በካናዳ ጦር ሠፈር ውስጥ በተነሳ እሳት አራት ሰዎች ሲሞቱ፣ በርካቶች ቆሰሉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በካናዳ አልበርታ ግዛት ውስጥ በሚገኝ የጦር ሰፈር ውስጥ በተነሳ ከባድ እሳት፣ አራት አገሪቱ ሠራዊት አባላት ሲሞቱ፣ በርካታ ሰዎች ተጎዱ።

ከዋና ከተማዋ ኦታዋ ለሕዝብ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ፣ "ሰላም በሆነበት ወቅት በካናዳ ምድር በሠራዊቱ ላይ ከደረሱ አስከፊ አሳዛኝ ክስተቶች አንዱ ነው" ሲሉ የተነሳውን እሳት ገልጸውታል።

በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ቅዳሜ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ እሳት የተነሳው የአገሪቱ ሥራ የሚበዛበት የጦር ሠፈር ማሰልጠኛ በሆነው የዌይንራይት ጦር ሠፈር ነው።

እሳቱ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፣ በምን ምክንያት እንደተነሳ እስካሁን ግልጽ አይደለም። ባለሥልጣናት ክስተቱት "ከሽብር እንቅስቃሴ" ጋር የተያያዘ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ካርኒ፣ "አገሪቱ በሞት ላጣናቸው ጀግና የጦር ኃይላችን አባላት ሐዘን ላይ ናት" ብለዋል።

ቢቢሲ በእሳቱ ምክንያት ሕይወታቸው ያጡትን አራት ወታደሮች ማንነት አረጋግጧል። ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱት 39 ሰዎች ውስጥ ቢያንስ 19 የሚሆኑት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የአልበርታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳንኤል ስሚዝ እሁድ ምሽት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

የእሳት አደጋ እና ነፍስ አድን ቡድኖች በድጋሚ እሳት እንዳይነሳ ለመቆጣጠር በስፍራው እንደሚቆዩ የዌይንራይት ከንቲባ ብሩስ ፑግ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በጦር ሠፈሩ የነበሩ እግረኛ ወታደሮች "ጥይት ጥቅም ላይ የሚውልበት ከፍተኛ ውጊያ ስልጠና" ላይ እንደነበሩ መግለጫው ላይ የተገኙት ሜጀር ጄኔራል ዌድ ሩትላንድ ተናግረዋል።

በጦር ሠፈሩ የማሠልጠኛ ስፍራ ውስጥ ቦምብ ማስወንጨፊያ፣ የእጅ ቦምቦች፣ አነስተኛ የጦር መሣሪያዎች እና ጥይቶችን ጨምሮ እጅግ በርካታ "የጦር መሣሪያዎች ሲንቀሳቀሱ" እንደነበር አስረድተዋል።

እሳቱ የተነሳበት ምክንያት አሁንም ላይ በምርመራ ላይ ቢሆንም አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት የተነሳ ሰደድ እሳት ወደ ማሰልጠኛ ስፍራው ተዛምቷል።

"መናገር ነገር ቢኖር፣ በወቅቱ በመላው ማሰልጠኛ ስፍራ በርካታ የስልጠና እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ ነበር። ያልተለመደው ኃይለኛ ንፋስ [መኖሩ] እሳቱ በፍጥነት እንዲዛመት እና ወደ ማሰልጠኛው የአስተዳደር ስፍራ አቅጣጫውን እንዲቀይር አድርጎታል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከንቲባ ፑግ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በጦር ሰፈሩ የመድፍ ተኩስ ሲሰማ የነበረ ሲሆን በድንገትም ቆሟል። ይሁን እንጂ በጦር ሰፈሩ የመድፍ ተኩስ መስማት ያልተለመደ ነገር እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ካርኒ በበኩላቸው ሠራዊቱ እና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች "ለማሰብ በሚከብድ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ" ሆነው ምሽቱን በሙሉ እሳቱን መጋፈጣቸውን ተናግረዋል።

ጉዳት ደረሰባቸው በማሰልጠኛ አካባቢው የነበሩ ሰዎች እንደሆኑ እና ተጠባባቂ ወታደሮችም እንደሚገኙበት ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የካናዳ ጦር እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ "በዚህ ሰዓት ክስተቱ ምርመራ እየተደረገበት ቢሆንም፣ የማንኛውም የሽብር እንቅስቃሴ ውጤት መሆኑን የሚያመላክት ነገር የለም" ብሏል።