የጂቡቲው ፕሬዚዳንት 97.8 በመቶ የመራጮች ድምጽ በማግኘት ለስድስተኛ ጊዜ አሸነፉ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ 97.8 በመቶ የመራጮች ድምጽ በማግኘት ቀጣዩ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል።

ይፋ የሆኑ የመጀመርያ ውጤቶች እንደሚያሳዩት ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ በአፍሪካ ቀንድ ወሳኝ ስፍራ ላይ የምትገኘውን ጂቡቲን ለስድስተኛ ጊዜ መምራት የሚያስችላቸውን ድምጽ አግኝተዋል።

አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ባገለሉበት አገራዊ ምርጫ ብቸኛ ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት የ78 ዓመቱ ብቸኛ ተፎካካሪያቸው ሞሃመድ ፋራህ ሳማታር 2.19 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል።

ላለፉት 27 ዓመታት አገሪቱን የመሩት ኦማር ጊሌ ከሥልጣን እንደሚወርዱ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በኅዳር ወር ሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ ከተደረገ እና የእድሜ ገደቡ ከተነሳ ወዲህ ራሳቸውን በዕጩነት አቅርበዋል።

የጊሌ ዘመቻ ሌሎች የቀጣናው መንግሥታት እና መካከለኛው ምሥራቅ በግጭት በሚታመሱበት ወቅት በጂቡቲ ውስጥ መረጋጋትን ማስጠበቃቸው ላይ ያተኮረ ነበር።

በባብ ኤል-ማንዴብ ወሽመጥ ላይ የምትገኘው ጂቡቲ፣ በዓለም ላይ በጣም እንቅስቃሴ ከሚበዛባቸው የባሕር ላይ ትራንስፖርት መስመሮች አንዱ ወደሆነው ወደ ሱዊዝ ካናል መግቢያ በር ሆና ታገለግላለች።

አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና ጃፓን በአገሪቱ ውስጥ ወታደራዊ ጦር ሠፈሮች አሏቸው።

ጊሌ ጅቡቲ እአአ በ1977 ከፈረንሳይ ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት ናቸው።

ዋና ዋና የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች እአአ ከ2016 ጀምሮ በአገሪቱ ነጻ የሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የለም በሚል ራሳቸውን ከምርጫው አግልለዋል።

ጊሌ ለስድስተኛ ጊዜ አገሪቱን እንዲያስተዳድሩ በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጹ ይህ ድል የመላው አገሪቱ ነው ብለዋል።

ባለሥልጣናት እንዳሉት ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የተመዘገቡ መራጮች አርብ ዕለት በተካሄደው ምርጫ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

የአነስተኛ ፖለቲካ ፓርቲ ተመራጭ የሆኑት ሳማታር እስካሁን ምንም አስተያየት አልሰጡም።

ውጤቶቹ ይፋ የሆኑት በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሆንም፣ ጉሌ ለተጨማሪ አምስት ዓመታት አገሪቱን ለመምራት ቃለ መሃላ ከመፈጸማቸው በፊት በሕገ መንግሥቱ ምክር ቤት ውስጥ ባሉ ዳኞች መረጋገጥ አለባቸው።

ፕሬዚዳንት ኦማር ጊሌ እአአ በ2021ቱን ምርጫም በተመሳሳይ ልዩነት አሸንፈዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2010 የጂቡቲ ፓርላማ የሥልጣን ዘመን ገደብን ያነሳ ሲሆን በተጨማሪም አንድ የሥልጣን ዘመንንም ከስድስት ወደ አምስት ዓመት ዝቅ እንዲል አድርጓል።

እንዲሁም 75 ዓመት የእጩዎች የዕድሜ ጣሪያ ውሳኔ አሳልፎ የነበረ ቢሆነም ይህም በኅዳር ወር ሕገ መንግሥቱን ፕሬዚዳንት ኦማር ጊሌ ዳግም መወዳደር እንዲችሉ ተቀይሯል።