የአሜሪካው ድርጅት የተሰረቀበትን የቢራ ምርት ለጠቆሙ ሽልማት እንደሚሰጥ አስታወቀ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፓብስት የተባለ የቢራ አምራች ድርጅት በካሊፎርንያ ከሚገኝ መጋዘኑ በሺዎች የሚቆጠር ቢራ እንደተሰረቀበት አስታውቋል።

"የእኛን ቢራ በመስረቃችሁ አንፈርድባችሁም፤ ግን በተገቢው መንገድ ብትወስዱ ይሻል ነበር" ሲል ድርጅቱ ለሌቦቹ መልዕክት አስተላልፏል።

ፖሊስ እንዳለው ቢራውን የሰረቁት ሐሰተኛ ሰነድ ለመጋዘኑ አቅርበዋል። በዚህም ወደ ሳን ዲያጎ ሊወሰድ የነበረ ወደ 25,000 ዶላር የሚያወጣ ቢራ ሰርቀዋል።

ድርጅቱ የተሰረቀውን 18,144 ኪሎግራም የሚመዝን ቢራ ማስመለስን "በቀላሉ እንደማያየው" አስታውቋል።

በአንድ ቀን ውስጥ ከመጋዘኑ ሁለት ጊዜ ቢራ መሰረቁን ፖሊስ ተናግሯል። ሁለቱ ዝርፊያዎች ትስስር ያላቸው ስለመሆኑ ምርመራ ተከፍቷል።

በመጀመሪያው ዝርፊያ ወደ አሪዞና ሊጓዝ የነበረ 45,000 ዶላር የሚያወጣ ቢራ ተሰርቋል። ቢራው በሁለት ሳምንት ውስጥ የታቀደለት ቦታ ሳይደርስ ሲቀር መሰረቁ ታውቋል።

ይህ ዝርፊያ ከተፈጸመ ከአንድ ሰዓት በኋላ በሐሰተኛ ሰነድ አማካኝነት በድጋሚ ሌላ ቢራ ተሰርቋል።

"በሁለቱ ክስተቶች መካከል ተመሳሳይ ነገሮች በምርመራችን አግኝተናል" ሲል ፖሊስ አስታውቋል።

ቢራውን የጫነው ድርጅት፣ አሽከርካሪው እና የተሽከርካሪው ዓይነት ተመሳሳይነት እንዳላቸውም ተገልጿል።

የቢራ አምራች ድርጅቱ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ "ቢራውን ከመጋዘኑ መውሰድ የነበረበትን ግለሰብ በማስመሰል ቢራውን ሰርቀዋል" ብለዋል።

ዘራፊዎቹ ቢራውን ጭነው ከመጋዘኑ እንደወጡም ገልጸዋል።

ቢራ አምራቹ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባወጣው መግለጫ "ይሄንን ነገር እንደ ቀልድ አናየውም" ብሏል።

ለሌቦቹ ባስተላለፈው መልዕክትም "ምንም ጥያቄ ሳይከተል ቢራውን ለመመለስ 18 ቀናት ከ44 ዲቂቃ አላችሁ" ሲል አሳስቧል።

ቢራው የሚመለስ ከሆነ ሽልማት እንደሚሰጥም ድርጅቱ ገልጿል። የሽልማቱን መጠን ግን ይፋ አላደረገም።