ቀጥታ, ዶናልድ ትራምፕ፣ ንጉሥ ቻርልስ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራት አይገባም ብለው እንደሚያምኑ ተናገሩ

ዶናልድ ትራምፕ፣ ንጉሥ ቻርልስ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራት አይገባም ብለው እንደሚያምኑ ተናገሩ። ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሐውስ በተዘጋጀ የእራት ግብዣ ላይ ንጉሥ ቻርልስ ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ሊኖራት አይገባም ብለው እንደሚያምኑ ሲናገሩ “ቻርልስ ከእኔ ጋር ይስማማል፤ ከእኔ በበለጠ ይስማማል” ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የዚምቧብዌ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ልጅ ከደቡብ አፍሪካ ሊባረር ነው

    ቤላርማይን ሙጋቤ

    የፎቶው ባለመብት, Gallo Images via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ቤላርማይን ሙጋቤ

    የዚምባብዌ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ የመጨረሻ ልጅ በአስቸኳይ ከደቡብ አፍሪካ እንዲባረር የጆሃንስበርግ ፍርድ ቤት ወሰነ።

    ቤላርማይን ሙጋቤ በዚህ ወር መጀመርያ ላይ በመኖሪያ ቤቱ የ23 ዓመት ወጣት ላይ በመተኮሱ የተከሰሰ ሲሆን ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።

    የ28 ዓመቱ የሙጋቤ ልጅ መሳሪያ በመደቀን እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያለ ሕጋዊ ፈቃድ በመኖር ጥፋተኛ መሆኑ ተገልጿል።

    ፍርድ ቤት በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ 36,000 ዶላር እንዲከፍል ወስኖበታል።

    አብሮት የተከሰሰው የአጎቱ ልጅ ቶቢያስ ማቶንሆድዜ በግድያ ሙከራ፣ በሕገወጥ ስደት፣ የጦር መሣሪያ በመያዝ እና በፍትህ ስርዓቱ ላይ ጣልቃ በመግባት ወንጀሎች የሦስት ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

    ሁለቱም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአስር ቀን በፊት ፖሊስ በጆሃንስበርግ በሚገኘው የሙጋቤ ልጅ ቤት ተጠርቶ ከመጣ በኋላ ነው።

    በቅጥር ግቢው ውስጥ ይሰራ የነበረው ግለሰብ በጥይት ተመትቶ ክፉኛ በመጎዳቱ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

    አቃቤ ሕጎች ለፍርድ ቤቱ ግለሰቡ ላይ የተተኮሰው በቅጥር ግቢው ውስጥ ሦስት ሰዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን አስረድተዋል።

    አክለውም ግለሰቡ ለማምለጥ ሲሞክር ከኋላው ሁለት ጊዜ ተተኩሱበት መመታቱን ገልጸዋል።

    ፖሊስ የመኖሪያ ቤቱ ላይ ብርበራ ያካሄደ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የጦር መሣሪያውን አላገኘም።

  2. በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለው እገዳ እንደሚራዘም ከተሰማ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    ነዳጅ የሚቀዳ ሰው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን እገዳ ለማራዘም ማቀዷ ከተሰማ በኋላ የዓለም ነዳጅ ዘይት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ።

    ማክሰኞ ዕለት 110 ዶላር የተሸጠው አንድ በርሜል ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ረቡዕ 115 ዶላር ገብቷል።

    የነዳጅ ዋጋ የጨመረው ዎል ስትሪት ጆርናል ዶናልድ ትራምፕ የኢራን ምጣኔ ሃብትን ለማዳከም በቴህራን ወደቦች ላይ የተጣለውን እገዳ እንደሚያራዝሙ ለረዳቶቻቸው መናገራቸውን ከዘገበ በኋላ ነው።

    ኢራን የአሜሪካ እገዳ እስካልተነሳ ድረስ በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦች እንደማያልፉ ተናግራለች።

    የካቲት 21 2018 ዓ.ም. እስራኤል እና አሜሪካ ኢራንን መደብደብ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

    ኢራን ለተከፈተባትን ጦርነት ምላሽ ለመስጠት በሚል የዓለም አንድ አምስተኛ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ምርት የሚመላለስበት የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታለች።

  3. ፈረንሳይ ዜጎቿ በፍጥነት ማሊን ለቅቀው እንዲወጡ አሳሰበች

    ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ታጣቂዎች ዋና ከተማዋ ባማኮን ጨምሮ በመላ አገሪቱ ጥቃት ከፍተዋል

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ታጣቂዎች ዋና ከተማዋ ባማኮን ጨምሮ በመላ አገሪቱ ጥቃት ከፍተዋል

    የማሊ ታጣቂዎች በሳምንቱ መጨረሻ የተቀናጀ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ ፈረንሳይ ዜጎቿ “በተቻለ ፍጥነት” አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አሳሰበች።

    ቅዳሜ ዕለት በማሊ ተገንጣይ ቡድኖች እና እስላማዊ ታጣቂዎች በጋራ በመሆን በከፈቱት ጥቃት ዋና ከተማዋ ባማኮን ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ ክፍል ውጊያ ተካሄዷል።

    ፈረንሳይ ረቡዕ በማሊ ያለው ሁኔታ “ፈጽሞ ያልተረጋጋ” መሆኑን በመግለጽ ዜጎቿ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር እንዳይሄዱ መክራለች።

    የማሊ የመከላከያ ሚኒስትር በዋና ከተማዋ ባማኮ አቅራቢያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸው ተገልጿል።

    ሳዲዮ ካማራ የተገደሉት እስላማዊ ታጣቂዎች እና ተገንጣዮች በመላ አገሪቱ በከፈቱት የተቀናጁ የጥቃት ማዕበሎች መሆኑን የበርካታ የዜና አውታሮች ዘገባ አመልክቷል።

    የማሊ ጦር ጄነራል አሲሚ ጎይታ የአገሪቱ ጸጥታ መረጋጋቱን በትናንትናው ዕለት አስታውቀዋል።

    ማክሰⶉ ምሽት የአገሪቱ ጦር በታጣቂዎች ላይ “ከፍተኛ ኪሳራ” ማድረሱን ገልጾ አሁንም ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁሟል።

  4. እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በፈጸመችው ተከታታይ ጥቃት ሦስት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተገደሉ

    የእስራኤል ጦር ማክሰኞ ዕለት በደቡብ ሊባኖስ የሄዝቦላህ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አስታውቋል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጦር ማክሰኞ ዕለት በደቡብ ሊባኖስ የሄዝቦላህ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አስታውቋል

    እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በፈጸመችው ሁለት ተከታታይ ጥቃት ሦስት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥቃቱን “የጦር ወንጀል” ሲሉ ኮንነውታል።

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር በመጀመርያው የእስራኤል ጥቃት የተጎዱ ሰዎችን ለማትረፍ የተላኩ ሦስት የአገሪቱ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በሁለተኛው ጥቃት መገደላቸውን አስታውቋል።

    በኋላ ላይ የሞታቸው መንስዔ ሲጣራ በፍርስራሸሶች ውስጥ ተቀብረው ሕይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።

    ሚኒስቴሩ ሁለቱ የተገደሉት ሰዎች ማን እንደሆኑ ይፋ አላደረገም። በጥቃቱ ሁለት የሊባኖስ ጦር ወታደሮች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ታውቋል።

    የእስራኤል ጦር ስለጥቃቱ ጥያቄ ቢቀርብለትም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።

    የሰብዓዊ መብቶች ብድኖች በሕክምና ባለሙያዎች ላይ ሆን ተብሎ የሚፈጸም ጥቃት ከጦር ወንጀል ጋር ይስተካከላል ብለዋል።

    በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል ዳግም ግጭት የተቀሰቀሰው የኢራን ጦርነትን ተከትሎ ወደ ቴል አቪቭ ሮኬቶችን ማስወንጨፍ በመጀመሩ ነው።

    እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደርሱም፣ በደቡባዊ ሊባኖስ የእግረኛ ጦሯን አሰማርታ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደች ትገኛለች።

    በእስራኤል ጦር በተፈጸሙ ጥቃቶች እስካሁን ድረስ 103 የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ 2500 ሰዎች ተገድለዋል።

    ከሟቾቹ መካከል 270 ሴቶች እና ከ 170 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሕጻናት መሆናቸው ተገልጿል።

  5. ትራምፕ ኢራን አቋሟን አስተካክላ የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለመተው መስማማት አልቻለችም ሲሉ ተቹ

    በዶናልድ ትራምፕ የተጋራ ምስል

    የፎቶው ባለመብት, TRUTH SOCIAL

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ ረቡዕ ዕለት የኢራን አመራሮች “በተቻለ ፍጥነት ብልህ ቢሆኑ” እና የኒውክሌር ፕሮግራማቸውን ለመተው ቢስማሙ እንደሚሻል ተናገሩ።

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የተጀመረው ጦርነት ሁለት ወር አልፎታል።

    “ኢራን አቋማቸውን ማስተካከል አትችልም። የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለመተው እንዴት መስማማት እንዳለባት አታውቅም” ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    ትራምፕ በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ከምስላቸው ጋር ባጋሩት በዚህ ልጥፍ ከጀርባቸው ቤቶች እየፈነዱ እርሳቸው ኤኬ-47 ጠብመንጃ ይዘው ይታያሉ።

    በምስሉ ላይ “ከእንግዲህ በኋላ ትዕግሥት የለም” የሚል ጽሑፍ ተካትቷል።

    ዋይት ሐውስ ከኢራን ጋር በኒውክሌር ፕሮግራሞቿ ላይ ለመነጋገር ቢሞክርም ቴህራን ግን ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች።

    ቴህራን በቅድሚያ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት የጠየቀች ሲሆን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ የሚደረገው ንግግር ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መጠየቋ ተዘግቧል።

    ትራምፕ ወደ ኢራን የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች እንቅስቃሴ ላይ እገዳ መጣላቸው ይታወሳል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል የአሜሪካው ፕሬዚዳንት እገዳው እንዲራዘም መወሰናቸውን ዘግቧል።

  6. የቀድሞ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ፔንታጎን በኢራን ትምህርት ቤት ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት ዝም ማለቱን ተቹ

    ወላጆች በቀብር ስነስርዓት ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አምስት የቀድሞ የአሜሪካ ባለሥልጣናት በኢራን ጦርነት መጀመሪያ ላይ በትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት የአሜሪካ ጦር ስለነበረው ተሳትፎ ባለመግለጹ ፔንታጎንን ተቹ።

    ከእነዚህ ባለሥልጣናት መካከል አንዳንዶቹ ጥቃቱ ከተፈጸመ ረጅም ጊዜ በኋላ እንኳን መሠረታዊ ዝርዝሮች ይፋ አለመሆናቸው በጣም ያልተለመደ መሆኑን ተናግረዋል።

    የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በሚናብ በሚገኝ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ የሚሳዔል ጥቃት 110 ሕጻናትን ጨምሮ 168 ሰዎች መገደላቸውን የኢራን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

    ከዚያን ጊዜ ወዲህ ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ ፔንታጎን ክስተቱ በምርመራ ላይ መሆኑን ብቻ አስታውቋል።

    የአሜሪካ ሚዲያዎች በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ ጦር መርማሪዎች የአሜሪካ መከላከያ ትምህርት ቤቱን ባለማወቅ በመምታታቸው ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢያምኑም የመጨረሻ መደምደሚያ ላይ አለመድረሳቸውን ዘግበዋል።

    ቢቢሲ ስለ ጥቃቱ እና ግልፅነት ባለመኖር ላይ ስለሚቀርበው ክስ ለፔንታጎን ባለሥልጣን ጥያቄ አቅርቦ "ይህ ክስተት በአሁኑ ጊዜ በምርመራ ላይ ነው" የሚል ምላሽ አግኝቷል።

    ባለሥልጣኑ አክለውም ተጨማሪ ዝርዝሮች እንደተገኙ ይፋ እንደሚደረጉ ተናግረዋል።

    ቢቢሲ በአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻዎች ወቅት ሰላማዊ ዜጎች የተገደሉባቸውን ሦስት ጉዳዮችን ፈትሿል።

    በእያንዳንዱ ጥቃት ላይ ፔንታጎን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ዝርዝር መረጃዎችን ሰጥቷል።

  7. የኢራንን ሥልጣን በበላይነት የተቆጣጠረው አብዮታዊ ዘብ

    ቴህራን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ለሁለት ወራት በዘለቀው የኢራን ጦርነት ቴህራን አንድ የማያሻማ መመሪያ የሚሰጥ ሃይማኖታዊ መሪ የላትም።

    ይህ በድንገት ፍጻሜውን ያገኘው የኢራን አገዛዝ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ በአክራሪ የአብዮታዊ ዘብ አዛዦች እጅ እንዲወድቅ አድርጓል።

    የእስላማዊ ሪፐብሊክ እአአ በ1979 ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በቁልፍ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጡት ጠቅላይ መሪው ነበሩ። ነገር ግን የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደል እና እርሳቸውን ተክቶ የልጃቸው ወደ ሥልጣን መምጣት የአብዮታዊ ዘቡ ጄነራሎች ውሳኔ ሰጪነት እንዲገን አድርጓል።

    በዚህ የተነሳ ደግሞ ወሳኝ የሆነው ውሳኔ ሰጭ አካል በመጉደሉ ሞጅታባ ኻሜኒ በአብዮታዊ ዘቡ አዛዦች ላይየበለጠ እንዲደገፉ አድርጓቸዋል።

    ሞጅታባ ኻሜኒ የሥርዓቱ ቁንጮ ላይ ናቸው። ነገር ግን ሦስት ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የውስት አዋቂዎች ለሮይተርስ እንደተናገሩት ጠቅላይ መሪው ውሳኔያቸውን የሚሰጡት በአዛዦቹ ላይ በመመስረት ነው።

    የኢራን አመራር በጦርነቱ የተነሳ ውሳኔዎቹን በጥቂት ጠቅላይ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ባሉ አክራሪ ቡድኖች ላይ እንዲመሰረት አድርጎታል።

    ይህ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ጫና ፈጥሯል። አንድ ከፍተኛ የፓኪስታን ባለሥልጣን “ኢራናውያን ምላሽ ሲሰጡ እጅግ በጣም ዝግ ብለው ነው” ብለዋል።

    “አንድ ወጥ የሆነ ውሳኔ ሰጭ መዋቅር የለም። አንዳንድ ጊዜ ምላሽ ለማግኘት ሁለት እና ሦስት ቀን ይወስዳል” ሲሉ አክለዋል።

    ተንታኞች እንዳሉት የስምምነቱ እንቅፋት በቴህራን ውስጥ ያለ የሥልጣን ሽኩቻ አይደለም። ነገር ግን ዋሽንግተን ለማቅረብ በተዘጋጀችው እና የኢራን አክራሪ ወገኖች ለመቀበል ፈቃደኛ በሆኑት መካከል ያለው ክፍተት ነው።

    ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው የሰላም ድርድር የኢራን የዲፕሎማሲ ፊት የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራጋቺ እና በቅርቡ የተቀላቀሏቸው የፓርላማው አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ ናቸው።

    ፖለቲካውን ከጀርባ ሆነው የሚዘውሩት ግን የአብዮታዊ ዘቡ አዛዥ አዛዥ አህመድ ቫሂዲ መሆናቸውን አንድ የፓኪስታን እና ሁለት የኢራን ምንጮች ለሮይተርስ አረጋግጠዋል።

    ቫሂዲ ቁልፍ ውሳኔ ሰጪ መሆናቸው በተኩስ አቁሙ ስምምነት ወቅትም ሆኑ ከዚያ በኋላ ከኢዝላማባድ ጋር ባለ ንግግር ወቅት ታይተዋል።

    ሮይተርስ በኢራን ስለተፈጠረው የአመራር ክፍተት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩን ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም። ከዚህ በፊት ግን በኢራን ውስጥ ባሉ አመራሮች መካከል መከፋፈል እንደሌለ እና የሥልጣን ሽኩቻ እንዳልተከሰተ በመግለጽ አስተየየት ሰጥቶ ነበር።

  8. ዶናልድ ትራምፕ ንጉሥ ቻርልስ ኢራን ኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራት እንደማይገባ እንደሚያምኑ ተናገሩ

    ለአራት ቀናት የሥራ ጉብኝት አሜሪካ የሚገኙት ንጉሥ ቻርልሰ ከባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ እንዲሁም ከፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ባለቤታቸው ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ዶናልድ ትራምፕ ንጉሠ ቻርልስ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራት አይገባም ብለው እንደሚያምኑ ተናገሩ።

    ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሐውስ ለንጉሡ በተዘጋጀ የእራት ግብዣ ላይ “ቻርለስ ከእኔ ጋር ይስማማል፤ ከእኔ በበለጠ ይስማማል” ሲሉ ተናግረዋል።

    ትራምፕ በዚህ ንግግራቸው ላይ ቴህራንን "በወታደራዊ ኃይል አሸንፈናታል” ብለዋል።

    "ያ ተቃዋሚ [ቴህራን] በጭራሽ [እንዲኖረው] አንፈቅድም፤ ቻርልስ ከእኔ ጋር ይስማማል። ከእኔም በላይ፤ ያ ​​ተቃዋሚ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዲኖረው በጭራሽ አንፈቅድም ።"

    የበርኪንግሃም ቤተ መንግሥት ቃል አቀባይ የትራምፕን ንግግር ተከትሎ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ "ንጉሡ መንግሥታቸው የኒውክሌር መስፋፋትን ለመከላከል ያለውን የረዥም ጊዜ እና የታወቀ አቋም ያደግፋሉ" ብለዋል።

    ለአራት ቀናት የሥራ ጉብኝት አሜሪካ የሚገኙት ንጉሥ ቻርልሰ የአሜሪካን የነጻነት በዓል ከማክበር ባሻገር ከዩኬ ጋር የተፈጠረውን የግንኙነት መሻከር ይጠግናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ንጉሥ ቻርለስ ከባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ ጋር በመሆን ሰኞ ዕለት ዋሺንግተን ሲደርሱ ደማቅ አቀባባል ተደርጎላቸዋል።

  9. በዓለም ላይ እጅግ ውድ የሆነውን ሃብት የሚቆጣጠረው ኦፔክ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ሲለያዩ ምን ይፈጠራል?

    ነጭ ልብስ የለበሰ ሰው በነዳጅ በርሜሎች አጠገብ ሲያልፍ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ምክንያት እየጨመረ የሚገኘው የነዳጅ ገበያ አዲስ ድንገተኛ ክስተት አስተናግዷል።

    የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ከፔትሮሊየም ላኪ አገራት ድርጅት (ኦፔክ) እንደምትወጣ አሳውቃለች።

    ኦፔክ እአአ በ1960 ነበር ባግዳድ ኢራቅ ውስጥ የተቋቋመው።

    በአምስት አገራት የተቋቋመው ኦፔክ የአባል አገራቱን ቁጥር 12 ማድረስ ችሎ ነበር።

    አሁን ግን የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ይህንን ቁጥርበአንድአጉድላዋለች።

    ተቋሙ ለዓመታት አባል አገራቱ የሚያመርቱትን ነዳጅ በመቆጣጠር የዓለም የነዳጅ ዋጋን ሲወስን ቆይቷል።

    የነዳጅ ዋጋ መጨመር ሲፈልግ ምርት ይቀንሳል፤ ዋጋው ለማረጋጋት ደግሞ አገራቱ ምርቱን እንዲጨምሩ ያደርጋል።

    የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በተቋሙ ውስጥ አባል ብቻ ሳትሆን ቁልፍ ከሚባሉት ተርታ አንዷ ነበረች።

    የኦፔክ ምርት በሳዑዲ አረቢያ ቁጥጥር ስር ቢሆንም፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሁለተኛው ከፍተኛ የመጠባበቂያ ምርት አቅም ነበራት።

    ይህም አገሪቱን አቅም ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።

    ሆኖም ግን ኦፔክ እያንዳንዱ አገር ምን ያህል ነዳጅ ማምረት እንደሚችል የሚያስቀምጠው ገደብ አለ።

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በቀን ከ3 እስከ 3.5 ሚሊዮን በርሜል ማምረት ተፈቅዶላታል።

    በቀን እስከ 5 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የማምረት አቅም ላላት አገር አነስተኛ ቁጥር ነው።

    በቀላል አነጋገር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ገንዘብ የማግኘት እድሏን በእጅጉ ቀንሶታል።

  10. በቴህራን እና ዋሺንግተን መካከል የሚካሄደው ንግግር መቋጫ ባለማግኘቱ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት ዳግም ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ስጋር የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ አሻቀበ። ረቡዕ ዕለት ማለዳ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል 111 ዶላር መሸጡ ተዘግቧል።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል እየተካሄደ የነበረው ውይይት በመቋረጡ የእስያ የነዳጅ ገበያ ዳግም ጭማሪ አሳይቷል።

    ሰኞ ዕለት የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ3 በመቶ ጭማሪ በማሳየት በበርሜል 109 ዶላር መሸጡን ቢቢሲ ዘግቧል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን እና በአሜሪካ በመዘጋቱ የዓለም የነዳጅ አቅርቦት ተስተጓጉሏል።

    ኒውዮርክ ታይምስ እንዲሁ በአሜሪካ አማካይ የነዳጅ ዋጋ የኢራን ጦርነተ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ መሆኑን ዘግቧል።

    ማክሰኞ ዕለት በአሜሪካ የነዳጅ ዋጋ በአማካይ በ4.18 በጋሎን ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ይህም የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረበት እአአ ከ2022 ወዲህ ከፍተኛው መሆኑን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  11. ትራምፕ፣ ቴህራን አሜሪካ በተቻለ ፍጥነት የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ትፈልጋለች አሉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ኢራን “የመፈራረስ አደጋ የተጋረጠባት መሆኗን” እና የመሪዎቿን ሁኔታ እስክታውቅ ድረስ አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን በፍጥነት እንድትከፍት መጠየቋን ተናገሩ።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ከኢራን ጋር መልዕክቱን መቼ እንደተለዋወጡ ያልገለጹ ሲሆን ከቴህራን ወገንም የተሰማ ምላሽ የለም።

    “ኢራን ‘የመፈራረስ አደጋ የተጋረጠባት መሆኗን’ ነግራናለች። የመሪዎቻቸውን ሁኔታ እስኪለዩ ድረስ (ያንን ማድረግ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ) በተቻለ ፍጥነት ‘የሆርሙዝ ውሽመጥን በተቻለ ፍጥነት እንድንከፍት’ ይፈልጋሉ” ብለዋል።

    ሮይተርስ ለዋይት ሐውስ በትራምፕ የማኅበራዊ ልጥፍ ዙሪያ ላቀረበው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።

    ትራምፕ ኢራን ለሁለት ወራት የቆየውን ጦርነት ለመፍታት ባቀረበችው አዲስ የመደራደሪያ ሃሳብ ደስተኛ አለመሆናቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረው ነበር።

  12. የባሕረ ሰላጤው አገራት ለኢራን ጥቃቶች ስለሚሰጡት ምላሽ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ሊወያዩ ነው

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ውስጥ የተፈጸመ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የባሕረ ሰላጤው ትብብር ምክር ቤት አባል አገራት መሪዎች የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ሊሰበሰቡ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ።

    የመሪዎቹ ስብሰባ የሚያተኩረው ሁለት ወር በሞላው ጦርነት ለዘነቡባቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ የኢራን የሚሳዔል እና ድሮን ጥቃቶች ምላሽ ማዘጋጀት ላይ እንደሚሆን ዜና ወኪሉ ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል።

    በአሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት የተከፈተባት ኢራን በስድስቱም የባሕረ ሰላጤው ትብብር ምክር ቤት አባል አገራት የሚገኙ የኤነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

    ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተቋማት እና ሌሎች የሲቪል መሠረተ ልማቶችን እንዲሁም ወታደራዊ ይዞታዎችንም አጥቅታለች።

    ሮይተርስ የጠቀሰው የሳዑዲ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያመለክተው የኳታር፣ ኩዌት እና ባህሬን መሪዎች እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በስብሰባው ለመሳተፍ ጅዳ ገብተዋል።

    የምክር ቤቱ አባል የሆነችው ኦማን በማን እንደምትወከል እስካሁን አለመታወቁም ተጠቅሷል።

    የባሕረ ሰላጤው ምክር ቤት ለጦርነቱ በቂ ምላሽ አልሰጠም በሚል ከኤምሬቶች ትችት ቀርቦበት ነበር።

  13. ግዙፉ የነዳጅ ኩባንያ ቢፒ የኢራን ጦርነት ከጀመረ ወዲህ ትርፉ በእጥፍ ማደጉን ገለጸ

    ግዙፉ የነዳጅ ኩባንያ ቢፒ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ግዙፉ የነዳጅ ኩባንያ ቢፒ የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ትርፉ ከእጥፍ በላይ ማደጉን አስታወቀ።

    ቢፒ በነዳጅ ንግድ ውስጥ "እጅግ በጣም ጥሩ" አፈጻጸም ማሳየቱን ገልጾ ከጥር እስከ መጋቢት ባሉት ወራት ብቻ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱን ይፋ አድርጓል።

    ይህ አሃዝ ተንታኞች ከጠበቁት በላይ መሆኑን የገለጸው ኩባንያው፣ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ካስመዘገበው 1.38 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ በእጥፍ እንደሚበልጥ ተናግሯል።

    ይህ ትርፍ የተመዘገበው አዲሷ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሜግ ኦኔል ኃላፊነታቸውን ከተረከቡ በኋላ ነው።

    የካቲት 21/2018 ዓ.ም. የተጀመረው የኢራን ጦርነት የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

    ጦርነቱን ተከትሎ 20 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት የሚያጓጓዝበት የሆርሙዝ ቁልፍ የባህር ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል።

    ብሬንት ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት በአሁኑ ወቅት በበርሜል 110 ዶላር እየተሸጠ ሲሆን፣ የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ዋጋው 73 ዶላር አካባቢ ነበር።

    ኦኔል "ኢንዱስትሪውን በግጭት እና ተግዳሮት በሞላበት ወቅት" ኩባንያውን መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።

    ቢፒ "ደንበኞች እና መንግሥታት በሚፈልጉበት ቦታ ነዳጅ እንዲያገኙ፣ በሰዎች ሕይወት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን መስተጓጎል ለመቀነስ በመሥራት እየረዳ" እንደሆነ ተናግረዋል።

  14. የጀርመኑ ቻንስለር የኢራን አመራሮች አሜሪካን “እያሳፈሯት ነው” አሉ

    የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬድሪክ መርዝ

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬድሪክ መርዝ ሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር የኢራን አመራሮች አሜሪካ ወደ ፓኪስታን አምርታ ያለ ውጤት እንድትመለስ በማድረግ “አሳፍረዋታል” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘገበ።

    ቻንስለሩ ይህንን ያሉት በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ይደረጋል ተብሎ የነበረው የሁለተኛ ዙር የሰላም ውይይት ሳይካሄድ ከቀረ በኋላ ነው።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል መርዝ አሜሪካ ከኢራን ጦርነት ለመውጣት ያዘጋጀችው ስልት መኖሩ እንደማይታያቸው መናገራቸውን ጨምሮ ገልጿል።

    በአሜሪካ እና በአውሮፓውያኑ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) አባል አገራት መካከል በኢራን ጦርነት ዙሪያ ልዩነት አለ።

    ቻንስለሩ ሰኞ ዕለት በመርስበርግ ከተማ ለተማሪዎች ንግግር ባደረጉበት ወቅት አሜሪካኖች ወደ ኢዝላምባድ እንዲጓዙ እና ያለ ምንም ውጤት እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ "ኢራናውያን በመደራደር በጣም የተካኑ ናቸው፤ ወይም ባለመደራደር ክህሎት ያላቸው ናቸው" ብለዋል።

    “በኢራን አመራር ሙሉ ሕዝቡ [አሜሪካውያን] ነው እንዲያፍር የተደረገው፤ በተለይ የአበዮታዊ ዘብ በሚባለው። እናም ተስፋ የማደርገው በተቻለ ፍጥነት [ጦርነቱ] እንዲጠናቀቅ ነው” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኔቶ አጋሮችን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት የባሕር ኃይላቸውን ባለመላካቸው ተችተዋል። የኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ወሽመጡ በመዘጋቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

  15. የሩሲያ ቅንጡ መርከብ እግድ በተጣለበት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል አለፈች

    500 ሚሊየን እንደምታወጣ የተገመተችው ኖርድ፣ ከዱባይ የተነሳችው አርብ ምሽት ነበር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, 500 ሚሊየን እንደምታወጣ የተገመተችው ኖርድ፣ ከዱባይ የተነሳችው አርብ ምሽት ነበር

    ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቁልፍ አጋር ጋር ግንኙነት ያላት ቅንጡ መርከብ በአሜሪካ እና ኢራን እገዳ በተጣለበት የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል አለፈች።

    142 ሜትር የምትረዝመው እና ማዕቀብ ከተጣለበት ሩሲያዊው ቢሊየነር አሌክሲ ሞርዳሾቭ ጋር ግንኙነት ያላት መርከብ ከዱባይ ወደ ሙስካት በሳምንቱ መጨረሻ ተጉዛለች።

    ኖርድ የተሰኘችው ይህች ቅንጡ መርከብ ከቅርብ ወራት ወዲህ በወሽመጡ በኩል ካለፉ ጥቂት መርከቦች መካከል አንዷ ሆናለች።

    የኢራን ልዑካን በዚህ ሳምንት ወደ ሩሲያ በማቅናት ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ተወያይተዋል።

    አንድ አምስተኛ የሚሆነው የዓለም ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ (ኤልኤንጂ) የሚያልፉት በዚህ የባሕር ወሽመጥ በኩል ነው።

    ከፑቲን ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው ሞርዳሾቭ የቅንጦት ጀልባው ባለቤት መሆኑ በግልጽ አይታወቅም።

    ሆኖም ስለ ኖርድ የሰፈሩ መረጃዎች እአአ በ2022 በሚስቱ ባለቤትነት በተያዘ ድርጅት መመዝገቧን ያመለክታሉ።

    500 ሚሊዮን ዶላር እንደምታወጣ የተገመተችው ኖርድ፣ ከዱባይ የተነሳችው አርብ ዕለት ምሽት ነበር።

    ቅዳሜ ማለዳ በኦማን አል ሞኡጅ መድረሷ ተገልጿል። የሩሲያን ባንዲራ የምታውለበልበው ኖርድ የኢራን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ የግል መርከቦች ከአካባቢው ቢርቁም መርከቧ ግን በወሽመጡ ላይ ያለችግር መቅዘፍ ችላለች።

  16. ኢራን ባቀረበችው የድርድር ነጥብ ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደስተኛ አለመሆናቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተናገሩ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ለሁለት ወራት የዘለቀውን ጦርነት ለመቋጨት ኢራን በቅርቡ ያቀረበችው የመደራደሪያ ነጥብ ዶናልድ ትራምፕን እንዳላስደሰታቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

    ይህም የኃይል አቅርቦትን ያስተጓጎለውን፣ የነዳጅ ዋጋን ያናረውን እና የሺዎችን ሕይወት የቀጠፈውን ጦርነት ለማስቆም የነበረውን ተስፋ የሚያጨፈግግ ነው ተብሏል።

    ኢራን በቅርቡ ያቀረበችው የመደራደሪያ ነጥብ ጦርነቱ እስኪቆም ድረስ የኒውክሌር ድርድርን ወደ ጎን የተወ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነጻ የመርከቦችን እንቅስቃሴ እልባት የሚሰጥ ነው።

  17. የአሜሪካ ግምጫ ቤት ኃላፊ ከኢራን አየር መንገዶች ጋር ‘የሚተባበር ማዕቀብ ይጣልበታል’ አሉ

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት ከኢራን አየር መንገዶች ጋር የሚተባበሩ ኩባንያዎች ማዕቀብ እንደሚጣልባቸው አስጠነቀቁ።

    ኃላፊው በኤክሰ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ እርምጃ አገራቸው ኢራን ላይ የምታደርገው የምጣኔ ሃብት ጫና አካል መሆኑን ተናግረዋል።

    ቤስንት መንግሥታት በሥራቸው የሚገኙ ኩባንያዎች ለኢራን አውሮፕላኖች አገልግሎት ላለመስጠት አስፈላጊውን ጥንቀቄ እንዲያደርጉ አስጠንቅቀዋል።

    ቤሴንት መንግሥታት ለኢራን አውሮፕላኖች “ነዳጅ መቅዳት፣ የምግብ አቅርቦት አገልግሎት መስጠት እና የአውሮፕን ማሳረፊያ ክፍያዎች ወይም አውሮፕላን ጥገናዎችን” እንዳይሰጡ አስጠንቅዋል።

    የአገሪቱ ግምጃ ቤት “ከኢራን ጋር ንግድ በሚያካሄዱ ወይንም በሚያመቻቹ ሦስተኛ ወገኖች ላይ እርምጃ ለመውሰድ አያመነታም” ብለዋል

    የኢራን አየር መንገዶች በሳምንቱ መጨረሻ ከጦርነቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በረራ መጀመራቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከቴህራን መንገደኞችን የጫኑ አውሮፕላኖች ወደ ኢስታንቡል፣ ኦማን፣ ኢረቅ፣ ኳታር እና ወደ ሳዑዲ ከተማ መዲና መብረራቸውን ዘግበዋል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ዋሸንግተን በኢራን መንግሥት ላይ “ጠናካራ የፋይናንስ ማነቆ” ማስቀመጧን ገልጿል።

    ቤሴንት በኤክስ ገጻቸው ላይ “ማዕቀብ ከተጣለባቸው አየር መንገዶች ጋር መስራት ለአሜሪካ ማዕቀብ ያጋልጣል” ሲሉ ጽፈዋል።

    የትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣን የግምጃ ቤት ዲፓርትመንት "የኢራንን እንቅስቃሴ ማቀላጠፍ በሚቀጥሉ" በውጭ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ሁለተኛ ደረጃ ማዕቀብ እንደሚጥል ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት በተለይም የኢራንን የነዳጅ ኤክስፖርትና የፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የተለያዩ ማዕቀቦችን ጥሏል።

  18. ቴህራን አሜሪካንን በዓለም አቀፍ ውሃ ላይ "የባህር ላይ ውንብድና" በመፈጸም ወነጀለች

    ቴህራን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን በሕንድ ውቅያኖስ ስለተያዘባት ድፍድፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በሰጠቸው ምላሽ ይህ “የባሕር ላይ ውንብድና ነው” አለች።

    አሜሪካ የኢራንን ነዳጅ የጫነች መርከብ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ በቁጥጥር ስር ያዋለችው ባለፈው ሳምንት ነበር።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ የአሜሪካን እርምጃ “የባሕር ላይ ውንብድና” ሲሉ በኤክሰ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    “ይህ ድርጊት በግልጽ የባሕር ላይ ውንብድናን ሕጋዊ ማድረግ ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ “በባሕሮች ላይ የሚፈጸም በትጥቅ የታገዘ ሽፍትነት ነው” ሲሉ አክለዋል።

    “ወደ ባሕር ላይ ውንብድና እንኳን በደህና መጣችሁ። አሁን ይህ የሚከናወነው ይፋዊ የመንግሥት ፈቃድ ባለው፣ በይፋ ባንዲራውን በሚያውለበልብ እና ወንጀሉን ‘ሕግ ማስከበር’ ሲል በሚጠራ አካል መሆኑ ነው” ሲሉ ቃል አቀባዩ የአሜሪካን እርምጃ ኮንነዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አክለውም “ዩናይትድ ስቴትስ ሙሉ በሙሉ ለዚህ ሕገወጥ ባሕሪዋ ተጠያቂ መሆን አለባት” በማለት ድርጊቱ “የዓለም አቀፍ ሕጎች እና የዓለም ነጻ ንግድ መሠረቶችን የሚጥስ የባሕር ላይ ትራንስፖርት መርሆችን የሚንድ ነው” ብለውታል።

    ቃል አቀባዩ ምላሽ የሰጡት የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጄኒን ፌሪስ ፒሮ የነዳጅ ጫኝ መርከቧን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል መያዣ ማውጣታቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ ነው።

    የአሜሪካ ጦር ባለፈው ሳምንት በሕንድ ውቅያኖስ ላይ 1.9 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የጫነች የኢራን መርከብን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቆ ነበር።

  19. ፑቲን ሩሲያ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ለማምጣት ማንኛውንም ነገር ታደርጋለች አሉ

    የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ለማምጣት ማንኛውንም ነገር እንደምታደርግ መናገራቸውን ታስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከኢራኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር በሴንት ፒተርስበርግ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ በውይይታቸው ወቅት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ለቴህራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢራን ሕዝቦች ለሉዓላዊነታቸው በድፍረት መታገላቸውን መናገራቸውን የሩሲያ ብሔራዊ የዜና ወኪል ታስ ዘግቧል።

    ታስ አክሎም ፑቲን ኢራን ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ ካለፈች በኋላ ሰላም እንደምትፈልግ ያላቸውን ተስፋ መግለጣቸውን ጠቅሷል።

    የዜና ኤጀንሲው ፑቲን ለኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራጋቺ፣ ሩሲያ “በመካከለኛው ምሥራቅ በተቻለ ፍጥነት ሰላም ለማምጣት ማንኛውንም ነገር እንደምታደርግ” መናገራቸውን ዘግቧል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው በሞስኮ እና በቴህራን መካከል ያለው ግንኙነት "እየተጠናከረ የሚሄድ" ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሆኑን መናገራቸውን የሩሲያ የመንግሥት ቴሌቪዥን ዘግቧል።

    የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ለማነጋገር ወደ ሞስኮ የተጓዘው የኢራን ልዑካን ቡድን ውስጥ ምክትል የውጭጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ እና በሞስኮ የኢራን አምባሳደር ካዜም ጃላሊ ይገኙበታል።

    የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሩሲያ ቴህራን እና ዋሺንግተን በሚያደርጉት ቀጣይ ድርድሮች "በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ያለው የማደራደር አገልግሎት" ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

    “የተረጋገጠ ሰላም፤ በዘላቂነት የሚቆይ እና ወደ ግጭት ዳግም መመለስ የሌለበት ሰላምን ለማረጋገጥ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ዝግጁ ነን” ሲሉ መናገራቸውን መገናኛ ብዙኃኑ ዘግቧል።

    አራግቺ በሴንት ፒተርስበርግ ለጋዜጠኞች ኢራን “የዓለም ታላቅ ልዕለ ኃያል [ዩኤስ] በመፋለም ላይ ነች” በማለት ዋሽንግተን “አንድም ግቧን አላሳካችም” ብለዋል።

    "ለዚህም ነው ድርድር የጠየቁትና እየተመለከትን ያለነው" ሲሉም አክለዋል።

    አሜሪካ ግን ድርድር ስለመጠየቋ ምንም ያለችው ነገር የለም።

    የኢራን ከፍተኛ ዲፕሎማት ጦርነቱ ኢራን “እንደ ሩሲያ ያሉ ታላላቅ ወዳጆች እና አጋሮች እንዳሏት” ያሳየ ነው ብለዋል።

  20. የሊባኖስ ፕሬዚዳንት የተኩስ አቁሙን በመጣስ ሄዝቦላህን ተቹ

    የእስራኤል እና የሊባኖስ ባንዲራዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን ከእስራኤል ጋር የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም በሚያደርጉት ጥረት “የሚያሳፍር ስምምነት” እንደማይቀበሉ ገለፁ።

    ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው ከድርድሩ መጀመርያው ጀምሮ ለአሜሪካ “የተኩስ አቁም አስፈላጊ የመጀመርያ እርምጃ” መሆኑን መናገራቸውን ገልጸዋል።

    አክለውም በደቡባዊ ሊባኖስ የሚኖሩ “የሌሎች ጦርነትን ዋጋ በግዛታችን ላይ እየከፈሉ ነው” ብለዋል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ የደረሱት የተኩስ አቁም በሦስት ሳምንት የተራዘመው ባለፈው ሳምንት ነው።

    ነገር ግን እስራኤል እና በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ የሚያደርጉት ውጊያ ቀጥለዋል።

    ሄዝቦላህ በቀጠናው ስላለው ሰላም በሚደረግ ድርድር ላይ አልተካተተም።

    ኦውን ጦርነቱ የተካሄደው “ለሊባኖስ ተብሎ ቢሆን” እደግፈው ነበር፤ ነገር ግን “ጦርነቱ የሚካሄደው የሌሎችን ፍላጎት ለማሳካት ሲሆን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አደርገዋለሁ” ብለዋል።

    “እኛ እያደረግን ያለነው የአገር ክህደት አይደለም፤ ይልቁንም የአገር ክህደት የሚፈጸመው የውጭ ጥቅሞችን ለማስከበር አገራቸውን ወደ ጦርነት በወሰዱት ነው” ሲሉ ሄዝቦላህን ሸንቁጠዋል።

    በደቡባዊ ሊባኖስ የእስራኤል የአየር ድብደባ እንደቀጠለ ነው። እሁድ ዕለት ብቻ በእስራኤል የአየር ድብደባ 14 ሰዎች ሲገደሉ ሁለት ሕጻናት እና ሁለት ሴቶችን ጨምሮ 37 ሰዎች መጎዳታቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ቅዳሜ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የአገሪቱ ጦር ሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ “የሄዝቦላህ ዒላማዎችን በኃይለኛው እንዲያጠቁ” ትዕዛዝ ሰጥተዋል። በዚሁ ዕለት ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ስድስት ሰዎች ተገድለዋል።