ሩሲያ በዩክሬን ዋና ከተማ ከፍተኛ ባለስቲክ ሚሳዔል ጥቃት ፈጸመች
ሩሲያ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ በተፈጸመችው ተከታታይ የባለስቲክ ሚሳዔል ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል፤ ቢያንስ 14 ሰዎች መቁሰላቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ምሽቱን በተሰነዘረው ጥቃት በክልሉ የሚገኙ በርካታ ቦታዎች ተመትተዋል። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ፤ የሩሲያ በሙሉ ወረራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ “ኪዬቭ ላይ ከተፈጸሙት እጅግ ግዙፍ የባለስቲክ ጥቃቶች አንዱ” ሲሉ ገልጸውታል።
የዩክሬን ጦር በበኩሉ የአገሪቱ የአየር መከላከያ ስርዓት ከተሰነዘሩት 41 ሚሳዔሎች ውስጥ 18 ያህሉት መትቶ መጣሉን አስታውቋል። ስርዓቱ 108 ድሮኖችን መጥለፉንም ገልጿል።
በሌላ በኩል ዩክሬንም ሩሲያ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ቀጥላለች። የዩክሬን ጦር እንደሚናገረው፤ በጥቁር ባሕር የሚገኙ ሁለት የሩሲያ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በድሮን ተመትተዋል።
የሩሲያ ደቡብ ምዕራባዊ ስታቭሮፖል ክልል ገዥ በበኩላቸው፤ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በተፈጸመው የድሮን ጥቃት እሳት መነሳቱን ተናግረዋል።
የዩክሬን አየር ኃይል እንደገለጸው በመዲናዋ ኪዬቭ የተሰነዘሩት ጥቃቶች ኢስካንደር እና ሃይፐርሶኒክ ዚርኮን ሚሳዔሎች እንዲሁም 125 ድሮኖችን ጨምሮ በተለያዩ የሩሲያ የጦር መሣሪያ ሥርዓቶች የተፈጸሙ ናቸው።
በከተማዋ የሚገኙ አንድ ሱፐርማርኬት እና የተማሪዎች ማደሪያን ጨምሮ የመኖሪያ እና የመኖሪያ ያልሆኑ ሕንፃዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ከንቲባው ቪታሊ ክሊትስችኮ ተናግረዋል።
እነዚህ ጥቃቶች ተፈጸሙት፤ ዩክሬን ንብረትነታቸው በሩሲያ ትልቁ የኦንላይን መደብር የሆነው ‘ዋይልድቤሪስ’ የሆኑ ሁለት መጋዘኖች ከተመቱ በኋላ ነው። በዚህ ጥቃት ስምንት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከፍተኛ እሳትም ተነስቷል።