የኢራኑ ጠቅላይ መሪ የአገራቸውን የኒውክሌር አቅም ለመከላከል ቃል ገቡ
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ የእስላማዊ ሪፐብሊኩን የኒውክሌር እና የሚሳዔል አቅም ለመከላከል ቃል ገቡ። ሞጅታባ ኻሜኒ ሐሙስ ዕለት በጽሑፍ በሰጡት መግለጫ አሜሪካ በፐርዢያ ባሕረ ሰላጤ ቦታ እንደሌላት በመግለጽ፣ መገኘት የሚገባት “ከውሃዎቿ በታች ነው” ብለዋል።
ኻሜኒ በሰጡት መገለጫ ላይ የኢራን የኒውክሌር እና የባሌስቲክ ሚሳዔል ፕሮግራም ለንግግር እንደማይቀርብ አመልክተዋል።
በቴሌቭዥን በተነበበው የጠቅላይ መሪው መግለጫ አያቶላህ ሞጅታባ ኻሜኒ የአሜሪካን ግዙፍ ወታደራዊ ኃይል ዕቅድ አለመሳካቱን በመግለፍ በቀጣናው ታሪክ ውስጥ “አዲስ ምዕራፍ“ ተከፍቷል ብለዋል።
ሞጅታባ ኻሜኒ ኢራን ወሽመጡን መቆጣጠሯ ባሕረ ሰላጤውን የበለጠ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል። መግለጫው አክሎም ቴህራን በወሽመጡ ላይ የሚኖራት “ሕጋዊ አመራር እና አዲስ አስተዳደር” የቀጣናውን ዜጎች በሙሉ ተጠቃሚ ያደርጋል ሲል ገልጿል
ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸውን መገደል ተከትሎ የጠቅላይ መሪነቱን ሥልጣን ከተረከቡ ጀምሮ ለሕዝብ ታይተው አያውቁም።
ጠቅላይ መሪው መግለጫውን የሰጡት የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ የሚደርሰው ጫና በበረታበት፣ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ቴህራን ወደቦች የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች ላይ የጣለው እገዳ በቀጠለበት ወቅት ነው።
ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን ተከትሎ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ አሻቅቧል። ሐሙስ ዕለት የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋ በበርሜል 126 ዶላር ተሸጧል።
ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ወደቦች ላይ የጣሉትን እገዳ እንደሚቀጥሉ የገለጹ ሲሆን አጋሮቻቸው ጥምረት በመፍጠር የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲያስከፍቱ ግፊት እያደረጉ ነው ተብሏል።
ኻሜኒ በመግለጫቸው ላይ አሜሪካን “ታላቋ ሴጣን” በማለት የጠሯት ሲሆን በፐርዢያ ባህረ ሰላጤ ምንም ጉዳይ የላትም ብለዋል።
የኢራን የበላይ መሪ "መሣሪያዎቻችን እና ቴክኖሎጂዎቻችን እንደ አገር የማንነታችን አካል ናቸው እና ምንም ቢሆን እንጠብቃቸዋለን" ሲሉ ተናግረዋል።
“ሁሉም የኢራን አቅሞች ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፣ ኢንዱስትሪ፣ የኒውክሌር እና ሚሳዔል ፕሮግራሞች” በ90 ሚሊዮን የኢራን ሕዝብ የሚታዩት እንደ ውድ ብሔራዊ ሃብቶች መሆኑን ጠቅላይ መሪው ተናግረዋል።
አክለውም “ልክ ውሃችንን፣ ግዛታችንን እና አየር ክልላችንን እንደምንከላከለው እንጠብቀዋለን” ብለዋል።
በሺህ ኪሎ ሜትሮች አቋርጠው መጥተዋል ያሏቸውን የውጭ ኃይሎች “በስግብግብነት እና በክፋት” ይንቀሳቀሳሉ ሲሉ ወንጅለው፣ በአካባቢው “ምንም ቦታ የላቸውም። ከውሃው በታች ካልሆነ በስተቀር" ብለዋል።
ኻሜኒ በዚህ መግለጫቸው ላይ ኢራን ወሽመጡን መቆጣጠሯን እንደምትቀጥል አመልክተዋል።
ኢራን በወሽመጡ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን 2 ሚሊዮን ዶላር እንደምታስከፍል ትናግራለች።
እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በቴህራን ላይ የጀመሩት ጦርነት ሁለት ወር አልፎታል።