ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሶማሊያዊቷ የቀድሞ ስደተኛ የዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ አባል ሆነች
ስደተኛ የነበረችው እና የሌበር ፓርቲን የወከለችው ትውልደ ሶማሊያዊቷ ሳጋል አብዲ ዋሊ በማዕከላዊ ለንደን በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሟሟያ ምርጫ አሸነፈች።
አብዲ ዋሊ ለብሪታንያ ፓርላማ የተመረጠች የመጀመሪያዋ ትውልደ ሶማሊያዊት ሆናለች።
የ42 ዓመቷ አብዲ ዋሊ፣ ቀደም ሲል በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ይያዝ የነበረውን የሆልቦርን እና ሴንት ፓንክራስ መቀመጫ አሸንፋለች።
በ1990ዎቹ ከሶማሊያ ከቤተሰቧ ጋር ወደ ብሪታንያ የመጣች ሲሆን፣ ያደገችውም በሰሜን ለንደን በሚገኘው ካምደን አካባቢ ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2026 ግንቦት ወር ላይ የካምደን ምክር ቤት መሪ በመሆን የተመረጠች ሲሆን በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት፣ የሌበር ፓርቲ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ያላትን ጠንካራ ግንኙነት አጉልቶ አሳይቷል።
ማሸነፏን ካወቀች በኋላ ባደረገችው ንግግር አብዲ-ዋሊ የቤተሰቦችን ሕይወት ለማሻሻል እንደምትሰራ ቃል በመግባት፤ "ወደ ፖለቲካ የገባሁት የመኖሪያ ቤት ችግርን ከተመለከትኩ በኋላ ነው" ብላለች።
የምክር ቤቱ መሪ ከመሆኗ በፊት በካምደምን ምክር ቤት ውስጥ የቤቶች ልማትን በኃላፊነት ትመራ ነበር።
የድምፅ ቆጠራው ከተጠናቀቀ በኋላ ባደገረችው ንግግር፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ያላትን ከፍተኛ ቁርጠኝነት የገለጸች ሲሆን፣ የሰዎችንና የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ለማሻሻል በየቀኑ እንደምትሰራ ተናግራለች።
ቀደም ሲል ስደተኛ እንደነበረች የተናገረችው ሳጋል አብዲ ዋሊ ማሸነፏ በብሪታንያ ውስጥ ከተለያዩ ማኅበረሰቦች የመጡ ሰዎች ኃላፊነት ሊይዙ እንደሚችሉ እንደሚያሳይ ተስፋ እንደምታደርግ ገልጻለች።
የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም፣ አብዲ ዋሊ ላደረገችው "ድንቅ የምርጫ ዘመቻ" እንኳን ደስ አለሽ በማለት፣ ከእርሷ ጋር አብሮ ለመስራት በጉጉት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
ለበርንሃም ሥልጣናቸውን ያስረከቡት ሰር ኪር ስታርመርም ውጤቱን በደስታ የተቀበሉ ሲሆን፣ አብዲ-ዋሊን "ለማኅበረሰባችን ብቁ እና ጠንካራ ተሟጋች እንደሆንሽ እንዲሁም ድንቅ የሕዝብ እንደራሴ እንደምትሆኚ አውቃለሁ" ብለዋል።
አብዲ ዋሊ ከተመረጠች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቢቢሲ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ፣ በለንደን ካምደን እንዲሁም በመላው ዩናይትድ ኪንግደም የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ትልቅ ችግር መሆኑን ገልጻለች። የሕዝቡን ሕይወት ለማሻሻል በየቀኑ እንደምትሰራም ተናግራለች።
"ካለው የቤት ችግር አዙሪት ለመውጣት መፍትሄው የተጨማሪ የማህበራዊ መኖሪያ ቤቶችን፣ ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውን ቤቶች እና ሌሎች የመኖሪያ ቤት ዓይነቶችን በመገንባት ብቻ ነው" ስትል ተናግራለች።
"መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ከእኔ ጋር በአንድ አቋም ላይ በመሆኑ በእጅጉ እኮራለሁ፤ እንዲሁም ከመጀመርያው ዕለት ጀምሮ በዚህ ላይ በትጋት እንደምሰራ አረጋግጣለሁ።"
አብዲ ዋሊ የቴምስ ዋተር ኩባንያን እንደገና በመንግሥት ባለቤትነት ሥር መሆን እንዳለበት አጥብቃ ትሞግታለች። ቴምስ ዋተር በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የውሃ አቅርቦት እና የፍሳሽ ማስወገጃ አገልግሎቶችን የሚሰጥ በእንግሊዝ የሚገኝ ትልቅ የውሃ አገልግሎት ኩባንያ ነው።
አብዲ-ዋሊ ኩባንያው በግል ባለቤትነት እንዲቆይ ከማድረግ ይልቅ መንግሥት ቁጥጥሩን እንዲረከብ የሚለው ሃሳብ ደጋፊ ናት። የሕዝብ ባለቤትነትን የሚደግፉ ወገኖች፣ ይህ እርምጃ ተጠያቂነትን እንደሚያሻሽል እና ውሳኔዎች ለሕዝብ ጥቅም መዋላቸውን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ይከራከራሉ።
ለወጣቶች ተጨማሪ ዕድሎችን መፍጠር ሌላው ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ገልጻለች።