ኢትዮጵያ የሩሲያ ፊልሞችን እንዳታሳይ ዩክሬን ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩክሬን፤ ስድስት የሩሲያ ፊልሞች በአዲስ አበባ እንዳይታዩ የኢትዮጵያ መንግሥትን እና የ21ኛው ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል አዘጋጆችን ጠየቀች።
ዩክሬን ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ለፌስቲቫሉ አዘጋጆች ይፋዊ ደብዳቤ መጻፏን በአዲስ አበባ የሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ ለቢቢሲ አረጋግጧል።
ዩክሬን በዋነኛነት ቅሬታ ያቀረበችበት ፊልም ‘ሂስ ኔም ወዝ ኖት ሊስትድ’ የተባለው በአውሮፓውያኑ 2025 የወጣው የሩሲያ ፊልም ነው።
የጦርነት ድራማ ዘውግ የሆነው ፊልሙ የተዘጋጀው በቭላድሚር ማሽኮቭ ሲሆን፤ አዘጋጁ የዩክሬንን ጦርነት በመደገፍ በአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብ ተጥሎበታል።
ስድስቱ ፊልሞች የሚታዩት በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ለሩሲያ ፊልሞች በተመደቡት ቀናት ነው። ፌስቲቫሉ ከአውሮፓውያኑ ኅዳር 15 እስከ 22 ድረስ ይከናወናል።
ቭላድሚር ማሽኮቭ የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ደጋፊ የሆነ ዝነኛ ተዋናይ እና አዘጋጅ ነው።
በአውሮፓ ኅብረት የማዕቀብ ዝርዝር ውስጥ የተካተተው በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2022 ነበር።
የአውሮፓ ኅብረት ማዕቀቡን የጣለበት ሩሲያ ክሬሚያን ስትጠቀልል በይፋ ድጋፍ በመስጠቱ እና በየካቲት 2020 በሞስኮ ጦርነት በሚደግፍ ሰልፍ በመሳተፉ መሆኑን አስታውቋል።
የዩክሬን ኤምባሲ ለቢቢሲ በላከው መግለጫ እንዳለመከተው ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከፌስቲቫሉ አዘጋጆች ለደብዳቤው ምላሽ አላገኘም።
“በየትኛውም አገር ላይ የሚከፈት ጦርነትን ምክንያታዊ ለማድረግ ባህል ጥቅም ላይ ሊውል አይችልም፤ በዚህ ዐውድ ዩክሬንን ማለት ነው” ሲል ኤምባሲው አቋሙን ገልጿል።
ቢቢሲ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከፌስቲቫሉ አዘጋጆች አስተያየት ቢጠይቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።
ሆኖም ግን የፌስቲቫሉ አዘጋጆች መሰናዶውን ለማስተዋወቅ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ባወጡት መረጃ ‘ሂስ ኔም ወዝ ኖት ሊስትድ’ ወይም His Name Was Not Listed የተሰኘው ፊልም ለዕይታ እንደሚቀርብ ተመልክቷል።



















