ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ህወሓት ለፌደራል መንግሥት እጅ የሰጡትን ሜጀር ጄነራል ጆን መዲድ "በከሃዲነት" ከሰሰ
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ፣ በፌደራል መንግሥት እጅ የገቡትን የትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ሜጀር ጀነራል ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስን (ጆን መዲድ) በ"ክህደት" ወነጀለ።
በቅርቡ የነበሩ ውጊያዎችን በተመለከተ እየተደረገ ያለው "ግምገማ እና ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት በመረዳት" ስብሰባ ላይ አለመገኘታቸውን የጠቀሰው ህወሓት፣ "በአንጻሩ ከጠላት ጋር ትስስር" ፈጥረዋል ሲል ከስሷል።
በህወሓት የሚመራው እና ትግራይ ክልል ተቆጣጥሮ የነበረው አስተዳደር ይህንን ያለው፣ 'ጆን መዲድ' በሚለው መጠሪያ ይበልጥ የሚታወቁት ወታደራዊ አዛዥ እጅ መስጠታቸው በስፋት ከተነገረ በኋላ፣ ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው።
በመስከረም አጋማሽ በተጀመረው ጦርነት በደቡባዊ ትግራይ ሲንቀሳቀስ የነበረውን የትግራይ ኃይሎች የደቡብ ግንባር ዕዝ ሲመሩ የነበሩት ሜጀር ጀነራል ዮሐንስ፣ የፌደራል መንግሥት እና አጋሮቹ እጅ የገቡት ሰኞ ዕለት ነበር።
ወታደራዊ አዛዡ፣ ለመከላከያ ሠራዊት እና ለአጋር ለሆኑት የትግራይ የሰላም ኃይሎች "እጃቸውን መስጠታቸውን" በትግራይ ባለአደራ አስተዳደር የፀጥታ እና ሰላም ዋና አስፈጻሚ የሆኑት ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር በየነ እና ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ቅርበት ያላቸው ሁለት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እንደ ምንጮች ገለጻ፣ ጆን መዲድ እና የኮሎኔልነት ማዕረግ እንዳላቸው የተገለጹ ሌሎች ሰባት አዛዦች በማዕከላዊ ትግራይ ዞን ራማ ወረዳ 'ስምረት' በተባለ አካባቢ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና አጋሮቹ "ተከበው" ነበር።
መዲድ በመከላከያ እጅ ከገቡ በኋላ ወደ አድዋ ከተማ መወሰዳቸውን ከምንጮቹ አንዱ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል። የትግራይ ሰላም ኃይል አዛዥ የሆኑት ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው ጆን መዲድ "እጅ መስጠታቸውን" ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ህወሓት ባወጣው መግለጫ፣ ወታደራዊ አዛዡ "የተሰዉ ጀግኖችን በመክዳት" ወደ ፌደራል መንግሥት መምራታቸውን በመግለጽ ከስሷል።
ጆን መዲድ፣ መስከረም 13 ቀን በተቀሰቀሰው ውጊያ "በርካታ አርሚዎችን በመምራት የትግራይ ሕዝብን ከአደጋ ለመከላከል ከትግራይ መንግሥት ተልዕኮ" እንደተሰጣቸው አስታውሷል።
ይሁን እንጂ ከዚህ ስምሪት በኋላ "ችግሮች መታየት በመጀመራቸው በብሔራዊ ትግሉ ላይ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ለመከላከል የተለየ ውሳኔ እንደተወሰነ" ገልጿል።
አንድ ወር ባለፈው ውጊያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በበርካታ የትግራይ አካባቢዎች የነበራቸውን ቁጥጥር ማጣታቸውን ተከትሎ ጆን መዲድ፣ ከደቡብ ግንባር አዛዥነታቸው እንደተነሱ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል። የዕዙን መሪነት ለብርጋዴር ጄኔራል አብርሃ ተስፋይ (ድንኩል) እንዳስረከቡም አስረድተዋል።
ጆን መዲድ "ከትግራይ ሠራዊት አሃዶች እና ከማዕከላዊ ዕዝ ተነጥለው ለብቻ" እንደነበሩ የጠቀሰው ህወሓት በበኩሉ፣ የግምገማ መድረኩ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ተደርጎላቸው እንደነበር አስታውቋል።
"ሆኖም ግን ሠራዊታችን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ግምገማ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት በመረዳት ወደ መድረኩ መምጣት አልፈለጉም" ሲል በመግለጫው አስፍሯል።
"በአንጻሩ ከጠላት ጋር ትስስር" ፈጥረዋል ያለው መግለጫው፣ ሌሎች "አመራሮች እና የስታፍ አባላት እየተዋጉ ሲያመልጡ" ጆን መዲድ "ጠላትን ተቀላቅለዋል" ብሏል።
"እርሱ እና ጥቂት አባላት ቀድሞ ወደጠራቸው ጠላት በመቀላቀል የትግራይ ሕዝብ እና የተሰዉ ጀግኖችን መክዳቱን መላ ሕዝባችን እና ሠራዊታችን ሊያውቅ ይገባል" ሲል ከስሷል።
የሜጀር ጀነራል ዮሐንስን እጅ መስጠት በተመለከተ እስካሁን ድረስ ከፌደራል መንግሥት በኩል የተሰጠ ይፋዊ ማብራሪያ የለም። ቢቢሲም ክስተቱን በተመለከተ ከራሳቸው ጆን መዲድም ሆነ ሌላ ገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አልቻለም።
ጆን መዲድ ማናቸው?
በ1954 ዓ.ም. በትግራይ ክልል አክሱም አቅራቢያ 'ናዕዴር አዴት' በተባለ ስፍራ የተወለዱት ጆን መዲድ፣ ረጅም ወታደራዊ ልምድ ያላቸው አዛዥ ናቸው። ደርግን ለመጣል ሲደረግ የነበረውን ትግል የተቀላቀሉት በ17 ዓመታቸው ሲሆን ቀጥሎም በኢትዮ ኤርትራ እና በቅርብ ጊዜ የትግራይ ጦርነቶች ውስጥ ተሳትፈዋል።
በ17 ዓመቱ የህወሓት ትግል ወቅት ከተሳተፉባቸው ተጠቃሽ ውጊያዎች አንዱ በኤርትራ 'ናቅፋ' የተባለ ቦታ የተደረገው ነው። በወቅቱ ከሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ ጋር በአንድነት ተሰልፈው የነበሩት የህወሓት ኃይሎች ከባድ የአየር ድብደባ እና ውጊያ አስተናግደው እንደነበር ይነገራል።
ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ፣ በርካታ የትግል ጓዶቻቸውን ከሞቱበት ይህ ውጊያ በሕይወት የመትረፋቸውን ጉዳይ ለመረዳት እንደሚቸገሩ ይናገራሉ። ከኤርትራ አገር ሆና ከተመሠረተች በኋላ ገንዘቧን የሰየመችው ይህ ከባድ ውጊያ በተደረገበት 'ናቅፋ' ስም ነው።
ከደርግ መውደቅ በኋላ መከላከያ ሠራዊትን የተቀላቀሉት ጆን መዲድ፣ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በቡሬ ግንባር በወታደራዊ አዛዥነት አገልግለዋል። ቀጥሎም በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን እና መካከለኛው ዕዝ በአመራርነት ስፍራዎች ሰርተዋል።
የኢትዮጵያ ጦር በእስላማዊ ታጣቂዎች የበላይነት የተወሰደበትን የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ለመደገፍ ወደ ሞቃዲሾ በዘመተበት ወቅትም የዘመቻ አስተባባሪ ነበሩ።
ሜጀር ጄነራል ጆን መዲድ ከመከላከያ ሠራዊት በጡረታ የተገለሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ከአጭር ጊዜ በኋላ ነበር። ወደ መቀለ ተመልሰውም የትግራይ ኃይሎችን የማደራጀት ተግባር ላይ ተሳትፈዋል።
በ2013 ዓ.ም. የትግራይ ጦርነት ተነስቶ የትግራይ ኃይሎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዋና ከተሞች ከወጡ በኋላ፣ ታጣቂዎችን መልሶ የማደራጀት ተግባር ውስጥም ቁልፍ ሚና እንደነበራቸው ይነገራል። በጦርነቱ የትግራይ ኃይሎች ካካሄዷቸው ዋነኛ ኦፕሬሽኖች ጋርም ስማቸው ተያይዞ ይነሳል።
ጆን መዲድ፣ ከፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም በኋላ በነበሩት ዓመታት ከወታደራዊ አዛዥነት ባሻገር የፖለቲካ ሰው ሆነው ብቅ ብለዋል። በጌታቸው ረዳ ፕሬዝዳንትነት የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ በይፋ ትችት ያቀርቡም ነበር።
የሚያደርጓቸው አወዛጋቢ ፖለቲካዊ ንግግሮች ፖለቲካዊ ስብዕናቸውን እያጎሉት መጥተዋል። በትግራይ አመራሮች ክፍፍል በዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ለሚመራው ክንፍ በመወገን የያዙትን አቋም የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ፣ ለተፈጠረው ፖለቲካዊ መከፋፈል አስተዋጾ እንዳደረጉ በመጥቀስ የሚወቅሷቸውም አሉ።