ቀጥታ, በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተደረሰው የአስር ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መሆን ጀመረ

በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተደረሰው የአስር ቀን የተኩስ አቁም ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለአስር ቀን ብቻ የተደረሰ ቢሆንም ሊራዘም እንደሚችል ጠቁመዋል። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሊባኖስ ጋር “ታሪካዊ የሰላም ስምምነት” ዕድልን ይፈጥራል ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ የኢራን ጦርን “በጣም በቅርቡ ማብቃት አለበት” አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኔቫዳ ለተሰበሰቡ ሰዎች የኢራን ጦርነት “በቅርቡ ማብቃት አለበት” ሲሉ ተናገሩ።

    ትራምፕ “በኢራን የሚካሄደው ጦርነት ያለምንም እንከን እየተካሄደ ነው” ካሉ በኋላ “በቅርቡ መጠናቀቅ አለበት” ብለዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ባያብራሩም የአሜሪካ ጦር ሮኬቶችን መትቶ ሲጥል ግን ብቃት እንዳለው ተናግረዋል።

    ባለፈው ሳምነት መጨረሻ ላይ በፓኪስታን ኢዝላማባድ የተካሄደው የሰላም ድርድር ያለምንም ውጤት ተበትኗል።

    ዋሺንግተን በሁለቱ አገራት መካከል ቀጣይ ድርድር ለማድረግ ንግግሮች መኖራቸውን ቢገልጽም መቼ እና የት ይካሄዳል የሚለውን ግን ይፋ ማድረግ አልፈለገም።

  2. በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተደረሰው የአስር ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መሆን ጀመረ

    በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተደረሰው የአስር ቀን የተኩስ አቁም ከእኩለ ለሊ ት ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለአስር ቀን ብቻ የተደረሰ ቢሆንም ሊራዘም እንደሚችል ጠቁመዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሊባኖስ ጋር “ታሪካዊ የሰላም ስምምነት” ዕድልን ይፈጥራል ብለዋል።

    በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ የተኩስ አቁሙን እንደሚያከብር ጠቅሶ በኋላ ላይ “በሁሉም የሊባኖስ ግዛቶች የተሟላ ጥቃቶችን ማቆም” እንዲያካትት እና “የእስራኤል ጦር በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ” ጠይቋል።

    ኔታንያሁ ጦራቸው በደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ 10 ኪሜ ያሀል ዘልቆ በመግባት “የደህንነት ቀጣና” ውስጥ እንደሚቆዩ የተናገሩ ሲሆን ይህ ግን ከሄዝቦላህ ፍላጎት ውጭ ነው።

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በስምምነቱ መሠረት የሊባኖስ መንግሥት ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ ጥቃት እንዳይፈጽም ለማድረግ “ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ” ይኖርበታል ብሏል።

    አክሎም የሊባኖስ የጸጥታ ኃይል ለሊባኖስ ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ መከላከያ “ሙሉ ኃላፊነት” እንዳለበት አስታውቋል።

    የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆን እንደጀመረ የእስራኤል መከላከያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ ከ380 በላይ የሄዝቦላህ ዒላማዎችን መደብደቡን ገልጿል።

    ዒላማ ከሆኑት መካከል የሮኬት ማስወንጨፊያዎች፣ ዋና መስሪያ ቤቱን እና የሄዝቦላህ አባላት ይገኙበታል።

    ትራምፕ የሊባኖስ እና የእስራኤል መሪዎች በዋሺንግተን ተገናኝተው በቀጣይ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ መጋበዛቸውን ተናግረዋል። እስካሁን ግን ከየትኛውም ወገን ስለግብዣው ማረጋገጫ አልተገኘም።

    ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ዛሬ ለሊባኖስ “ታሪካዊ” ቀን ነው ሲሉ ጽፈዋል።

    “መልካም ነገሮች እየሆኑ ነው” ያሉት ትራምፕ በሌላ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው “ሄዝቦላህ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ተገቢውን እና የተረጋጋ ባህሪውን እንደሚያሳይ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

  3. ትራምፕ በሰዓታት ውስጥ እስራኤል እና ሊባኖስ የ10 ቀን የተኩስ አቁም እንደሚጀምሩ ተናገሩ

    ዶናልድ ትራምፕ የሊባኖሱን ፕሬዚዳንት እና የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ማነጋገራቸውን እና የተኩስ አቁም በጥቂት ሰዓት ውስጥ እንደሚጀመር ተናገሩ።

    ትራምፕ በመግለጫቸው ላይ በኢራን የሚደገፈውን እና ከእስራኤል ጋር ውጊያ እያካሄደ ያለውን ሄዝቦላህን አልጠቀሱም።

    “ከሊባኖሱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን እና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢቢ ኔታንያሁ ጋር ጥሩ ውይይት አድርጌያለሁ” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    “እነዚህ ሁለቱ መሪዎች በአገራቸው መካከል ሰላም ማስፈን እንዲቻል የ10 ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ከ7:00 (ሌሊት) ጀምሮ ይጀምራሉ።”

    የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም ከእስራኤል ጋር የተደረሰውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም መቀበላቸውን አስታውቀዋል።

    ማክሰኞ ዕለት ከ34 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የሁለቱ አገራት ልዑካን በዋሺንግተን መገናኘታቸውን ያስታወሱት ትራምፕ ኃላፊዎቻቸውን “ዘላቂ ሰላም” ማምጣት እንዲቻል ከእስራኤል እና ሊባኖስ ጋር እንዲሰሩ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።

    "ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ፣ የፔንታጎን የጋራ ወታደራዊ አዛዦች ሊቀ መንበር የሆኑት ጄነራል ዳን ራዚን ኬን፣ ከእስራኤል እና ሊባኖስ ጋር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እንዲሰሩ መመሪያ ሰጥቻለሁ።”

    “በመላው ዓለም ዘጠኝ ጦርነቶችን መፍታት በመቻሌ ክብር ይሰማኛል እና ይህ ደግሞ 10ኛው ይሆናል” ሲሉ በመልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን እና የሊባኖስን ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን በዋይት ሐውስ ለተጨማሪ ንግግር መጋበዛቸውን አስታውቀዋል።

    “ሁለቱም ወገኖች ሰላም ይፈልጋሉ እና በፍጥነት ይሆናል" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።

    የሁለቱ አገራት መሪዎች ግብዣውን ስለመቀበላቸው የታወቀ ነገር የለም።

  4. የአሜሪካ እና የሊባኖስ ፕሬዚዳንቶች በስልክ ተወያዩ -ቤይሩት

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን ዛሬ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በስልክ መወያየታቸውን ጽህፈት ቤታቸው ገለጸ።

    ጽህፈት ቤቱ በኤክስ ገጹ ላይ ኦውን ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እንዲሁም “ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን ለማረጋገጥ” ስለሚያደርጉት ጥረት አመስግነዋል ብሏል።

    አውን በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል “በተቻለ ፍጥነት በቀረበ ጊዜ” የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ በድጋሚ ጠይቀዋል።

    ትራምፕ ለፕሬዚዳንት ኦውን እና ሊባኖስ ያላቸውን ድጋፍ መግለጻቸውን ጽህፈት ቤቱ አክሎ ገልጿል።

    ዛሬ የሊባኖሱ ፕሬዚዳንት እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ይወያያሉ ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ይህ ግን መሰረዙን ቢቢሲ ከሊባኖስ ባለሥልጣናት ምንጮቹ አረጋግጧል።

    እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባ ቀጥላለች።

    አንድ ከፍተኛ የሊባኖስ ባለሥልጣን የእስራኤል የአየር ድብደባ ደቡባዊ ሊባኖስን ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል የሚያገናኝ ቁልፍ ድልድይን ማውደሙን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

  5. የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ኢራን ላይ 'ከዚህም በላይ የከፉ' ጥቃቶች እንደሚፈጸም ዛቱ

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እዝራኤል ካትዝ ኢራን ከአሜሪካ ጋር የጀመረችው ድርድር ላይ ከስምምነት የማትደርስ ከሆነ ‘ከዚህም በላይ የከፋ’ ጥቃት ሊሰነዝሩ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ።

    “ኢራን ታሪካዊ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች። ይህ ወደ ወደፊቱ ድልድይ እና ወደ መገለል እና ውድመት ምርጫ የሚያደርጉበት ቅጽበት ነው።”

    ኢራን መነጠል እና ውድመትን የምትመርጥ ከሆነ እስራኤል እስካሁን ያልደበደበቻቸውን ዒላማዎች “በጣም በፍጥነት በመለየት” “እስካሁን ከተፈጸሙት የከፋ” ጥቃት እንደሚፈጽሙ ዝተዋል።

    “ምርጫው በእጃቸው ነው እና ውጤቱም የራሳቸው ነው” ሲሉ አስተያያታቸውን አጠናቅቀዋል።

    ቀደም ሲል የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ኢራን ከስምምነት ላይ የማትደርስ ከሆነ ጦራቸው ጥቃቱን ዳግም ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን በመናገር “በብልሃት እንድትመርጥ” አስጠንቅቀው ነበር።

  6. የሊባኖሱ ፕሬዚዳንት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር እንደማይነጋገሩ ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስተር እና የሊባኖሱ ፕሬዚዳንት መካከል ዛሬ ምንም ዓይነት ንግግር እንደማይኖር የሊባኖስ ባለሥልጣናት ምንጮች ለቢቢሲ ገለፁ።

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዩ ዛሬ መነጋገር እንደማይችሉ ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።

    የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ሊደረግ የነበረው ንግግር መሰረዙን የሚገልጽ መግለጫ ማውጣት አለመፈለጉን ቢቢሲ ከምንጮቸ ሰምቷል።

    ፕሬዚዳንት አውን ከሄዝቦላህ እና ከአብዛኛው የሊባኖስ ሕዝብ ጋር ያላቸው ግንኙነት እስራኤል ጥቃት መቀጠሉን ተከትሎ ደፍርሷል።

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ንግግር እንዲደረግ የሚፈልጉ ሲሆን የተኩስ አቁም ግን ቁልፍ መሆኑን ተናግረዋል።

    እስራኤል በበኩሏ የወታደራዊ ዘመቻዋን ለማቋረጥ ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች።

    ዶናልድ ትራምፕ የሊባኖሱ ፕሬዚዳነት ጆሴፍ ኦውን እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ዛሬ እንደሚነጋገሩ ገልጸው ነበር’

    ይህንን የትራምፕ ሃሳብ የእስራል ሚኒስትርም አረጋግጠውት ነበር።

  7. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለጦርነት የሚያወጡ 'አምባገነኖች'ን ተቹ

    ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዛሬ በካሜሩን ባደረጉት ንግግር በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለጦርነት የሚያወጡ መሪዎችን ባልተለመደ ሁኔታ በግልጽ ተችተዋል።

    ይህ የሆነው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያላይ እንደገና ከተቿቸው በኋላ ነው።

    ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በካሜሮን ባሜንዳ ባደረጉት ንግግር፣ “ለራሳቸው ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም ሲሉ ሃይማኖትንና የእግዚአብሔርን ስም የሚጠቀሙ” ሰዎችን አውግዘዋል።

    ጳጳሱ ይህ ዓመፅን ለማጽደቅ እምነትን መጠቀም መሆኑን በመጥቀስ አስጠንቅቀዋል።

    ለአስር ዓመታት ያህል በዘለቀው ግጭት ለተጎዳው የአካበቢው ማኅበረሰብ ባደረጉት ንግግር “ሰላምን ለማወጅ” ብመጣም ነገር ግን የአካባቢው ነዋሪዎች “ለእኔም ሆነ ለመላው ዓለም ሰላምን እያወጁ” እንደሆነ ተረድቻለሁ ብለዋል።

    ሊዮ ጦርነት የሰው ልጅ እንደሚቀጥፍ ሲያስረዱ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ዓለም አቀፍ አለመመጣጠን መኖሩን በመግለጽ ተችተዋል።

    “የጦርነት ጌቶች ለማውደም የሚፈጀው ቅጽበት እንደሆነ የማያውቁ ለመምሰል ይሞክራሉ፤ ነገር ግን መልሶ ለመገንባት የሕይወት ዘመን በቂ አይደለም” ብለዋል።

    አክለውም “በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለግድያና ለውድመት ይውላል፤ ነገር ግን ለፈውስ፣ ለትምህርትና ለማደስ የሚያስፈልጉ ሀብቶች የትም አይገኙም” ብለዋል።

    ሊቀ ጳጳሱ የጦርነት ጌቶች ሲሉ የጠሯቸውን “ወሳኝ የሆነ የተግባር ለውጥ” እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው ወደ “ሰብአዊ ወንድማማችነት የበለፀገ እና ዘላቂ መንገድ” እንዲሸጋገሩ አሳስበዋል።

    “ዓለም በጥቂት አምባገነኖች እየተናጠች” እያለ “በብዙ አቃፊ እና ደጋፊ ወንድሞችና እህቶች ተይዛ ትገኛለች” በማለት ተስፋን ፈንጥቀዋል።

  8. የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ኢራን የማትስማማ ከሆነ ዳግም ጥቃት እንደሚጀመር አስጠነቀቁ

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ኢራን ከስምምነት ላይ የማትደርስ ከሆነ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የማጥቃት ዘመቻ ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ “በብልሃት እንድትመርጥ” አስጠነቀቁ።

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት እና የፔንታጎን የጋራ ወታደራዊ አዛዦች ሊቀ መንበር የሆኑት ጄነራል ዳን ኬን እንዲሁም የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ አድሚራል ብራድ ኩፐር ዛሬ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

    ሄግሴት ኢራን ከአሜሪካ ጋር በሚኖራት ድርድር “በብልሃት እንድትመርጥ” አስጠንቅቀዋል። ሚኒስትሩ ጦሩ ማንኛውንም ትዕዛዝ መሣሪያውን “አቀባብሎ” እና “ለመሄድ ዝግጁ ሆኖ" እየጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።

    ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት እንደምታረጋግጥ የገለጹት ሄግሴት ይህም “በጥሩ መንገድ” ወይም “በከባድ ሁኔታ” እንደሚከናወን ተናግረዋል።

    ሚኒስትሩ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጣሉትን እገዳ የአሜሪካ ጦር “ከ10 በመቶ ባነሰ አቅሙ” ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

    አክለውም ኢራን የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ለመፈጸም መዛቷን ጠቅሰው ይህ ቁጥጥር ሳይሆን “የባህር ላይ ውንብድና” ነው ብለዋል።

    ጄነራል ኬን ሚኒስትሩ ያሉትን አጠናክረው የአሜሪካ ጦር የማጥቃት ዘመቻውን ለመቀጠል “በቅጽበቶች ትዕዛዝ” ውስጥ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

    አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በጣለችው የእንቅስቃሴ ገደብ እስካሁን ድረስ 13 መርከቦች እንዲመለሱ ሲነገራቸው በመመለስ “ብልህ ውሳኔ” መወሰናቸውን ተናግረዋል።

    አሜሪካ ተጨማሪ የባሕር ኃይል መርከቦችን ማሰማራት እንደማያስፈልጋት ጠቅሰዋል።

    አድሚራል ኩፐር በበኩላቸው አሜሪካ የተኩስ አቁም ጊዜውን ስልቶቿን እና ብልሃቶቿን ለማስተካከል እየተጠቀመችበት መሆኑን ተናግረው ከእስራኤል የተሻለ ወዳጅ በቀጠናው ላይ የለም ብለዋል።

  9. በአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ውስጥ ቀጥሎ ምን ሊከሰት ይችላል?

    የፓኪስታን ልዑካን ቴህራን ሲገቡ አሜሪካ ከኢራን ጋር ለሁለተኛ ዙር ድርድር ለመቀመጥ እየተነጋገረች መሆኑ ተሰምቷል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት ለ40 ቀናት ከተካሄደ በኋላ የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሷል።

    ነገር ግን ባለፈው ሳምነት መጨረሻ ላይ በፓኪስታን ለሃያ ሰዓታት ያህል የተደረገው ውይይት ያለ ምንም ስምምነት ተቋጭቷል።

    መጀመርያው ዙር ንግግር ያለምንም ስምምነት መጠናቀቁን እንዴት ልናየው እንችላለን? ቀጣይ ዙር ንግግርስ ፍሬ ያፈራ ይሆን? አሜሪካ እና ኢራን የተጠና እና የተመጠነ ግጭት ውስጥ ይቆያሉ ወይስ መከላከል ወደማይቻል ሰፊ ጦርነት ያመራሉ?

    ቀጣዮቹ አራትን ቢሆኖች በመጪው ጊዜ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ያመለክታሉ።

  10. የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ “በሊባኖስ የሚኖር የተኩስ አቁም በኢራን ካለው እኩል አስፈላጊ ነው” አሉ

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን አፈ ጉባዔ ሞሐማድ ባጋር ጋሊባፍ ከሊባኖስ አቻቸው ናቢህ ቤሪ ጋር በስልክ በተወያዩበት ወቅት “በሊባኖስ የሚኖር የተኩስ አቁም” በቴህራን ካለ “የተኩስ አቁም እኩል” አስፈላጊ ነው ማለታቸውን ዘገቡ።

    ጋሊባፍ አክለውም “በኢዝላማባድ በነበረ ድርድር [ከአሜሪካ ጋር] እና ከዚያም በኋላ” ኢራን “ጠላቶቿ ቋሚ የተኩስ አቁም ላይ እንዲስማሙ ጫና ስታደርግ" እንደነበር ተናግረዋል።

    ጋሊባፍ ዛሬ ከፓኪስታን መከላከያ አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ጋር መገናኘታቸውን መገናኛ ብዙኃኑ ዘግበዋል።

    የፓኪስታን ልዑክ ወደ ቴህራን የሄደው ኢራን እና ዩኤስ መካከል ስለተደረሰው የተኩስ አቁም ለመነጋገር እንደሆነ ተገልጿል።

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ጋሊባፍ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ቁልፍ የፖለቲካ ሰው ሆነው ወጥተዋል።

    በኢዝላማባድ የተደረገው ውይይት ላይ የተገኘውን ልዑክ የመሩት ጋሊባፍ ናቸው።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ትናንት በዋሺንግተን እና ቴህራን መካከል በአሸማጋይዋ ፓኪስታን በኩል የሚደረጉ የመልዕክት ልውውጦች “እንደቀጠሉ" መሆናቸውን ተናግረዋል።

    ነገር ግን የተኩስ አቁሙ ሊራዘም ስለመቻሉ ያሉት ነገር የለም።

  11. እስራኤል ደቡባዊ ሊባኖስን ከቀሪው አገሪቱ ክፍል ጋር የሚያገናኝ ድልድይን አወደመች

    አንድ ከፍተኛ የሊባኖስ ባለሥልጣን የእስራኤል የአየር ድብደባ ደቡባዊ ሊባኖስን ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል የሚያገናኝ ቁልፍ ድልድይን ማውደሙን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናገሩ።

    የሊባኖስ ብሔራዊ የዜና ወኪል በበኩሉ ታየርን ከሲዶን ጋር የሚያገናኘው ቃስሚዬህ ድልድይ በተፈጸመበት ሁለት ተከታታይ ጥቃት መውደሙን ዘግቧል።

    እስራኤል ቀደም ሲል ሄዝቦላህ የአገሪቱን መሠረተ ልማቶች እንዳይጠቀም ለማድረግ ድልድዮችን ዒላማ አድርጋ ጥቃት እንደምትፈጽም ገልጻ ነበር።

    ጥቃቶቹ እየተፈጸሙ ያሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ኦውን ጋር ዛሬ እንደሚነጋገሩ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት ነው።

    የእስራኤል ጦር 40 ሺህ ያህል ሰዎች እንደሚኖሩበት በሚገመተው ናባቴህ ከተማ እንዲሁ የአየር ድብደባ መፈጸሙ ተገልጿል።

  12. የእስራኤል እና ሊባኖስ ንግግር ምን ያህል ትርጉም ያለው ነው?

    የእስራኤል እና ሊባኖስ መሪዎች ሊነጋገሩ ነው የሚለው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የማኅበራዊ ትስስር ገፅ ልጥፍ ረቡዕ ምሽት የወጣው ዘርዘር ያለ መረጃ ሳያካተት ነበር።

    በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እና በሊባኖሱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን በስልክ ቢነጋገሩ እንኳ ትልቅ እና ታሪካዊ ትርጉም ይኖረዋል።

    እስራኤል እንደ አገር እ.አ.አ በ1948 ከተመሰረተች ወዲህ ከሊባኖስ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ኖሯት አያውቅም።

    አገራቱ ጠላት ሆነው ቆይተዋል። አሜሪካ በዋሽንግተን መቀመጫቸውን ያደረጉ የሁለቱ አገራት አምባሳደሮች በዚህ ሳምንት እንዲነጋገሩ ከማድረጓ በፊት፤ አገራቱ ለመጨረሻ ጊዜ የቀጥታ ለውይይት የተቀመጡት በአውሮፓውያኑ 1993 ነው።

    ከስድስት ሳምታት አውዳሚ ጦርነት በኋላ የሊባኖስ መንግሥት በእስራኤል እና በኢራን በሚደገፈው ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ እየጠየቀ ነው። አገራቱ ከዚህ ጉዳይ ውጭ ከፍተኛ ደረጃ ንግግር ለማድረግ መስማማታቸው አጠራጣሪ ነው።

    እስራኤል የረጅም ጊዜ ግቧ ከሊባኖስ ጋር የሰላም ስምምነት ማድረግ መሆኑን ተናግራለች።

    ይሁን እንጂ ሄዝቦላህ ትጥቁን ሳይፈታ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይደረግ ደጋግማ ገልፃለች።

    የእስራኤል መሪዎች የአገራቸው ዜጎችን ከሄዝቦላህ ጥቃቶች ለመጠበቅ “ነፃ ቀጣና” የሚሉትን ከባቢ ለመፍጠር ወታደራዊ ወረራው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

    በእስራኤል ድንበር አካባቢ የሚገኙ የሊባኖሳውያን መንደሮችን ያወደሙ ሲሆን የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እንዲመለሱ እንደማይፈቅዱም ገልጸዋል። እስራኤል ከፈተችው ዘመቻ የተፈናቀሉ ሊባኖሳውያን ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን ተሻግሯል።

    ምንም እንኳ እስራኤል የሊባኖሱን ጦርነት ከኢራን ጦርነት ለይታ ብታይም፤ ቴህራን ግን በቀጣናው በሚደረግ የሰላም ስምምነት ሊባኖስም እንዲያካተት ጫና እያደረገች ነው።

    ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ባለፉት ቀናት አሜሪካ፤ እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር የምታደርገውን ጠንካራ ውጊያ እንድታቆም የምታደርገው ጫና ጨምሯል።

  13. ኢራን በኦማን በኩል ባለው የሆርሙዝ ክፍል መርከቦች ያለ ጥቃት እንዲያልፉ የሚፈቅድ እቅድ ማቅረቧ ተዘገበ

    ኢራን፤ ሆርሙዝን በምትጎራበታት ኦማን በኩል ባለው የወሽመጡ ክፍል የሚጓዙ መርከቦች ጥቃት ሳይፈጸምባቸው የሚያልፉበትን መንገድ ልታጤን እንደምትችል የሚገልጽ እቅድ ለአሜሪካ ማቅረቧን ሮይተርስ ዘገበ።

    አሜሪካ እና እስራኤል የከፈቱት ጦርነት ዋነኛ አጀንዳ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ በኢራን የተዘጋው የሆርሙዝ ወሽመጥ ነው። ከዓለም የነዳጅ አቅርቦት 20 በመቶው የሚተላለፍበት ይህ መስመር መዘጋቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር እና አቅርቦቱ እንዲስተጓጎል አድርጓል።

    ወሽመጡ በመዘጋቱ የተነሳ በመቶዎች የሚቆጠሩ መርከቦች እና ከ20 ሺህ በላይ ባሕርተኞች ካሉበት መንቀሳቀስ አልቻሉም።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሆርሙዝን እንዲያስከፍቱ የሚደርስባቸው ጫና የበረታ ሲሆን ያለ ስምምነት በተበተነው የባለፈው ሳምንት የዋሽንግተን እና ቴህራን ድርድር አንዱ አንኳር ነጥብም ይህ ወሽመጥ ነበር።

    አሜሪካ እና ኢራን ሌላ ዙር ድርድር ሊያካሂዱ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ዘገባዎች እየወጡ ነው። ኢራን የስምምነት እቅድ እንዳቀረበች የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጭ ጠቅሶ ዘግቧል።

    በኦማን ውሃ ላይ የሚያልፉ መርከቦች ከኢራን በኩል ምንም አይነት መስተጓጎል ሳይገጥማቸው እንዲጓዙ ፈቃደኛ ልትሆን እንደምትችል መግለጿን ምንጩ ተናግረዋል ተብሏል።

    ኢራን በወሳኙ መተላለፊያ ላይ ያጠመደቻቸውን ፈንጂዎች ለማስወገድ ስለመስማማቷ እንዲሁም ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦችም ጭምር እንዲያልፉ ትፈቅድ እንደሆነ ግን አልተገለጸም።

    እንደ ምንጩ ገለጻ፤ ኢራን ይህንን እቅዷን ተግባራዊ የሚታደርገው ያቀረበቻቸው ጥያቄዎች ከአሜሪካ ምላሽ የሚያገኙ ከሆነ ነው።

    34 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኘው በኢራን እና ኦማን መካከል ነው። የፋርስ ባሕረ ሰላጤን ከህንድ ውቅያኖስ ጋር የሚያገናኘው ይህ መስመር፤ ከመካለኛው ምሥራቅ የሚነሱ የኤነርጂ ምርቶች እንዲሁም እንደ ማዳበሪያ ያሉ ወሳኝ ሸቀጦችን ለማጓጓዝ ያገለግላል።

  14. የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ከሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጋር ሊገናኙ መሆኑ ተገለጸ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ከሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን ጋር ዛሬ እንደሚገናኙ የእስራኤል የደኅንነት ምክር ቤት አባል ተናገሩ።

    ይህ የተባለው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው የእስራኤል እና ሊባኖስ መሪዎች ሐሙስ እንደሚገናኙ ካሳወቁ በኋላ ነው።

    ትራምፕ ረቡዕ ምሽት በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው በለጠፉት ጽሑፍ መሪዎቹ ከአስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ “ነገ [ሐሙስ]” ይነጋገራሉ ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ “በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል ትንሽ እስትንፋስ እንዲኖር እየመከርኩ ነው። የሁለቱ አገራት መሪዎች ከተነጋገሩ በጣም ረጅም ጊዜ ሆኗል፤ 34 ዓመት ገደማ። ነገ [ሐሙስ] ይካሄዳል” ብለዋል።

    ይህ የፕሬዝዳንቱ መግለጫ እስራኤል እና ሊባኖስ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋሽንግተን ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ካደረጉ ከቀናት በኋላ የተሰጠ ነው።

    ፕሬዝዳንቱ ይህን ቢሉም ሊባኖስ ይደረጋል በተባለው ንግግር ላይ የምታውቀው ነገር እንደሌለ ጠቁማለች።

    በሊባኖስ ፕሬዝዳንታዊ ፅሕፈት ቤት የሚሰሩ አንድ ባለሥልጣን አገራቸው ከእስራኤል ጋር ሊደረግ ነው ስለተባለው ንግግር አታውቅም ሲሉ ንግግሩ ላይ ያለውን ጥርጣሬ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

    የሁለቱ አገራት ታሪካዊ ንግግር በእስራኤል እና በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላህ መካከል ያለውን ጦርነት ለማስቆም ያለመ ነው።

    አሁን የእስራኤል የካቢኔ አባል ለአገሪቱ ጦር ራዲዮ የመሪዎቹን ግንኙነት ማሳወቃቸውን ተከትሎ ንግግሩ ሊካሄድ የመቻል እድሉ ጨምሮ ታይቷል።

    ኢራን በበኩሏ ከዋሽንግተን ጋር የተደረሰው የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ሊባኖስንም እንዲያካትት የማድረግ ጉዳይን አሜሪካ ማስከበር እንዳለባት ተናግራለች።

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ባገር ጋሊባፍ በኤክስ ገፃቸው ባወጡት መግለጫ “በሊባኖስ የተጠናከረ የተኩስ አቁም” መሟላት የሄዝቦላህን “ፅኑ ትግል” ረገብ ያደርገዋል ብለዋል።

    ኢራን ‘አክሲስ ኦፍ ሪዝስታንስ’ በሚል የምትጠራው እና ሄዝቦላህ አባል የሆነበት ተገዳዳሪ ኃይል “በጦርነትም በተኩስ አቁምም አንድ ነፍስ” ናቸው ብለዋል።

  15. አሜሪካ 10 መርከቦችን ወደ ኢራን መመለሷን አስታወቀች

    የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ ወሽመጥ ወደ ኢራን በሚገቡ እና በሚወጡ መርከቦች ላይ የጣለው እግድ ሠኞ ዕለት ገቢራዊ ከሆነ በኋላ አንድም መርከብ እግዱን እንዳለለፈ ገለፀ።

    ጦሩ መርከቦችን እንደሚይዝ ወይም ወደ ኢራን ወደቦች ለመግባት እና ለመውጣት የሚሞክሩትን እንደሚመለስ ገልጿል።

    በወሽመጡ አልፈው ወደሌላ አገራት ወደቦች የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች ማለፍ እንደሚፈቀድላቸውም ጠቁሟል።

    ትናንት ረቡዕ ምሽት የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በሰጠው መረጃ “10 መርከቦች ወደመጡበት እንዲመለሱ ተደርጓል። እግዱ ተፈፃሚ ከሆነበት ሠኞ ወዲም ምንም መርከብ ሰብሮ አላለፈውም” ብሏል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ከሚያልፉ መርከቦች ላይ ትሰበስበው የነበረውን ቀረጥ በማስቀረት እንዲሁም የነዳጅ ሽያጯን በማስተጓጎል ጫና እንደሚያሳድሩ ተስፋ አላቸው።

    ኢራን እገዳውን “የባሕር ላይ ውንብድና” ያለችው ሲሆን፤ በባሕረ ሰላጤው፣ በኦማን ሰርጥ እና በቀይ ባሕር የአፃፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።

  16. ትራምፕ የእስራኤል እና ሊባኖስ መሪዎች ዛሬ እንደሚነጋገሩ ቢያሳውቁም፤ የቤይሩት ባለሥልጣን አገራቸው ጉዳዩን እንደማታወቅ ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የእስራኤል እና ሊባኖስ መሪዎች ከአስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ሐሙስ እንደሚነጋገሩ ገለፁ።

    ትራምፕ ረቡዕ ምሽት በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው በለጠፉት ጽሑፍ መሪዎቹ “ነገ [ሐሙስ]” ይነጋገራሉ ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ይህን ቢሉም ሊባኖስ ይደረጋል በተባለው ንግግር ላይ የምታውቀው ነገር እንደሌለ ጠቁማለች።

    በሊባኖስ ፕሬዝዳንታዊ ፅሕፈት ቤት የሚሰሩ አንድ ባለሥልጣን አገራቸው ከእስራኤል ጋር ሊደረግ ነው ስለተባለው ንግግር አታውቅም ሲሉ ንግግሩ ላይ ያለውን ጥርጣሬ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

    ትራምፕ “በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል ትንሽ እስትንፋስ እንዲኖር እየመከርኩ ነው። የሁለቱ አገራት መሪዎች ከተነጋገሩ በጣም ረጅም ጊዜ ሆኗል፤ 34 ዓመት ገደማ። ነገ [ሐሙስ] ይካሄዳል” ብለዋል።

    ይህ የፕሬዝዳንቱ መግለጫ እስራኤል እና ሊባኖስ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋሽንግተን ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ካደረጉ ከቀናት በኋላ የተሰጠ ነው።

    የሁለቱ አገራት ታሪካዊ ንግግር በእስራኤል እና በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላህ መካከል ያለውን ጦርነት ለማስቆም ያለመ ነው።

    ኢራን በበኩሏ ከዋሽንግተን ጋር የተደረሰው የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ሊባኖስንም እንዲያካትት የማድረግ ጉዳይን አሜሪካ ማስከበር እንዳለባት ተናግራለች።

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ባገር ጋሊባፍ በኤክስ ገፃቸው ባወጡት መግለጫ “በሊባኖስ የተጠናከረ የተኩስ አቁም” መሟላት የሄዝቦላህን “ፅኑ ትግል” ረገብ ያደርገዋል ብለዋል።

    ኢራን ‘አክሲስ ኦፍ ሪዝስታንስ’ በሚል የምትጠራው እና ሄዝቦላህ አባል የሆነበት ተገዳዳሪ ኃይል “በጦርነትም በተኩስ አቁምም አንድ ነፍስ” ናቸው ብለዋል።

  17. ዋሽንግተን የቴህራን ወደቦች ላይ የጣለችው እግድ ሲፀና፤ የአሜሪካ-ኢራን ንግግር "እየቀጠለ ነው"

    አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች በሚገቡ እና በሚወጡ ሁሉም መርከቦች ላይ የጣለችው እግድ በፀናበት ወቅት ዋይት ሐውስ አሜሪካ ከኢራን ጋር “ውጤታማ እና ቀጣይነት ያለው” ንግግር እያደረገች መሆኑን ገለፀ።

    በ24 ሰዓታት ውስጥ የተከሰቱ አዲስ ሁነቶች፡

    የአሜሪካ-ኢራን ንግግር

    • አሜሪካ የሁለት ሳምንቱ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲራዘም በይፋ ጠይቃለች መባሉን ዋይት ሐውስ አስተባብሏል።
    • ፕሬስ ሴክሬታሪያት ካሮሊን ሌቪት አሜሪካ ስምምነት ሊደረስ እንደሚችል ባለው ተስፋ “ጥሩ ስሜት” እንደሚሰማት ተናግረዋል። ሆኖም ቀጣዩ ዙር ንግግር መቼ ሊደረግ እንደሚችል ቀን አለመቆረጡን ገልፀዋል።
    • ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካ እና ኢራን ንግግር አሸማጋይ የሆነው የፓኪስታን ልዑክ ከኢራን መንግሥት ጋር ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ቴህራን ገብቷል።

    የአሜሪካ እግድ

    • አሜሪካ ወደ ኢራን ወደብ የሚገቡ እና የሚወጡ ማንኛውም መርከቦች ላይ የጣለችው እግድ እንደፀና ነው። ዋይት ሐውስ እግዱ “ሙሉ ለሙሉ እየተተገበረ ነው” ያለ ሲሆን፤ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚፀና ግን አልጠቀሰም።
    • የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እግዱ ከተጣለ በኋላ አንድም መርከብ እንዳልገባ እና እንዳልጣ የገለፀ ሲሆን፤ 10 መርከቦች እንዲመለሱ ከተናገራቸው በኋላ ትዕዛዙን አክብረው ወደ ኢራን መመለሳቸውን አስታውቋል።
    • ቢቢሲ ቨርፋይ በቀጣናው በርካታ መርከቦች አድራሻቸውን በመደበቅ መረጃቸውን እያጠፉ መሆኑን ለይቷል።

    እስራኤል-ሄዝቦላህ ግጭት

    • በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል በሊባኖስ ግጭቶች ቀጥለዋል። የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) በደቡባዊ ሊባኖስ ከቲታኒያ ወንዝ በታች ያለውን ስፍራ የሄዝቦላ ‘መቀበሪያ’ ነው ሲል ገልፆታል።
    • የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጦርነቱን በሚመለከት አገራቸው “ለየትኛውም ሁኔታ” ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የእስራአል ግብ ከአሜሪካ ግብ ጋር የሚጣጣም ነው ብለዋል።
    • ኔታኒያሁ ይህን ያሉት እስራኤል እና ሊባኖስ ታሪካዊ የተባለውን ንግግር ማክሰኞ ዕለት ካደረጉ እና ሊባኖስ ንግግሩን “ውጤታማ”፤ እስራኤል ደግሞ ሁለቱም አገራት “በተመሳሳይ ገፅ” ላይ እንዳሉ ካሳወቀች በኋላ ነው።
  18. የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢራን ጦርነት የተነሳ ከትራምፕ ለሚደርስባቸው ጫና “እንደማይንበረከኩ” ተናገሩ

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በኢራን የሚካሄደውን ጦርነት እንዲቀላቀሉ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሚደርስባቸው ጫና “እንደማይንበረከኩ” ገለጹ።

    ስታርመር ይህንን ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ለስካይ ኒውስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ አሜሪካ የዩናይትድ ኪንግደምን እርዳታ በጠየቀችበት ወቅት “አልተገኘችም” ካሉ በኋላ ነው።

    ትራምፕ አክለውም ከዩኬ ጋር የተደረሰው የታሪፍ ስምምነት “መቼም ቢሆን ሊቀየር ይችላል” ብለዋል።

    የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርላማ ቀርበው ባደረጉት ንግግር “ሃሳቤን አልቀይርም፣ እጅ አልሰጥም፤ ጦርነቱን መቀላቀል የእኛ ብሔራዊ ጥቅም አይደለም፤ ስለዚህም አናደርገውም” ሲሉ አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል።

    “በኢራን ላይ ያለኝ [አቋም] ከጅማሬው አንስቶ ግልጽ ነው፤ እዚህ ጦርነት ውስጥ ተገድደን አንገባም” ብለዋል።

    “የእኛ ጦርነት አይደልም፤ የተለየ አቅጣጫ እንድይዝ ብዙ ጫና ተደርጎብኛል፤ ጫናው ዛሬ ምሽት የተፈጠረውንም ያካትታል” ሲሉ የትራምፕን ቃለ መጠይቅ አመልክተዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቃለ መጠይቁ የአሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ልዩ ግንኙነት እንዴት እንደሚገልጹት ተጠይቀው ነበር።

    “እገዛ ስንጠይቃቸው አልተገኙም፤ እንዲህ አይነት ግንኙነት ነው። ስንፈልጋቸው አልነበሩም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት የተነሳ የሁለቱ አገራት ግንኙነት የመሻከር ምልክቶች እየታዩበት ነው። የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር በጦርነቱ ውስጥ ቀጥታ እንዲሳተፉ የቀረበላቸው ጥሪ ውደቅ ማደረጋቸውን ተከትሎ ከትራምፕ ተደጋጋሚ ትችት ደርሶባቸዋል።

  19. ቻይና፤ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት አሳሰበች

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ መደበኛ የመርከቦች እንቅስቃሴ እንዲመለስ ጥረት መደረግ እንዳለበት ለኢራን አቻቸው አባስ አራግቺ ተናገሩ።

    ዋንግ በሆርሙዝ ወሽመጥ የኢራን ሉዓላዊነት እና ደኅንነት መከበር እንዲሁም መጠበቅ ያለበት ቢሆንም በውሃ አካላት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም ነፃነት እና ደኅንነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

    ሁለቱ ሚንስትሮች በስልክ ባደረጉት ውይይት ዋንግ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት ዓለም አቀፍ ፍላጎት እንዳለ ገልፀዋል።

    “በወሽመጡ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለስ መስራት የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ሙሉ በሙሉ ጥሪ ነው” ማለታቸውን መንግሥታቸው ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

    የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአሁናዊ ሁኔታው በጦርነት እና በሰላም መሀል የሚገኝ ወሳኝ እጥፋት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰላም በር እየተከፈተ መሆኑን መናገራቸውን ኤፒ ዘግቧል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቻይና የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲፀና እና ንግግሮች እንዲቀጥሉ ድጋፍ ታደርጋለችም ብለዋል።

  20. አሜሪካ የወታደራዊው ዘመቻ “አቻ” የሆነ ኢኮኖሚያዊ እርምጃ በኢራን ላይ ልትወስድ መዘጋጀቷን አስታወቀች

    አሜሪካ ከወታደራዊው ዘመቻ “አቻ” በሆነ ደረጃ በኢራን ፋይናንስ ላይ ጫና ማሳደር የሚያስችል እቅድ እያጠናቀቀች መሆኗን የግምጃ ቤት ኃላፊው ስኮት ቤሴንት ተናገሩ።

    የትራምፕ አስተዳደር የኢራን ኢኮኖሚን ይበልጥ ለማሽመድመድ ያቀደበትን እቅድ ተግባራዊ የሚያደርገው አሜሪካ እና ኢራን በቶሎ ስምምነት ላይ ካልደረሱ መሆኑን የዜና ወኪሉ አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል።

    የግምጃ ቤት ኃላፊው ቤሴንት ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ የኢራን ፋይናንስ ላይ ጫና የሚያሳድረው “ኦፕሬሽን ኢኮኖሚክ ፊውሪ” እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ወታደራዊ ጥቃት ሲከፍቱ ለዘመቻው የተሰጠው ስያሜ “ኦፕሬሽን ኢፒክ ፊውሪ” የሚል ነበር። ከወታደራዊው ዘመቻ ጋር ተመሳሳይ መጠሪያ የሚይዘው ኢኮኖሚያዊ ጫና የቦንብ ድብደባው እኩያ እንደሚሆን ቤሴንት ገልጸዋል።

    ኢራን ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን በመደብደብ ስህተት ሰርታለች ያሉት የግምጃ ቤት ኃላፊው፤ በአሁኑ ሰዓት ጥቃት የተፈጸመባቸው በባንክ ስርዓቶቻቸው ውስጥ ያሉትን የኢራን ፈንዶች “ግልጽ” ያደረጉ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

    እነዚህ አገራት በባንክ ስርዓታቸው ውስጥ የሚገኙ የኢራን አብዮታዊ ዘብ አመራሮች አካውንቶችን እንቅስቃሴ እንዲያግዱ አሜሪካ መጠየቋንም አስታውቀዋል።

    በተጨማሪም አገራቱ የኢራንን ነዳጅ እንዳይገዙ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል። አገራቱ በባንክ ስርዓቶቻቸው ውስጥ የኢራን ገንዘብን የሚያስቀምጡ ከሆነ ሁለተኛ ደረጃ ማዕቀብ እንደሚጣልባቸው ገልጸዋል።

    የኤፒ ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ ሁለተኛ ደረጃ ማዕቀብ የሚጣለው ከኢራን ጋር የንግድ ልውውጥ በሚያደርጉ፣ ግለሰቦች፣ ተቋማት እንዲሁም በኢራን ቁጥጥር ስር ባሉ መርከቦች ላይ ነው። አሜሪካ አጋር እንደሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንዲሁም እንደ የዋሽንግተን ተቀናቃኟ ቻይና ያሉ አገራትም ማዕቀቡ ሊደርስባቸው ይችላል።

    ቤሴንት፤ “የኢራንን ነዳጅ የምትገዙ ከሆነ፣ በባንኮቻችሁ ውስጥ የኢራን ገንዘብ ተቀምጦ ከሆነ ሁለተኛ ደረጃ ማዕቀብ ልንጥልባችሁ ፈቃደኛ ነን ብለን ለኩባንያዎች፣ ለአገራት ነግረናቸዋል” ብለዋል።

    ይህ እርምጃ ኢራን ውስጥ “የተመለከትነው [ወታደራዊ] እንቅስቃሴ የፋይናንስ እኩያ እንደሚሆን ኢራናውያን ማወቅ አለባቸው” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

    ከመግለጫው በኋላ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ከኢራን ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና መርከቦች ላይ ማዕቀቦቹን መጣሉን ይፋ አድርጓል። ማዕቀብ የተጣለባቸው ሦስት ግለሰቦች፣ ዘጠኝ መርከቦች እና 17 ተቋማት ናቸው።