ከሁለት ወር በፊት ኢራን ላይ የተከፈተው ጦርነት እስካሁን አሜሪካን 25 ቢሊዮን ዶላር እንዳስወጣት የዋሽንግተን መከላከያ መስሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊ ተናገሩ።
አሜሪካ በኢራን ጦርነት ምን
ያህል ገንዘብ ወጪ እንዳደረገች በይፋ ሲገለጽ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የአሜሪካ መከላከያ ሚንስትር ፒት ሄግሴት ከኢራን
ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በቃለ መሃላ ስር ሆነው በሰጡት ስድስት ሰዓት በቆየ የምክር ቤት ማብራሪያ ላይ ከዴሞክራቲክ ሕግ አውጪዎች
ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።
መከላከያ ሚንስትሩ ትናንት ረቡዕ በተወካዮች
ምክር ቤት የጦር አገልግሎት ኮሚቴ ፊት የቀረቡት ከአሜሪካ ጦር የጋራ ጦር አዛዦች ኃላፊ ጄነራል ዳን ኬን እና ከመከላከያ መስሪያ
ቤቱ የፋይናንስ ዋና ኃላፊ ጁሌስ ኸርትስ ጋር በመሆን ነው።
ሄግሴት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር “የተጋፈጥነው
ትልቁ ጠላት” የዴሞክራቶች እና የተወሰኑ ሪፐብሊካኖችን “የሽንፈት ቃላቶች ነው” ብለዋል።
የኮሚቴው አባል የሆኑ ዴሞክራት ሕግ አውጪዎች
ከኢራን ጋር በሚደረገው ጦርነት የፌደራል መንግሥቱ ገንዘብ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝበትን መንገድ ተችተዋል።
ከመከላከያ
መስሪያ ቤቱ የፋይናንስ ዋና ኃላፊ ኸርትስ ባደረጉት ንግግር እስካሁን ለጦርነቱ 25 ቢሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።
ኸርትስ እንደገለጹት አብዛኛው ገንዘብ የወጣው
ለተተኳሽ እና መሣሪያዎችን ለመተካት ነው። የወጪው ሙሉ ዝርዝር ከጊዜ በኋላ እንደሚቀርብ ለሕግ አውጪዎች ተናግረዋል።
አሜሪካ እና ኢራን የሰላም ንግግር ለማድረግ
ተኩስ አቁም ላይ ቢደርሱም ጦርነቱ በይፋ አልተቋጨም።
በምክር ቤቱ ውሎ ዋነኛ መነጋገሪያ ከሆኑ ነጥቦች
አንዱ ገንዘብ ነው። ዋይት ሀውስ የአሜሪካ የመከላከያ በጀት በ1.5 ትሪሊዮን ዶላር እንዲጨምር ለኮንግረስ ጥያቄ አቅርቧል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የአሜሪካ ወታደራዊ
ወጪ በዚህ ደረጃ ከፍ ሲል ይህ የመጀመሪያው ነው።
መከላከያ ሚንስትሩ ሄግሴት የበጀት ጥያቄው “ጊዜው
የሚጠይቀውን አጣዳፊነት ያሳያል” ሲሉ ለኮሚቴው ተናግረዋል።
ጄነራል ኬን በበኩላቸው 1.5 ትሪሊዮን ዶላር
አሜሪካ በፍጥነት የሚያድግ ቴክኖሎጂ መታጠቅ እንድትችል የሚያግዝ “ለወደፊት ደኅንነት የሚውል ታሪካዊ ቅድመ ክፍያ” ነው ብለዋል።
የኮሚቴው አባላት የሆኑ ዴሞክራቶች የአሜሪካ ጦር ኢራን ላይ የሚያካሂደውን ዘመቻ ብዙውን ጊዜ የሚገልጹት ያለ ኮንግረስ ፈቃድ እንደተከፈተ “የምርጫ ጦርነት” ነው።
የካሊፎርኒያው ዴሞክራቲክ ተወካይ ጆን ጋራሜንዲ፤
“ጦርነቱን በተመለከተ ከመጀመሪያው ዕለት አንስቶ የአሜሪካ ሕዝብን ስትዋሹ ነበር” ሲሉ ባለሥልጣናቱን ወቅሰዋል።
ትራምፕ በሌላ
የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት “አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል” ሲሉም ለሄግሴት ተናግረዋል።
የምክር ቤት አባሉን አስተያየት “ግድ የለሽ”
ሲሉ የጠሩት ሄግሴት በበኩላቸው፤ ትራምፕ “አጣብቂኝ” ውስጥ ናቸው መባሉን አስተባብለዋል። “ለትራምፕ ያለህ ጥላቻ አውሮሃል” ሲሉም
የምክር ቤት አባሉን ተናግረዋል።
የኮሚቴው አባል የሆኑ አብዛኞቹ ሪፐብሊካኖች
ከመከላከያ መስሪያ ቤቱ ጎን ቆመዋል። የኮንግረስ አባሉ ካርሎስ ጊሜኔዝ ኢራን የህልውና ስጋት ናት ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።