አምስተርዳም በአደባባዮች ስጋን እና ነዳጅ የሚጠቀሙ ምርቶችን ማስተዋወቅ አገደች

አምስተርዳም የስጋ እና ነዳጅ የሚጠቀሙ ምርቶችን በአደባባይ ማስተዋወቅ የከለከለች የመጀመሪያዋ ከተማ ሆናለች።
እአአ ከግንቦት 1 ጀምሮ ለበርገር፣ ለቤንዚን መኪናዎች እና ለአየር መንገዶች የሚደረጉ ማስታወቂያዎች ከቢልቦርዶች፣ ከአውቶቡስ እና ቀላል ባቡር መጠበቂያዎች እና ከባቡር ጣቢያዎች እንዲነሱ ተደርገዋል።
በከተማው ውስጥ ቀላል ባቡር በሚንቀሳቅስባቸው ፌርማታዎች ላይ ተለጥፈው የነበሩ ማስታወቂያዎች እንዲነሱ ተደርገዋል።
አሁን በምትኩ የኔዘርላንድስ ብሔራዊ ሙዚያም እና የፒያኖ ኮንሰርት ማስታወቂያዎች ተሰቅሎባቸዋል።
እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ በእነዚህ ስፍራዎች የዶሮ ጥብስ፣ ኤስዩቪ መኪና እና ዝቅተኛ ወጪ የሚጠይቁ በዓላትን የሚያስተዋውቁ ፖስተሮች ተለጥፈው ነበር።
የከተማዋ ፖለቲከኞች ይህ እርምጃ የአምስተርዳምን የመንገድ ገጽታ ከአካባቢው አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ግቦች ጋር ለማጣጣም የተወሰነ ነው ብለዋል።
እነዚህ ዓላማዎች የኔዘርላንድ ዋና ከተማ በ2050 ከካርቦን ልቀት ነፃ እንድትሆን እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ የስጋ ፍጆታቸውን በግማሽ እንዲቀንሱ ለማድረግ ያለመ ነው።
"የአየር ንብረት ቀውስ በጣም አጣዳፊ ነው" ያሉት የግሪንሌፍት ፓርቲ አባል አኔኬ ቪንሆፍ ናቸው።
"በአየር ንብረት ፖሊሲዎች ውስጥ ግንባር ቀደም መሆን ከፈለጉ እና የጎዳና ማስታወቂያዎች ወደ ተቃራኒው መንገድ የሚጓዙ ከሆነ ምን እያደረጉ ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።
"አብዛኛዎቹ ሰዎች ማዘጋጃ ቤቱ ተቃውሟችንን እያሰማን ፖሊሲ ላወጣንበት ጉዳይ ለምን የሕዝብ ስፍራዎችን በመከራየት ገንዘብ እንደሚያገኘ አይረዳም" ሲሉ ተናግረዋል።
በእንስሳት መብቶች ላይ የሚያተኩረው ፓርቲ ፎር ዘ አኒማልስ መሪ አንኬ ባከርም ይህንን ሃሳብ ይጋሩታል።
አዲሶቹን ገደቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ በመወትወት ግንባር ቀድም ሲሆኑ ከተማዋ የእነዚህ ማስታወቂያዎች ሞግዚት መሆን የለባትም ሲሉ ይሞግታሉ።
ባከር "እያንዳንዱ ሰው የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይችላል፤ ነገር ግን እንደ እውነቱ ከሆነ ትላልቅ ኩባንያዎች ምን መመገብና መግዛት እንዳለብን ሁልጊዜ እንዳይነግሩን ለማድረግ እየሞከርን ነው" ብለዋል።
"በአንድ በኩል ሰዎች የራሳቸውን ምርጫ ማድረግ ስለሚችሉ የበለጠ ነፃነት እየሰጠናቸው ነው አይደል?" ሲሉ ይጠይቃሉ።
በአምስተርዳም የስጋ ማስታወቂያዎች ያላቸው ድርሻ ከነዳጅ ምርቶች ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
የውጭ ማስታወቂያዎች የበለጠ የተያዙት በልብስ፣ በፊልሞች እና በሞባይል ስልኮች ነው።
ነገር ግን እገዳው የፖለቲካ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ተጠብቋል። ስጋን ከበረራዎች፣ ከመርከብ ጉዞዎች እና ከቤንዚን እና ከናፍጣ መኪኖች ጋር በማገናኘት ከግል የአመጋገብ ምርጫ ወደ የአየር ንብረት ጉዳይ ቀይረውታል።
ኢንዱስትሪውን የሚወክለው የደች የስጋ ማኅበር በውሳኔው ደስተኛ አለመሆኑን ገልጿል።
የደች የጉዞ ወኪሎች እና የአስጎብኚዎች ማህበር የአየር ጉዞን ጨምሮ በበዓላት ላይ የማስታወቂያ እገዳ መጣሉ የኩባንያዎች የንግድ ነፃነት ላይ ያልተመጣጠነ ገደብ መጣል ነው ብሏል።











