበር።

    እንደ ምንጩ ገለጻ ሀብቱን የመልቀቅ እርምጃው “በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ ጉዞን ደኅንነት ከማረጋገጥ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ” ነው።

    የኢራንን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍም ድርድር ከመጀመሩ በፊት ሀብቶቹ መለቀቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይህንን እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ ጉዳዩን ለደጋፊዎቻቸው ለማብራራ ችግር ይገጥማቸዋል።

    ዘገባው ከወጣ በኋላ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ምላሽ የሰጡ የዋሽንግተን ባለሥልጣናት ግን ጉዳዩን አስተባብለዋል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት እንዲለቀቀ ያልፈቀደው 6 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የኢራን ሀብት እንደያዘች የገለጸችው ኳታርም ማስተባበሏል በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

  15. የሄዝቦላህ ባለሥልጣን ከእስራኤል ጋር ንግግር የሚያደርገውን የሊባኖስ መንግሥት ወቀሱ

    ሊባኖስ ውስጥ የተፈጸመ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የሄዝቦላህ አባል የሆኑት ሕግ አውጪው ሀሰን ፋድላላህ ከእስራኤል ጋር ንግግር ሊያደርግ ተዘጋጀው የሊባኖስ መንግሥት ላይ ወቀሳ አቀረቡ።

    ሕግ አውጪው አስተያየት የሰጡት፤ የሊባኖስ ፕሬዝዳንት በሚቀጥለው ሳምንት ዋሽንግተን ውስጥ ንግግር እንደሚካሄድ ካስታወቁ በኋላ ነው።

    እስራኤል በበኩሏ ከሊባኖስ ጋር በምታደርገው የተኩስ አቁም ንግግር ውስጥ ሄዝቦላህ እንደማይሳተፍ ገልጻለች።

    ሕግ አውጪው ፋድላላህ በሄዝቦላህ በሚተዳደረው አል ማናር ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በወጣው መግለጫቸው፤ የአገሪቱን መንግሥት እርምጃ “ግልጽ የሕገ መንግሥት እና የሊባኖስ ሕግጋት ጥሰት” ሲሉ ጠርተውታል።

    ድርድሩ በሊባኖስ ያለውን “የአገር ውስጥ ክፍፍል ያባብሰዋል” ሲሉም ተችተዋል።

    አክለውም፤ "ጠላት በውጊያ ሜዳ ሊያሳካ ያልቻለውን ነገር... የውሳኔ ሰጪነት አቅም በሌለው፣ መሠረታዊ ግዴታዎቹን በዘነጋ፣ ሕዝቡን መጠበቅ በተሳነው እና የሀገርን ሉዓላዊነት ያስከብራል ተብሎ ሊታመን በማይችል አካል በኩል በሚደረግ ድርድር አያገኘውም” ብለዋል።

  16. የኢራን ባለ 10 ነጥብ እቅድ - ተደራዳሪዎች ማሳካት የሚፈልጉት ምንድነው?

    የኢራንን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ (መሐል) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ (ግራ) ከድርድሩ አስቀድሞ ፓኪስታን ገብተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Iranian Foreign Ministry/EPA

    የምስሉ መግለጫ, የኢራንን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ (መሐል) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ (ግራ) ከድርድሩ አስቀድሞ ፓኪስታን ገብተዋል

    ለዛሬው ድርድር ቀጠሮ ከመያዙ አስቀድሞ ኢራን እና አሜሪካ ለሁለት ሳምንት የሚቆይ ድርድር ላይ መድረሳቸው ይታወሳል። በዚህ ሁለት ሳምንት ውስጥ ተዘግቶ በከረመው የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች ለማለፍ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጾ ነበር።

    ኢራን በበኩሏ የራሷን ባለ 10 ነጥብ የድርድር እቅድ አቅርባለች። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "እቅዱ ለድርድር መነሻነት ሊያገለግል ይችላል" ብለዋል።

    በዚህ የኢራን እቅድ እና አሜሪካ ባቀረበችው ባለ 15 ነጥብ መደራደሪያ ውስጥ ምን ጉዳዮች እንደተካተቱ የሚገልጹ የተለያዩ ዘገባዎች ቢወጡም እስካሁን ድረስ የእቅዶቹ ይዘት በይፋ አልተገለጸም።

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በቴህራን እቅድ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል በቀጣናው የሚደረግ ጦርነት በሙሉ እንዲቆም የሚጠይቀው ነጥብ ይገኝበታል።

    ኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ለማንሳት “ሙሉ ቁርጠኝነት” እንዲሰጥ እንዲሁም በአሜሪካ የተያዙት የኢራን ገንዘብ እና ሀብቶች እንዲለቀቁ ተጠይቋል። በጦርነቱ ኢራን ላይ ለደረሰው ጉዳት “መልሶ ግንባታ ወጪ መሸፈኛ የሚሆን ሙሉ የካሳ ከፍያ” እንዲፈጸም የሚለውም ቴህራን ባቀረበችው እቅድ ውስጥ ተካትቷል።

  17. የኢራን እና አሜሪካ ተደራዳሪዎች ከፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተገናኙ

    የአሜሪካውን ልዑክ የሚመሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ እና የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ

    የፎቶው ባለመብት, Pakistan Prime Minister's Office

    የኢራን እና አሜሪካ ባለሥልጣናት እየተጠበቀ ካለው ድርድር አስቀድሞ ከፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ ጋር ተገናኙ።

    የአሜሪካውን ልዑክ የሚመሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሻሪፍን ማግኘታቸው ተገልጿል።

    የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ቫንስን ከማግኘታቸው አስቀድሞ ከኢራን ተደራዳሪዎች ጋር ለምሳ መገናኘታቸውን የአገሪቱ መንግሥት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት የፓኪስታኑን መሪ ያገኙት ከልዩ መልዕክተኛው ስቲክ ዊትኮፍ እና ከትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር ጋር መሆኑ ተገልጿል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ሻሪፍ፤ ይህ ንግግር በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መወጣጫ ደረጃ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው መናገራቸው ጽሕፈት ቤታቸው ባወጣው መግለጫ ተጠቅሷል።

    የአሜሪካ እና ኢራን ድርድር በምን መልኩ እንደሚካሄድ እንዲሁም ሁለቱ ወገኖች ፊት ለፊት ይገናኙ እንደሆን ማወቅ አስቸጋሪ ነው።

    ከዚህ ቀደም እንደተደረጉ ድርድሮች ሁሉ ፓኪስታን በሰላም እቅዱ ላይ ለውጥ ይኖር እንደሆን ለማየት አንዴ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ቀጥሎ ደግሞ የኢራን ልዑክ ወደሚገኙባቸው ክፍሎች እየገባች ልታደራድር ትችላለች።

    የኢራንን ተደራዳሪ ልዑክ የሚመሩት የፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት አሜሪካ የኢራንን ሀብት ለመልቀቅ መስማማት አለባት ብለዋል።

    የቴህራን ሀብት ስለመለቀቁ የሚጠቁሙ የኢራን ሪፖርቶች አሉ። ሆኖም ትክክለኛነቱ ከአሜሪካ በኩል እስካሁን አልተረጋገጠም። እናም ደግሞ ጉዳዩ በአሜሪካ ለሚገኘው የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ እሾሃማ እንደሚሆን ይጠበቃል።

    ኢራን ለአሜሪካ ባቀረበችው ባለ 10 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ላይ የተያዙ የቴህራን ገንዘቦች እና ሀብቶች እንዲለቀቁ የሚጠይቀው ነጥብ ይገኝበታል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢስላማባድ የሚገኙ የኢራን ጋዜጠኞች የቴህራን ቅድመ ሁኔታዎች የማይሟሉ ከሆነ ድርድሩ እንደሚሰረዝ እየተናገሩ ነው።

    የኢራን ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ወኪል የሆነች ጋዜጠኛ የኢራንን ጥቅም፣ ጥያቄ እና ቀይ መስመሮች ከማያስከብር ድርድር መውጣት በራሱ “ስኬት ነው” ብላለች።

  18. በአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ላይ የሚነሱ አራት ቁልፍ ጥያቄዎች

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እስላማባድ ሲገቡ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በፓኪስታን የሚደረገው የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር እየተጠበቀ ነው። ነገር ግን ስለ ድርድሩ ዝርዝር ጉዳዮች በቂ መረጃ አልወጣም።

    የአሜሪካ እና ኢራን ተደራዳሪ ልዑካን በኢስላማባድ የፓኪስታን ባለሥልጣናትን ለማግኘት በተቃረቡበት በአሁኑ ሰዓት አራት ቁልፍ ጥያቄዎችን እንመልከት።

    በንግግሩ ማን ይሳተፋል?

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አማች ከሆኑት ልዩ አማካሪ ጃሬድ ኩሽነር እና ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር በመሆን ከኢራን ጋር የሰላም ንግግር ለማድረግ በፓኪስታን መዲና ኢስላማባድ ገብተዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ ቁልፍ የኢራን መንግሥት ባለሥልጣን ሆነው ብቅ ያሉት የፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባጋር ጋሊባፍ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ከንግግሩ ቀደም ብለው ማምሻውን ኢስላማባድ ደርሰዋል።

    የፓኪስታን ሚና ምንድን ነው?

    ሁለቱም ወገኖች በፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር እና በአገሪቱ የወታደራዊ አዛዥ አሲም ሙኒር አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

    ፓኪስታን በሁለቱ ተፋላሚ አገራት መካከል ቁልፍ አደራዳሪ ሆናለች። ከወዲሁ ጥርጣሬ ውስጥ የወደቀው የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስም ሚና ተጫውታለች።

    ንግግሩ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል?

    በአጭሩ ለመመለስ ንግግሩ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ግልፅ አይደለም። ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ቁርኝነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ንግግሩ አንድ ቀን ምን አልባትም እስከ ቅዳሜ ምሽት እንደሚካሄድ ዘግቧል።

    የሚጠበቁ ቁልፍ የንግግሩ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

    የድርድሩ ዋነኛ ነጥቦች፤ ኢራን በመዳፏ የጠረነፈችው የሆርሙዝ ወሽመጥ፣ በሊባኖስ የቀጠለው ግጭት እና ኢራን ያከማቸችው የበለፀገ ዩራኒየምን ያካትታል።

  19. የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ለኢራን ድርድር ፓኪስታን ገቡ

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በፓኪስታን ባለሥልጣናት አቀባበል ሲደረግላቸው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት እና ዋና ተደራዳሪ ጄዲ ቫንስ ከኢራን ጋር ለሚደረገው ድርድር ከልዑክ ቡድናቸው ጋር ፓኪስታን ገቡ።

    ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር ጋር ኢስላማባድ ከተማ የገቡት ቫንስ ከሰዓታት በኋላ በሚጀምረው የንግግር ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

    ለአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት አቀባበል ያደረጉት የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሐማድ ኢሻቅ ዳር ዋሽንግተን ለዘላቂ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ሰላም ያላትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

    ሚኒስትሩ፤ አሜሪካ እና ኢራን “ገንቢ በሆነ መልኩ ተሳትፎ ያደርጋሉ” የሚል ተስፋቸውን መግለጻቸውን የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። ፓኪስታን ሁለቱም ወገኖች ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ያላትን ፍላጎት በድጋሚ አረጋግጠዋል።

    ጄዲ ቫን ወደ ፓኪስታን ከመጓዛቸው በፊት ባደረጉት ንግግር “ድርድሩ እንዲካሄድ እየጠበቁ” እንደሆነ ገልጸው፤ ነገር ግን ኢራን “ለመጫወት እንዳትሞክር” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    የኢራኑን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ በበኩላቸው “ቀና ፍላጎት አለን፤ ነገር ግን እምነታችንን አንጥልም” ሲሉ ፓኪስታን ከደረሱ በኋላ መናገራቸውን የአገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

    “ከአሜሪካውያን ጋር በነበረን የድርድር ልምድ ሁልጊዜም ሲያጋጥመን የነበረው ክሽፈት እና የቃል ኪዳኖች መሰበር ነው” ብለዋል።

  20. አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ የደረሰባቸው ከፍተኛ እና አካል የሚያጎድል ጉዳት እንደሆነ ሮይተርስ ዘገበ

    የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ጠቅላይ መሪነት ሥልጣንን ከተረከቡ ወዲህ በአካል ያልታዩት ሞጅታባ ኻሜኒ፤ አባታቸውን በገደለው የአየር ጥቃት ከደረሰባቸው የፊት እና የእግር ጉዳት እያገገሙ እንደሆነ በቅርባቸው ካሉ ምንጮች መስማቱን ሮይተርስ ዘገበ።

    የዜና ወኪሉ ዘገባ እንደሚያመለክተው አዲሱ ጠቅላይ መሪ በጥቃቱ ፊታቸው እንደተበላሸ እና አንድ ወይም ሁለት እግሮቻቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ ሦስት ምንጮች ተናግረዋል።

    ይህም ቢሆን ግን የ56 ዓመቱ ሞጅታባ ከጉዳታቸው እያገገሙ እንደሆነ እና አዕምሯቸው ስል ሆኖ መቀጠሉን ምንጮቹ ገልጸዋል ተብሏል።

    በድምጽ በሚደረጉ የኦንላይን ስብስብሰባዎች ላይ እየተሳተፉ እንዲሁም ከአሜሪካ ጋር እንደሚሄደው ድርድር ባሉ ዋነኛ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እየሰጡ መሆኑ ተገልጿል።

    በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት አባታቸውን ተክተው ወደ ሥልጣን የመጡት ሞጅታባ ኻሜኒ፤ በዚሁ ዕለት የደረሰባቸው ጉዳት መጠን እስካሁን በይፋ አልተገለጸም።

    ከዚህ ቀደም የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ በጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ጥቅም ላይ የሚውልን ቃል በመጠቀም ያሉበት ሁኔታ ጠቁሞ ነበር።

    የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በበኩላቸው ኻሜኒ “መቁሰላቸውን እና አካል መጉደል ደርሶባቸው ሊሆን እንደሚችል” ባለፈው ወር ተናግረው ነበር።

    የአሜሪካ የስለላ መረጃ ግን ኻሜኒ እግራቸውን አጥተዋል ተብሎ እንደሚታመን ማሳየቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ መናገራቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።