የዚምቧብዌ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ልጅ ከደቡብ አፍሪካ ሊባረር ነው
የዚምባብዌ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ የመጨረሻ ልጅ በአስቸኳይ ከደቡብ አፍሪካ እንዲባረር የጆሃንስበርግ ፍርድ ቤት ወሰነ።
ቤላርማይን ሙጋቤ በዚህ ወር መጀመርያ ላይ በመኖሪያ ቤቱ የ23 ዓመት ወጣት ላይ በመተኮሱ የተከሰሰ ሲሆን ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።
የ28 ዓመቱ የሙጋቤ ልጅ መሳሪያ በመደቀን እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያለ ሕጋዊ ፈቃድ በመኖር ጥፋተኛ መሆኑ ተገልጿል።
ፍርድ ቤት በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ 36,000 ዶላር እንዲከፍል ወስኖበታል።
አብሮት የተከሰሰው የአጎቱ ልጅ ቶቢያስ ማቶንሆድዜ በግድያ ሙከራ፣ በሕገወጥ ስደት፣ የጦር መሣሪያ በመያዝ እና በፍትህ ስርዓቱ ላይ ጣልቃ በመግባት ወንጀሎች የሦስት ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
ሁለቱም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአስር ቀን በፊት ፖሊስ በጆሃንስበርግ በሚገኘው የሙጋቤ ልጅ ቤት ተጠርቶ ከመጣ በኋላ ነው።
በቅጥር ግቢው ውስጥ ይሰራ የነበረው ግለሰብ በጥይት ተመትቶ ክፉኛ በመጎዳቱ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።
አቃቤ ሕጎች ለፍርድ ቤቱ ግለሰቡ ላይ የተተኮሰው በቅጥር ግቢው ውስጥ ሦስት ሰዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን አስረድተዋል።
አክለውም ግለሰቡ ለማምለጥ ሲሞክር ከኋላው ሁለት ጊዜ ተተኩሱበት መመታቱን ገልጸዋል።
ፖሊስ የመኖሪያ ቤቱ ላይ ብርበራ ያካሄደ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የጦር መሣሪያውን አላገኘም።